1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት የሳሞአ ሥምምነት እንድትወጣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ

ማክሰኞ፣ የካቲት 5 2016

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች ህዳር 2016 ዓ. ም የተወሰኑ የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የፓሲፊክ ሀገራት የንግድና የኢኮኖሚ አሳሪ የአጋርነት ስምምነትን ከአውሮፓ ኅብረት ጋራ ``የሳሞአ ስምምነት`` መፈራረማቸውንና ኢትዮጵያ አንዷ ፈራሚ መሆኗን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ራሷን ከስምምነቱ እንድታገል ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4cLxn
Äthiopien Interreligiöse Konferenz in Gonder
ምስል Gondar City Administration Government/Communication Affairs Department

"ግብረሶደማዊነት እንቃወማለን"

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገርን እጅግ የሚጎዱ  አንቀጾች የተካተቱበት እና "ለሀገራችን ሕዝብ ዕድገትን ሳይሆን ውድቀትን፣ ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠትን የሚያስከትል፣  የሀገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል" ያለውና መንግሥት ፈርሞታል ካለው አለም አቀፍ ስምምነት እንዲወጣ ጠየቀ። 

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች ህዳር 2016 ዓ. ም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑ የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የፓሲፊክ ሀገራት ተፈራረሙት ካለው ስምምነት ኢትዮጵያ ራሷን እንድታገል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ስምምነቱን ባለማጽደቅ አደራውን እንዲወጣ ሲሉ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "የኢትዮጵያ መንግሥት እንደዚህ አይነት ሥምምነት አፀድቃለሁ ብሎ አልፈረመም።" በማለት ጉባኤው "የተሳሳተ መረጃ " እንዳለው ለዶቼ ቬለ ገልጿል።


``አደገኛ የተባሉት አንቀጾች ተፈጻሚ አይሆኑም`` - ጉባኤው

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች ህዳር 2016 ዓ. ም የተወሰኑ የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የፓሲፊክ ሀገራት ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ጸንቶ የሚቆይ የንግድና የኢኮኖሚ አሳሪ የአጋርነት ስምምነትን ከአውሮፓ ኅብረት ጋራ ``የሳሞአ ስምምነት`` መፈራረማቸውንና ኢትዮጵያ አንዷ ፈራሚ መሆኗን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ራሷን ከስምምነቱ እንድታገል ጠይቀዋል። 

Logo | Inter Religious Council of Ethiopia
ምስል Inter Religious Council of Ethiopia

ለዚህ በምክንያትነት የተጠቀሰውም "የአጋርነት ስምምነቱ ከሃይማኖት መሠረታዊ አስተምህሮ የወጡና የሀገራችንን ባሕልና ነባር እሴቶችን የሚንዱ ፣ ግብረሶዶማዊ ልምምዶች ቀጥተኛ ባልሆነ አግባብ የተካተቱ መሆናቸውን" በመጥቀስ አደገኛ ያላቸው አንቀጾች ተፈፃሚ ሊሆኑ እንደማይችሉ አስታውቋል።

ተፈረመ የተባለው ስምምነት ምን ይዟል ?

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ መስዑድ ዐደም ጉባኤው ከተቃወማቸው አንቀጾች ጥቂቶቹን ገልፀዋል። ተከናወነ የተባለው የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር የአጋርነት ስምምነት በዋናነት የሰብዓዊ መብቶች፣ የዲሞክራሲና የአስተዳደር፣ የሰላምና ደኅንነት፣ የሰብዓዊና ማኅበራዊ ልማት፣ አካታች የሆነ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ፣ እና የሰዎች ፍልሠትና የመዘዋወር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቢሆንም ኢ- ግብረ ገብ የሆኑ አንቀጾችን ማካተቱንም አቶ መስዑድ ገልፀዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሃይማኖቶች መሠረታዊ አስተምህሮ፣ ከዶግማዊና ቀኖናዊ ጉዳዮች ጋር የሚቃረኑና  የማይስማሙ ወይም ተቀባይነት የሌላቸው አንቀጾች በኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታና ደረጃ በምንም መልኩ ፍፁም ተፈፃሚ ሊሆኑ እንደማይችሉ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ 


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ መንግሥት ጉዳዩን በውል እንዲያጤነው ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው መንግሥትን በጉዳዩ ላይ ማብራርያ መጠየቁን አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ "የኢትዮጵያ መንግሥት እንደዚህ አይነት ሥምምነት አፀድቃለሁ ብሎ አልፈረመም"። የጉባኤው የሥራ ኃላፊዎች "ያላቸው መረጃ የተሳሳተ ነው" ሲል ለዶቼ ቬለ ምላሽ ሰጥቷል።

ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ