1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርቅ፣ረሃብ እና የምግብ ዋስት እጦት በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ መጋቢት 18 2016

በኢትዮጵያ ያለው የድርቅ አዝማሚያ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ኮነ፣ በተለይ በሰሜን እና ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎች አስጊና ወደ ከፍተኛ ረሃብ ሊሸጋገር የሚችል የድርቅና ረሃብ አደጋ ማንዣበቡን አመልክተዋል

https://p.dw.com/p/4eC8G
ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ የዉኃ ጉዳዮች መማክርት ቦርድ አርማ
ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደጋገመዉ ድርቅና ረሐብ የከፋ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ጠቁመዋልምስል EWAC

ድርቅ፣ረሃብ እና የምግብ ዋስት እጦት በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተደጋጋሚ የሚደርሰዉ ድርቅና ረሐብ አስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት ሰሞኑን ባደረገዉ አዉደጥናት አመለከተ።ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉ የመማክርቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ኮነ ፍስሐ እንደገለጹት፣በተለይ በሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ከፍተኛ ረሐብ ሊሸጋገር የሚችል የድርቅና የምግብ እጥረት ተከስቷል።የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት በአብዛኛዉ የዉኃ ጉዳይ አጥኚዎችንና ባለሙያዎች የሚያስተናብር ነዉ።

በኢትዮጵያ ድርቅና ረሃብዘላቂ ፈተናዎች ሆነው ቆይተዋል።ይህም አካባቢዊና ዓለማ አቀፋ ስጋት ቀስቅሷል ሲሉ፣ የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት የቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ ይናገራሉ።" የተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ 24 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ገልጿል።"

የችግሩ ስፋት በዚህ ሁኔታ እያለ ነው እንግዲህ፣ የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት ይህን አውደጥናት ያካሄደው።መማክርቱ፣በዚህ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የውኃ ባለሙያዎችና ከውኃ ጋር  በተያያዘ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጥናት የሚያደርግ የባለሙያዎች ቡድን ነው።

 

የውኃ ጉዳዮችና የሃገር ብሄራዊ ደህንነት

 

አውደ ጥናቱ አሁን የተዘጋጀበትን ምክንያት በተመለከተ፣ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው፣ የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች መማክርት ምክትል ፕሬዚዳንትና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ኮነ ፍስሐ የሚከተለውን መልሰዋል።

ባሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሕዝብ ለረሐብ የተጋለጠዉ በሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ ነዉ
በድርቅ ክፉኛ በተጎዳዉ በትግራይ ክልል ሰዎች ለረሐብ መጋለጣቸዉን ነዋሪዎችና ባለስልጣናት በተደጋጋሚ እያስታወቁ ነዉምስል Million Hailesilassie/DW

"የውኃ ጉዳዮች ከአንድ አገር ብሄራዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ውኃ ደግሞ በቀጣይነት የአንድን ሀገር የምግብ ዋስትና ወይንም በምግብ ደረጃ አንድ ሃገር ሊኖር የሚገባውን ደህንነት ለማሟላት የምንጠቀም ነው።ስለዚህ ድርቅ፣ረሃብና የምግብ ደህንነት መጓደል አገራችን ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮች በመሆናቸው፣ ይህንን የአገር ደህንነት ወይም የምግብ ዋስትና አለመኖር እንለዋለን።በዚህ ዙርያ ላይ ጥናት ማድረግና ይህንን ነገር ምንድነው ችግሩ የሚለውን ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልጋል በሚል ነው።"

በኢትዮጵያ ያለው የድርቅ አዝማሚያ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ኮነ፣ በተለይ በሰሜን እና ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎች አስጊና ወደ ከፍተኛ ረሃብ ሊሸጋገር የሚችል የድርቅና ረሃብ አደጋ ማንዣበቡን አመልክተዋል።በበይነ መረብ በተካሄደው በዚሁ ዓውደ ጥናት ላይ ከኢትዮጵያ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢ የነበሩት ወይዘሮ ትዕግስት ካሳ፣ የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አሁን ያለውን ሁኔታ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል።

በትግራይና ዐማራ ያለው ሁኔታ

 

"ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ የትግራይ ሕዝብ የምግብ እጥረቱ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ያንን ያህል ሕዝብ ችግር ውስጥ እንደከተተው የሚያሳዩ ጥናቶች እየወጡ ነው።ትልቁ ችግር ተደርጎ መወሰድ ይችላል። ዐማራ ላይ አሁን አካባቢው ጦርነት ላይ በመሆኑ አካባቢው በተለያየ ቦታ ላይ ቀውሱን አባብሶታል። እንደአጠቃላይ ጥናቶቹን ስናያቸውም፣ እኔም በምሰራበት የተሰሩ ዳሰሳዎች  የሚያሳዩት፣ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ጋር ከረሃብ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ መግባቱን የሚያሳዩ ነገሮች አሉ።በተለይ ወደ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት ግን በግልጽ የተጎዱ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።"

 

የድርቅ ክትትልና አደጋ ቅነሳ

 

ከኔብራስካ ዩንቨርስቲ የድርቅ ክትትልና አደጋ ቅነሳ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት፣ ዶክተር ጸጋዬ ታደሰ በበኩላቸው፣የድርቅና ረሃብ አደጋ ከመከሰቱ በፊትምን መደረግ አለበት ለሚለው ካስቀመጧቸው የመፍትሄ ዐሳቦች መኻከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል። 

መማክርቱ በአብዛኛዉ የዉኃ ባለሙያ፣ ሙሕራንና አጥኚዎችን የሚያስተናብር ነዉ
የኢትዮጵያ የዉኃ ጉዳይ መማክር አርማ ምስል EWAC

"ቀድሞ መዘጋጀት ነው።ፖሊሲዎቹ አሉ እነዚያ ነገሮች በደንብ መተግበር  ግን አልተቻሉም። መሬት ካልወረዱ ምንድነው ጥቅማቸው? ችግር ሲኖር ወዲያው ማሳወቅና ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብም ቢሆን ከሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ሰዎች፣ መንግስትም ራሱ የሚችለውን ማድረግ አለበት።"

የተለያዩ የድርቅ አደጋ መከታተያ ዘዴዎችና የብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ አገልግሎት  የሚሰጣቸው መረጃዎች ሁሉ አስቀድሞ በትክክልና በተገቢ ሁኔታ መተግበር መቻል እንዳለባቸውም ዶክተር ጸጋዬ አመልክተዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ