ጠቅላይ ሚንሥትሩ በአውሮጳ ኦነግ እንዲሁም አዲሷ ተሿሚ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 02.11.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጠቅላይ ሚንሥትሩ በአውሮጳ ኦነግ እንዲሁም አዲሷ ተሿሚ

በኢትዮጵያ የፌዴራል ጠ/ፍርድ ቤት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ፕሬዚዳንት ኾነው መሾማቸው፤ የጠቅላይ ሚንሥትሩ የአውሮጳ ጉብኝት እና በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ ርምጃ መውሰድ መጀመሩ የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የሚያጠነጥንባቸው ርእሰ ጉዳዮች ናቸው።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:45

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በኢትዮጵያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ ፕሬዚዳንት መሾማቸው፤ የሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዐቢይ መነጋገሪያ ኾኗል። በበርካቶች ዘንድ በቀድሞ ሥራቸው ለሚታወቁት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ከፍተኛው ሹመት መሰጠቱ ከየአቅጣጫው ድጋፍ አስገኝቷል። አዲሷ ተሿሚ በይበልጥ የሚያወቁት በሴቶች እኩልነት በእንግሊዝኛው አጠራሩ (feminism) አቀንቃንነታቸው ነው ሲሉ አስተያየት የሰጡም አሉ። የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የአውሮጳ ጉዞ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ ድጋፍ እና ትችት ተሰንዝሮበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር  በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ ትጥቅ ርምጃ መውሰድ መጀመሩ ሌላው መነጋገሪያ ርእስ ነበር።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ለሦስት ቀናት የአውሮጳ ጉብኝት ከሀገር መውጣታቸው እንደተሰማ ነበር የኦነግ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉና በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ግጭት መከሰቱ የተነገረው። ግጭቱ በእርግጥ ከጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓም ቅዳሜ ጀምሮ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቤግ ከተማና በቀለም ወላጋ ዞን በግዳም ከተማ መካከል በጋራ አካይና ላጋ ሃዳ ጃርሳ በሚባሉ ቦታዎች ተከስቶ እንደነበር ተገልጦም ነበር።

በሥላቅ ጽሑፎቹ የሚታወቀው አበበ ቶላ፦ «በሕዝብ መሃል በሚደረግ ጦርነት ማን ያሸንፋል!?» ሲል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ትጥቅ ያለመፍታቱን ጉዳይ በተመለከተ ተችቷል። «ኦነግ መሣሪያ አልፈታም ማለቱ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው!» ያለው አበበ «የኦሮሞ ሕዝብ ላለፉት ዓመታት በመንግሥት ታጣቂዎች ሲገደል እና ሲቆስል የኖረው ከበቂ በላይ ነው። ትላንት የኦሮሞ ልጆች በየቦታው በመንግሥት ሲታፈኑ እና ሲገደሉ አንድም ርምጃ ያልወሰደው ኦነግ ዛሬ ሃገር ከተረጋጋ በኋላ የሰለጠነ ፖለቲካ አራምዶ ለሕዝቡም ለሃገሪቱም የሚበጅ ሰላማዊ ትግል እንደማድረግ 'መሳሪያዬን አለቅም' ብሎ ሙጭጭ በማለት ሕዝቡን ምንም ዋጋ ለሌለው ጦርነት መዳረግ ተገቢ አይደለም» ብሏል።

ዮሐንስ ሽመልስ፦ «ፖለቲካዊ ትርጉም» የሚል ርእስ በሰጠው የፌስቡክ ጽሑፉ፦ ኦነግ ሀገር ቤት ሲገባ ትጥቅ እንዳልነበረው መንግሥት መናገሩን ገልጧል። ኦነግ በበኩሉ፦ «ሸርና ደባ በኢሕአዴግ» እየተፈጸመበት መኾኑን መጥቀሱን ተናግሯል። «ሰሞኑን ባደረጋችሁት ውጊያ ተጠያቂው ማን ነው? ስንት ሕዝብስ አለቀ?» ሲል ደግሞ የሚጠይቀው ያዬሰው ነው። «ኦነግ አገር ቤት ገብቶ ሲታጠቅ መንግስት የማንን ጎፈሬ እያበጠረ ነበር?» ሲል ጥያቄውን ያክላል። «አስመራ ላይ የተፈራረማችሁትን ሰነድ ለምን ይፋ አታደርጉትም?» ሲልም ጥያቄ አቅርቧል።

ታደሰ በሚል የትዊተር ስያሜ የቀረበ ጽሑፍ፦ «ኦነግ አስቸጋሪ ኾኖ አይደለም፤ የትእግስት ጉዳይ ኾኖ እንጂ» ሲል ይነበባል። «ከባዱን መንገድ ከኾነ ምርጫቸው በጣም ቀላል ነው፤ መንግሥት ርምጃ ይወስዳል» ሲል ይጠናቀቃል የታደሰ ጽሑፍ።  ተሾመ ኤም ባረጎ በተሰኘ የትዊር ስም የቀረበ ጽሑፍ፦ «የኦነግ ደጋፊዎች ሕወሓት ታጥቋል እና እኛም ይላሉ። ኾኖም ኦዴፓ በመንግሥት ውስጥ ኦሮሞን እንደሚወክል ዘንግተውታል። ኦነግ በኦሮሚያ ፖሊስ ውስጥ እንዲቀየጥ ከተፈቀደለት የአርበኞች ግንቦት 7ም በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋ እና እንደውም በመሠረቱ በሁሉም የኢትዮጵያ የፌዴራል ክፍሎች ያሉትን ወታደራዊ ክፍሎች ሊይዝ ይገባል» ይላል።

በDW ፌስቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል መሣይ ቢፋ በእንግሊዝኛ ቋንቋ፦ «ድል ለኦነግ» ሲል ጽፏል። ዘነበ ብሩ፦ «ኦሮሞ የሚጠቃው በልጆቹ ነው» ብሏል። ፋንታሁን ዐወቀ አጠር ባለው አስተያየቱ፦ «ኦነግ መች ተቀየረ የዘር ፖለቲካ ይዞ» ብሏል። ማሚት አሠፋ፦ «አቶ ለማ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ሲሉ ኦነግ ደግሞ ጫካ ሱሴ ነው ብለዋል» ስትል መሣይ ጥበቡ፦ «40 ዓመታት ጫካ፤ ካለምንም ውጤት ጫካ ውስጣቸው ነው ሱስ» የሚል አስተያየት አስፍሯል። መኮንን ቀጀላ፦ «እግዚአብሔር ከመናቆርና ከመገዳደል አንድ ያርገን ያፋቅረን» የሚል አስተያየት ሰጥቷል። ሙሉጌታ አንዳርጌ፦ «ኦነግ የሚጠይቀው ጥያቄ ካለ፤ በሰላምና በውይይት ቢፈታ ይመረጣል። የኣንድም ሰው ሕይወት መጥፋት የለበትም» ሲል ቅድሚያ ለሠላም አጽንዖት ሊሰጠው እንደሚገባ አስረግጧል።

የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የአውሮጳ ጉዞን በተመለከተ ዐይናለም ጸጋዬ፦ «ይኽ ድንቅ ከኾነ መሪ የምንጠብቀው ነው፤ እናመሠግናለን ዶክተር ዐቢይ አህመድ» ሲል አድናቆቱን ገልጧል። ከጠቅላይ ሚንሥትሩ የፍራንክፉርት ንግግር ቀደም ብሎ ቲጂ ዜድ በሚል የፌስቡክ መጠሪያ የቀረበ አስተያየት እንዲህ ይነበባል። «ጀርመን ጠቅላይ ሚንስትሩን ለመደገፍ የተዘጋጃቹ እባካቹ ሀገሩ ላይ እየተበደለ እና እየተፈናቀለ ያለውን ሕዝባችሁን አትርሱ!!! ጠቅላይ ሚንስትሩን አገር ሳትበታተን የሕዝቡን ጩኸት ትኩረት እንዲሰጡት የሕዝባችሁን ጩኽት አስተጋቡ!! ፍትኅ ለተጨቆኑ የኢትዮጵያ ልጆች።»

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ጀርመን ፍራንክፈርት ንግግር ሲያሰሙ ከተጠበቀው ቁጥር ያነሰ ታዳሚ ነው የተገኘው።  ንግግራቸውን ያደመጡ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በርካታ ተጠቃሚዎች ለጠቅላይ ሚንሥትሩ አድናቆታቸውን ገልጠዋል። ዐይናለም ጸጋዬ፦ «ይኽ ድንቅ ከኾነ መሪ የምንጠብቀው ነው፤ እናመሠግናለን ዶክተር ዐቢይ አህመድ» ሲል አድናቆቱን ገልጧል። አብርሐም በእንግሊዝኛ የሺብር በአማርኛ ትዊተር ላይ ሁለቱም፦ «የቃላት ማሳጅ ብቻ» ብለዋል። እጅግ ድንቅ ንግግር ሲሉ አድናቆታቸውን የገለጡ በርካቶች ናቸው። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙዎች የተቀባበሉት ከጠቅላይ ሚንሥትሩ ንግግር የተቀነጨበ ው የሚከተለው ነው።

«ግን እርግጠኛ መኾን ያለባችሁ አንድ ነገር፤ ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክ እና መልክ እንደ ቂጣ ጠፍጥፎ የሚጋግራት የግል ርስት ሳትሆን፤ ዘመናትን ያስቆጠረች ታላቅ ሕዝብ የመሰረታት ታላቅ ሀገር መኾኗን ነው። እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው እንዲሉ ሀገሬ አንቀላፍታ ይኾናል እንጂ አልሞተችም። ኢትዮጵያ ደክሟት ይሆናል እንጂ አልተሸነፈችም! እምዬ ቀጥና ይኾናል  እንጂ አልተበጠሰችም።»

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ፈረንሳይ ፓሪስ፤ ጀርመን በርሊን እና ፍራንክፉርት ከተሞች ተጉዘው ኢትዮጵያ በተመሰለሱ ቅፅበት የተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ሹመት ሲሰጡ መታየታቸውን በተመለከተ ማሂ የካሡ ልጅ፦ «እረፍት እየወሰደ ነው ግን ስትል ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡ እንደተሰማ ወዲያው ነበር ሰፊ መነጋገሪያ የኾነው። ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በተሾሙበት እለት ካሠሙት ንግግር ቀጣዩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተንሸራሽሯል።

ወ/ሮ  መዓዛ አሸናፊ ሹመትን በተመለከተ ከተሰጡት በርካታ አስተያየቶች መካከል በDW የፌስቡክ ገጽ ላይ የተሰጡትን የተወሰኑትን እናስቀድም።

«ለውጡ እያስደመመን ነው በትክክል በሚገባት ቦታ በችሎታዋ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው እኔ የምለው የስልጣን ጥመኞችን ወገብ የሰበረ ሥራ መሆኑ ትልቅ አድናቆት አለኝ» የነጋሢ በራኪ አስተያየት ነው። አህመድ ሲራጅ፦ «ሴቶች እየተደሰቱና እየፎከሩ ቢሆንም የማደንቃቸው ግን ሥራቸውን ሠርተው ለሀገሪቱ ውጢታማ ሲሆኑ ብቻና ብቻ ነው የኔም አድናቆቴን እገልፃላቸዋለው» ብሏል። ለአህመድ አስተያየት ፋይዛ ሞሐመድ፦ «እናንተ ያለ እኛ ምንም ናችሁ እቤት ውስጥ ውጤታማ እንደሆንን በሀገር ጉዳይም እንሰራለን ስንል እንሰራለን አንቀልድም» ስትል መልስ ሰጥታለች።

ጋዜጠኛ ቆንጂት ተሾመ፦«ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ሴት መኾናቸው ተጨማሪ ጥቅም ይሰጣል እንጂ ባላቸው የትምህርት ዝግጅት፣ ልምድና ሰብዕና ብቻ እንኳ ብንመዝናቸው ለተሾሙበት የሥራ ኃላፊነት እጅግ የሚመጥኑ ናቸው። የኢትዮጵያ የፍትኅ ሥርዓት ለሴቶችም ለወንዶችም እኩል ጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሆን ይሰራሉ ብዬ አምናለሁ። መልካም የስራ ጊዜ ለእመቤት መዓዛ» ብላለች። ሹመቱም እጅግ ተገቢ መኾኑን ገልጣለች።

ቬሮኒካ መላኩ ፌስቡክ ላይ፦ «የፍትኅ ቅርንጫፉ ደህና ሰው ያገኘ ይመስላል። መአዛ ካልሰነፈች ትችላለች ብቻ ሳይሆን በደንብ አድርጋ ትችላለች» ስትል አድናቆቷን ገልጣለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic