1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍልሰት ሕግ ማሻሻያ

ማክሰኞ፣ የካቲት 28 2015

ጀርመን በተለይም ከፍተኛ ክህሎት ያላቸውን የውጭ ዜጎች ለማስገባት ሕጎችን ብታወጣም መስፈርቶቹ የሂደቱ ውስብስብነትና አዝጋሚነት ብዙዎችን ሊስብ አልቻለም። ሚኒስትር ኃይል በዚህ ረገድ ችግሮች መኖራቸውን አምነው የትምህርት ማስረጃዎች እውቅና አሰጣጥ ፣ የቪዛ መጓተትና የመሳሰሉት ከተስተካከሉ ሁሉም ወገን ተጠቃሚ ይሆናል የሚል ተስፋ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4OMgh
Afrika Entwicklungsministerin Schulze und Arbeitsminister Heil in Ghana
ምስል Isaac Kaledzi/DW

ጀርመን ያቀደችው የፍልሰት ሕግ ማሻሻያ

የአዛውንቱ ህዝብ ቁጥር ወደፊት እየጨመረ በሚሄድባት በጀርመን የተተኪው ሰራተኛ ኃይል ጉዳይ ከወዲሁ ማሳሰቡ አልቀረም።አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት  ከ 12 ዓመት በኋላ በጡረታ መውጫ እድሜ ማለትም 67 ዓመትና ከዚያ በላይ እድሜ ውስጥ የሚገኙ  አረጋውያን ቁጥር ከአራት እስከ 20 ሚሊዮን ይደርሳል የሚል ግምት አለ። ከዚህ ሌላ በሀገሪቱ በተወሰኑ የሙያ ዘርፎች ውስጥ የሚታየው በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ሰራተኛ እጥረትም ሀገሪቱ ከወዲሁ የተዘጋጀችበት ጉዳይ ነው። የጀርመን መንግሥት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ባለሞያዎችን እጥረት ለማቃለል በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ የውጭ አገር ባለሞያዎች የጀርመንን የስራ ዓለም በቀላሉ ሊቀላቀሉ እንዲችሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። መንግሥት በዚህ ጥረት  አፍሪቃውያን ሠራተኞችንም ጭምር ለመሳብ ያስችላል ያለውን የተሻሻለ የፍልሰት ሕግ በቅርቡ ለማውጣት አቅዷል። ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ የምጣኔ ሀብትና የስራ አስተዳደር ባለሞያ መንግስት ለጉዳዩ  ትኩረት የሰጠው  በተለይ በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ያስረዳሉ ። እርሳቸው እንደሚሉት አንደኛው ወደፊት ለጡረተኞች የሚከፈል ገንዘብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ጀርመን በምርት ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያተረፈችውን ስም ይዛ እንድትቀል ማስቻል ነው።
የጀርመን መንግሥት የሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ሁቤርቱስ ኃይል ፣ጀርመን በቅርቡ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል በጣም ዘመናዊ ያሉት የፍልሰት ሕግ እንደምታወጣ ተናግረዋል።
«በዚህ ላይ እየሰራን ነው። ዘመናዊውን የፍልሰት ሕግ፣ መንግሥትና የሀገሪቱ ፓርላማ በዚህ ዓመት ያጸድቁታል።ይህን የምናደርገው የጀርመንን የሰራተኛ ኃይል አስተማማኝ ከማድረግ በተጨማሪ ወደፊት በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ልዩ ክህሎት ያላቸው ባለሞያዎች ፍልሰት ስለሚያስፈልገንም ነው።እናም ሕጉን እናሻሽላለን።»
ይሁንና ጀርመን በተለይም ከፍተኛ ክህሎት ያላቸውን የውጭ ዜጎች ለማስገባት ሕጎችን ብታወጣም መስፈርቶቹ የሂደቱ ውስብስብነትና አዝጋሚነት ብዙዎችን ሊስብ አልቻለም። ሚኒስትር ኃይል በዚህ ረገደ  ችግሮች መኖራቸውን አምነው የትምህርት ማስረጃዎች እውቅና አሰጣጥ ፣ የቪዛ መጓተትና የመሳሰሉት ከተስተካከሉ ሁሉም ወገን ተጠቃሚ ይሆናል የሚል ተስፋ ሰጥተዋል።
«እርግጥ ነው የተበላሸ ቢሮክራሲ ነው ያለን።አሁን ጥያቄው ለውጭ ዜጎች የትምህርት ማስረጃዎች እውቅና እንዴት እንሰጣለን የሚለው ነው? ቁልፉ ጉዳይ በምን ያህል ፍጥነት ቪዛ እንሰጣቸዋለን ነው? ጀርመን ዘመናዊ ፍልሰት የሚካሄድባት ስለሆነች እነዚህን በጣም ጥሩ በሆነ መንገድ ካደራጀናቸው በሦስት አቅጣጫ የምናተርፍበት ነው የሚሆነው፤የሰራተኞቹ መነሻ የሆኑ ሀገራት ለኛ ሰራተኞቹ ለሚፈልሱበት ሀገር እንዲሁም ወደኛ ለሚፈልሱት ሰራተኞች ሦስታችንም ተጠቃሚ የምሆንበት ነው።»
በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ለሰለጠኑ የሶስተኛ አገር ዜጎች ባለሞያዎች የሚሰጠው ብሉ ካርድ ወይም ሰማያዊ ካርድ ሙያቸው ተፈላጊ የሆነ የውጭ ዜጎች በቀላሉ ጀርመን መስራት የሚያስችላቸው አማራጭ ነው። ተሻሽሎ የሚወጣው የፍልሰት ሕግ አምዶች አንዱ ይኽው ብሉ ካርድ እንደሚሆን ተጠቁሟል። በተለይ ከፍተኛ የሰራተኛ እጥረት ባለባቸው ሞያዎች ለመስራት የሚያመለክቱ የውጭ ሰራተኞች  ብሉ ካርድ ለማግኘት የመጀመሪያ ዲግሪ ማስረጃ እና በዓመት የሚያኙት ደሞዝ ቢያንስ ከ56ሺህ ዩሮ በላይ መሆኑን ማረጋገጫ ማቅረብ አለባቸው። ከዚህ ውጭ አሁን በሚሰራበት ሕግ በህክምና በምህንድስና በተፈጥሮ ሳይንስ  በሂሳብና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስኮች ጀርመን ስራ ያገኙ የውጭ ዜጎች ደሞዝ ደግሞ ከ43 ሺህ 992 ዩሮ በላይ ሊሆን ይገባል ።ይሁንና ተሻሽሎ ይወጣል በተባለው ሕግ ግን ዝቅተኛው የደሞዝ መጠን  ይቀንሳል ተብሏል። ሌላኛው የሕጉ ማሻሻያ አምድ ደግሞ የስራ ልምድ ነው።የስራ ውል  ያገኙ አመልካቾች ፣ በሚሰማሩበት የስራ ዘርፍ ቢያንስ የሁለት ዓመት ልምድ ማቅረብ ከቻሉ የሙያ ማስረጃቸው አስቀድሞ እውቅና ባይሰጠውም ወደ ጀርመን መምጣት የሚችሉበት እድል ይኖራቸዋል። ከዚህ ሌላ ተሻሽሎ የሚወጣው ሕግ ፣ጀርመን ውስጥ በሚፈለጉ ሞያዎች ትምህርታቸውን የጨረሱ ሆኖም ጀርመን ላልተቀበለቻቸው ስደተኞችም እድል እንደሚሰጥ ነው ዶክተር ፀጋዬ ያስረዱት።  
አፍሪቃ ያሏት ጥቂት በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሞያዎች ጀርመንን ወደ መሳሰሉ ሀገራት የመፍለሳቸው ጉዳይ ቀድሞም አሁንም አነጋጋሪ ነው።በቂ ደሞዝ የተመቻቸ የስራ ሁኔታና አንዳንዴም ስራ በማይገኝባቸው ሀገራት ምሁራና መሰደዳቸውን ትክክል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ከአፍሪቃ የተማረ ሰው ፍልሰትን የሚያበረታቱ እርምጃዎችን የሚነቅፉ ብዙዎች ናቸው። የጀርመን የፍልሰት ሕግ ማሻሻያ በአንዳንድ የጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተተቸ ነው ።ህዝቡም የበኩሉን አስተያየት እየሰጠ ነው።  ማሻሻያው አያስፈልግም ከሚሉት አንስቶ ለሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ ይሰጥ ያሉም አሉ። 
ያም ተባለ ይህ በዚህ ዓመት ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ዘመናዊው የጀርመን የፍልሰት ሕግ ሞያቸው ጀርመን ውስጥ በጣም ተፈላጊ ለሆነ የውጭ ዜጎች ከከዚህ ቀደሙ ቀላል እና ሂደቱንም የሚያፋጥን ይሆናል ተብሎ ይገመታል።   

Symbolbild Blue Card für Europa
ከአሜሪካኑ ግሪን ካርድ ጋር ይመሳሰላል የሚባለው የአውሮጳው ብሉ ካርድ ምስል chromorange
Symbolfoto BAMF
የፌደራል ጀርመን የፍልሰት እና የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤትምስል Christoph Hardt/Geisler-Fotopress/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ