1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደበዘዘው ግንቦት 20፤ ምክክር በአዲስ አበባ፣ የኢሰመኮ ማሳሰቢያ

ዓርብ፣ ግንቦት 23 2016

በየሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛው መድረክ የሚነጋገርባቸው ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች እጅግ በርካታ ናቸው። ለዚህ ሳምንት በሦስት ዐበይት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች የተሻሉ ካልናቸው የተወሰኑትን መራርጠናል።

https://p.dw.com/p/4gVww
ብሔራዊ ምክክር
በአዲስ አበባ የተጀመረው ብሔራዊ ምክክርምስል Solomon Muchie/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ግንቦት 23 ቀን 2016

 

የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፊውዳል ዘውዳዊ አገዛዝ አላቅቄ ወደ እኩልነት አስተዳደር አሸጋግራለሁ ያለው ወታደራዊ መንግሥት እራሱን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር ብሎ ይጠራ በነበረው ኃይል ከሥልጣን ከተወገደ ዘንድሮ 33 ዓመት ደፈነ። ለ27 ዓመታት የ17 ዓመቱን መራር የትጥቅ ትግል በመዘከር በድምቀት ይከበር የነበረው የደርግ አገዛዝ የወደቀበት ግንቦት 20 በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት እንደዋዛ ማለፉ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ይህን ካስተዋሉት አንዱ ይስሀቅ አብርሃም፤ «መቼም ቢሆን ጉልበተኞች ሥልጣን የያዙበት ቀን በዐል ሁኖ የሚከበረው ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ብቻ ነው።» ሲሉ፤ አዲስ ዘመን አዲስ ዘመን በበኩላቸው፤ «ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ህዝብ በብሔር፣ በጎሳ፣ በጠላትነት እንዲተያይ የተደረገበት፣ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችበት ፣ የኢትዮጵያን ሠራዊት የተበተነበት። ግንቦት 20 ኢትዮጵያ በጭለማ የተዘፈቀችበት ለውጥ ነው። ተማርን ያሉ ስዎች ናቸው ሀገሪቱን እንጦሮጦስ የከተቷት። ባልተማሩ ሰዎች የሚመሩ ሃገራት በልምድ ሀገር እና የሕዝቦቻቸውን ሕይወት ሲለውጡ የእኛ ምሁሮች ያወረሱን በዘር ከረጢት ውስጥ መወሸቅን ነው።» ይላሉ። ከእሳቸው ሃሳብ የሚቀራረብ አስተያየት ያጋሩት ደሳለኝ ተሰማም እንዲሁ፤ «ግንቦት 20 በኢትዮጵያ ለዘረኝነት እዉቅና የተሰጠበት፣ በታሪካችን ጠባሳ ጥሎ ያለፈበት ቀን በመሆኑ እስከ አሁን ሕዝባችን በዘር ቆጠራ ተዘፍቆ የእርስ በእርስ ጦርነት ልዩ መገለጫ የሆነ ችግር አውርሶን በማለፋ ዋንኛ ችግር ነዉ ።» ነው የሚሉት። እደግ ዓለሙ፤ «ግንቦት 20 የሚባል ቀንን ለመስማት አልፈልግም።» ነው የሚሉት፤ ምክንያት ያሉትን ሲዘረዝሩም፤ «ይህ ክፉ ቀን የትውልድን ራእይ ያመከነ ፤ መጠፋፋትን የወለደ ፤ የግል ጥቅመኝነት ያሰፈነ ፤ ዜጎች ሀገራቸውን ሳይሆን በብሔራቸው ብቻ እንዲያስቡ ያደረገ፣  በመሆኑ ውግዘት እንጂ መታሰብ የሌለበት ዕለት ነው።» ባይ ናቸው። ጌታሁን ናደው ግን፤ «የቋንቋ የባህል የማንነት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ምላሽ ያገኘበት ወቅት እና ከአሃደዊ ጨፍላቂ ባላባታዊ ሥርዓት ነፃ የወጣንበት ግንቦት 20ን እናከብራለን።» ብለዋል። የንጉሥ ልጅ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ፣ «ግንቦት 20 ተመልሳ ትመጣለች ብለን በጉጉት ብንጠብቃት ጭራሽ የካቲት 24 ሆና መጣች።» አሉ፤ ጌታሁን ናደው ደግሞ፤ «ግንቦት 20 የማይከበር ከሆነ ደርግ ወደ ሥልጣን ይመለሳል።» ነው የሚሉት። ታደሰ ደምሴ ግን፤ «አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት አሁንም ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል።ትግል ትግል...» ሲሉ፤ አቡ ቢላሊ ቶይቤ፤ «ዘላለም በእራሷ ጨካኝ ልጆች ቅኝ ስትገዛ የኖረች፤ የምትኖር ሀገር።» ብለዋል።

የኢህአዴግ አርማ
የኢህአዴግ አርማ

ከቀናት በፊት ነው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን «ኢትዮጵያ እየመከረች ነው» በሚል የሀገራዊ ምክክር መባቻ መርሐግብሩን አዲስ አበባ ላይ ይፋ ማድረጉ የተነገረው። የምክክሩን ሃሳብ በአዎንታዊነት የሚያነሱት በርካታ ቢሆኑም በጥርጣሬ እንዲሁም በጥያቄ የሚመለከቱትም ጥቂት አይደሉም። ሀሰን አህመድ፤ «ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም የሆናል ብለን ብናየው ጥሩ ነው።» ሲሉ፤ ደሳለኝ ተሰማም፤ «ጭቅጭቅ ንትርክ ጠፋቶ ሁሉም ወገን ወደ ቀልቡና ልቦናዉ ተመልሶ አገራችንን የምንጠቅምበት ዘመን ፈጣሪ ያምጣልን አሜን።» ይላሉ። መጋቢት ተስፋዬ ግን ይጠይቃሉ፣ «ቆይ ከማን ጋር ነዉ ምትመክሩት የተለየ ሐሳብ ያላቸው ሁሉ ቂልንጦ፣ ቃሊቲ፣ አዋሽ አርባ፤ ሌላዉ ስደት ላይ፣ ፋኖና ኦነግ ጫካ፤ ከራስ ጋር ምክክር? እኔ በግሌ ሁለተኛው ዙር ከእዳ ወደ ምንዳ ስልጠና ብየዋለሁ።» በማለት። ሰሚራ ሁሴን አህመድ ደግሞ፤ «ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ህዝቦቿ ግን በጦርነት እየጋዩ ነው።» ብለዋል። ሻይሉ ደነቀ የም፤ «ጦርነት ላይ ያለች ሀገር ሀገራዊ ምክክር እያደረኩ ነው ስትል ከማየት በላይ የሚያስገርም ነገር የለም።» ነው ያሉት። ለማ ዲሬ፣ ጥያቄዎቻቸውን በተራ ቁጥር ሰድረዋል፤ «1ኛ ገለልተኛ የሆኑ አካላትን ያሳትፋል ወይ? 2ኛ_ በሀገራችን ውስጥ ያሉት ተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሐሳብን ያካተተ ነው ወይ? 3ኛ_ መሣሪያ በመታጠቅ በየጫካው እና በየአካባቢው ሰዎች በሠላም ወጥተው በሠላም መግባት የሚከለክሉትን ታጣቂዎች በሃሳብ ሆነ በሌላ በሌላው ያሳተፈ ምክክር ነውን????» በማለት ጥያቄዎቻቸውን በበርካታ የጥያቄ ምልክት አጅበው ሃሳባቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል።

HD HD የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሀገራዊ ምክክሩን «ጊዜ መግዣ ነው» ሲሉት፤ ጎመን በጤና ደግሞ «በህዝብ ላይ ይቀለዳል» ነው የሚሉት። ፍሬሕይወት ተሾመ በበኩላቸው፤ «እውነት ነው ሀገራዊ ምክክር የሚያስፈልግ አፈንግጦ ለወጣ፣ ነፍጥ ካነሳ፤ ካኮረፈ ጋር እንጅ ተስማምቶት እየተገዛ ከለው ጋር ምክክር ልፋት እና ሀብት ብክነት ብቻ ነው ትርፉ።» ነው የሚሉት። በርከት ያሉት አስተያየት ሰጪዎች የምክክር ኮሚሽኑን ገለልተኛነት ዛሬም የሚጠይቁ ናቸው። አብርሃም በሀይሉ፤ «አገራዊ የምክር ኮሚሽኑ በመንግሥት ካድሬዎች የተሞላ ስለሆነ ምንም ለውጥ አያመጣም የሚሰማውም የለም።» ነው የሚሉት።  ቴዎድሮስ አሰፋ፤ «የምክክር ኮሚሽኑ ገለልተኛ ነው ብዬ አለምንም ከንቱ ልፋት ነው ፈጣሪ ይርዳን።» ብለዋል። ወፍ የለም የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «አገራዊ የምክክር ኮምሽኑ በገዥው ፓርቲ የሚዘወር መሆኑ እውን ነው። ምክንያቱም በምክክር ሂደቱ አስፈላጊና ጠቃሚ አጀዳዎችን የሚሰጡ የፖለቲካ ሰዎች ያለምንም ፍርድ እስር ቤትናቸውና ። ዜጎች በብሔራቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ከእስር ባልተፈቱበት ሁናቴ በባዶ ሜዳ አገራዊ መግባባት ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል ማለት አስቂኝ ድራማ መሆን አለበት።» በማለት ይሞግታሉ። ልኑር ካንቺጋርም ጥያቄ አላቸው፤ «የምክክር ኮምሽኑ በማን ትዛዝ ነዉ የሚንቀሳቀሰዉ ?» የሚል።

ብሔራዊ ምክክር
ከቀናት በፊት ነው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን «ኢትዮጵያ እየመከረች ነው» በሚል የሀገራዊ ምክክር መባቻ መርሐግብሩን አዲስ አበባ ላይ ይፋ ማድረጉ የተነገረው።ምስል Seyoum Getu/DW

ጌቴ ተሰማ፤ «የምክክሩን ኮሚሽን የሚመሩት ጥልቅ እውቀት ያላቸው ለሀገራቸው ሲሉ እንጂ ምንም ያላጡ ናቸው። ለህዝባቸው ታሪክ ሠርተው ማለፍ የሚፈልጉ ስለሆነ እናግዛቸው። እኛ እንጂ እነሱ የሚያጡት የለም። ህዝባችን ሰላም ከፈለገ ያግዛቸው።» ይላሉ። ጎታ ባዶ ኮፋሌ በበኩላቸው፤ ፣«ይህን ኮምሽን ሰዉ ለምን ማመን አቃተዉ?? የሀገሪቱ ችግር ፖለቲካዊ ስለሆነ ይመስለኛል።» ብለዋል።

ሀብታሙ ቦ፤ «እኔ በበኩሉ በዚህ አደገኛ ውጥረትና ጦርነት ውስጥ ሆኖ የሚካሄደውን ምክክር ውጤታማነት እጠራጠራለሁ።» ነው ያሉት። ታሪኩ ጉራራ በበኩላቸው፤ «የዚህች ሀገር ችግር የፖለቲከኞችና የፓርቲዎች በውስጣቸውም ሆነ እርስ በእርስ አለመስማማት ነው። ስለሆነም መፍትሄው በንቃት በፖለቲካው ውስጥ በሚሳተፉ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች መካከል ግልጽ ውይይት እንዲካሄድ ማድረግ እንጂ ሰላማዊውን እና በፖለቲካው ተሳትፎ የሌለውን ማኅበረሰብ ሰብስቦ ማወያየት አይደለም።» ብለዋል። ደስታው መንግሥቶ ኖ መንግሥቶ በፋንታቸው፤ «እንደኔ አስተሳሰብ ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ ምክክሩ ውጤት አያመጣም ባይ ነኝ።» ሲሉ ሀሰን ጂቢቾ ግን፤ «ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ጠመንጃ እና ጉልበት አያስፈልግም ። በመመካከር ፣ በመደማመጥ እና ሰጥተው በመቀበል መሆን አለበት።» በማለት ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አርማምስል Ethiopian Human Rights Commission

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ዐውድ ውስጥና ውጭ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ስጋቶችን በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል። ኮሚሽኑ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ ሁሉንም የትጥቅ ግጭቶች በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና የሰብአዊ መብቶችን መከበር ማረጋገጥ እንደሚገባ ያሳሰበበት መግለጫም የብዙዎችን ትኩረት ከሳቡ የሰሞኑ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ነው። ነገሪ አምደ ጽዮን፤ «ይህ ሪፖርት በአማራና በሌሎች ኢትዮጵያዊን ላይ ከተፈጸመባቸው ጭፍጨፋና ግፍ 10 በመቶውን እንኳ አይገልጽም፡፡» ባይ ናቸው።

ወፍ የለም የሚል መጠሪያ የያዙ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ለሚፈጥራቸው ዘርፈ ብዙ መዓቶች ኢትዮጵያውን በሁሉም ማዕዘናት ዝምታንና በፍራቻ ውስጥ መኖርን የመረጡ ይመስላል። መብታቸውን ከመጠየቅ ይልቅ ፈጣሪ በመዓት ወርዶ ችግሮቻቸውን እዲፈታላቸው የሚጠብቁ ሞኞች የበዙባት አገር ሆናለች።» ነው ያሉት። ኢቢ ኤች ኤፍ ዲም እንዲሁ በኤክስ ገጻቸው፤ «ውድ ኮሚሽነር ዜጎቻችሁ ለሰላም እየጮሁ ነው፤ ለሚፈጸመው የመብት ጥሰትም የሕግ የበላይነት እንዲከበር እየጠየቁ ነው። ሰላሌ፣ ሆሮጉዱሩ፤ ምዕራብ ወለጋ፤ ጉጂ፤ ቦረና ስለሚገደሉት፣ ንብረታቸውንና ክብራቸውን ስለሚያጡት ዜጎች ያቀረባችሁት ዘገባ የት አለ?» ሲሉ የበኩላቸውን ጥያቄ አቅርበዋል። ቶላ ጋዲሳ ኢንሰርሙ፤ «የእኔ ጥያቄ ይህ ሁሉ ትንተና ለማን ነው የሚቀርበው ወይም የሩብ ዓመት ዘገባ ይሆናል እንጂማ ለዚህ ሁሉ ተሳታፊ አካላቶችን (engaged actors) ተጠያቂ ሊያደርጋቸዉ አይመስለኝም። እንደተለመደው እኛ ማንኛውም የሚወጣ ዘገባ ከማዳመጥ ባለፈ ምንም የምንለው ነገር የለም። እየሆነ ያለው ግፍ ግን በጣም የሚያሳዝን ነው።» በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ሸዋዬu ለገሠ

እሸቴ በቀለ