1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ዴሊቨር አዲስ፤ገዢና ሻጭን የሚያገናኘው መተግበሪያ

ረቡዕ፣ ሰኔ 10 2012

በኢንተርኔት ግንኙነት የሚሰራው ይህ መተግበሪያ በተንቀሳቃሽ ስልክ በነፃ የሚጫን ነው።ያም ሆኖ የኢንተርኔትና የመብራት መቆራረጥ በከተማዋ የደንበኞችን አድራሻ በቀላሉ ለማግኜት መቸገር፣ለአገልግሎቱ ፈተናዎች ናቸው።ይህንን ችግር ለመፍታት ከደንበኞች ጋር የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ።

https://p.dw.com/p/3dvCG
Logo von Deliver Addis | Essen Lieferservice in Addias Abeba

ዴሊቨር አዲስ

     

ኢትዮጵያ ዉስጥ የኮቪድ-19 በሽታ  መሰራጨቱ ከተረጋገጠ ካለፈው ሚያዚያ  ወዲህ እንደ ብዙዎቹ መስኮች ሁሉ የሆቴሎችና ምግብ ቤቶች ገበያ  እየተቀዛቀዘ መሆኑ ይነገራል። «ዴሊቨር አዲስ» የተባለው የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ  በአዲስ አበባ ከተማ  ይህንን ችግር በመፍታት ረገድ እገዛ እያደረገ ነው ተብሏል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በዚህ መተግበሪያ ላይ ያተኩራል።አዘጋጇ ፀሐይ ጫኔ ነች።የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ ከጤና ችግርነቱ በተጨማሪ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያስከተለ ነው።ይህ ወረርሽኝ በሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ የፈጠረውን ጫና በመቀነስ ረገድም የሞባይል መተግበሪያዎች ሚናቸው ቀላል አይደለም።
በኢትዮጵያም የኮቪድ-19 በሽታ መግባቱ ከተረጋገጠ ካለፈው ሚያዚያ ወር ወዲህ የሰዎች ዕንቅስቃሴ ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶችን የመሳሰሉ በርካታ የንግድ ተቋማት ገበያቸው እየተቀዛቀዘ መሆኑ ይነገራል። 
ምግብ ከቤት ማብሰል የማይችሉና ገዝተው የሚመገቡ ሰዎችም እንደወትሮው ወደ ምግብ ቤቶች ጎራ ብለው ለመመገብ ኮቪድ-19 ጫና ማሳደሩ አልቀረም።
«ዴልቨር አዲስ» የተባለው የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ታዲያ በአዲስ አበባ ከተማ ይህንን ችግር በመፍታት ረገድ እገዛ እያደረገ ነው። 
ይህ መተግበሪያ ምግብ ቤቶች ተመጋቢው ያለበት ቦታ ድረስ ምግብ ማድረስ እንዲችሉ በማድረግ በርካታ ደንበኞችን በማገናኜት እንደ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ነው። የዴሊቨር አዲስ ረዳት የግብይት ክፍል ሀላፊ ወይዘሪት ሜሮን ስለሺ አጠቃቀሙን እንዲህ ታስረዳለች።
« ዴሊቨር አዲስ ምግብና ሌሎች ዕቃዎችን ለማዘዝ የሚያገለግል ነው።አንድ ደንበኛ መተግበሪያውን በመጫን በተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም በድረ-ገፅ ማዘዝ የሚቻልበት ነው።» ካለች በኋላ አሰራሩም «በመጀመሪያ አንድ ደንበኛ አካውንት በመክፈት ይኖርበታል ።ከዚያም ከምግብ ቤቶች ወይም ከገበያ መደብሮች ምግብ፣አበቦችን፣መጠጦችን ወይም ሌሎች ስጦታዎችን እዚያው መተግበሪያው ላይ በመምረጥና በኦን ላይን ማዘዝ ይችላል።» ብላለች።ከደንበኞች የሚጠበቀው የሚገኙበትን አድራሻና የክፍያ ሁኔታ ማሳወቅ ብቻ መሆኑንም ጠቅማለች።ይህ ከተሟላ የታዘዘው ነገር በአንድ ስዓት ውስጥ እንደሚደርስም ገልፃለች። 
በዚህ ሁኔታ መተግበሪያውን ከሚጠቀሙ ሰዎች መካከል አቶ ዮሴፍ ጌታቸው አንዱ ናቸው።ላለፉት ሁለት ዓመታት የ«ዴሊበር አዲስ» ደንበኛ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ዮሴፍ ፤ከሚሰሩበትና ከሚኖሩበት አካባቢ የምግብ ቤቶች ባለመኖራቸው ምግብ ለመግዛት ሩቅ ቦታ ለመሄድ ይገደዱ ነበር።በአሁኑ ወቅት ግን መተግበሪያው ይህንን ችግር እንዳቃለላቸው ይናገራሉ።
«እኔ የምሰራበት አካባቢ ምንም ምግብ ቤት የለም።ያለው በእግር ብዙ ርቀሽ ሄደሽ ስጋ ቤት ነው።አንደኛ ያንን በየቀኑ መብላት አይቻልም።»ስለዚህ በመተግበሪያው አማካኝነት ቢሮም ሆነ ቤታቸው ሆነው የተለያየ ነገር ማዘዝ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
«ዴሊቨር አዲስ» በጎርጎሪያኑ 2015 ዓ/ም ፈለግ ፀጋዬ በተባለ ወጣት የተሰራ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መተግበሪያ ሲሆን ከ4 ዓመታት በላይ በከተማዋ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።አሜሪካን ሀገር ተወልዶ ያደገው ይህ ወጣት ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሲመጣ ያጋጠመው ችግር

Deliver Addis | Essen Lieferservice in Addias Abeba: Gründer Feleg Tsegaye
ምስል Deliver Addis

ለፈጠራው መነሻ እንደሆነው ይናገራል። 
«ችግሩ እንዴት ምግብ ማብሰል እንዳለብኝ አላውቅም ነበር።ስለዚህ ለኔ ቀላሉ ነገር የምግብ አሰራር ከመማር ይልቅ ከምግብ ቤት ምግብ መግዛት ነበር።በወቅቱ በመኖሪያ አካባቢዬ አንድ ምግብ ቤት ነበር።ስለዚህ እዚያ ምግብ ቤት አንድ አይነት ነገር መብላት ሲሰለቸኝ አሁን ይህ መቀየር አለበት አልኩና ይህንን መተግበሪያ ሰራሁ።»
ይህ መተግበሪያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ የተዘጋጄ በመሆኑ ለአጠቃቀም ቀላል እንዲሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለማዘጋጀትና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች አልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የወደፊት ዕቅድ መኖሩንም የዴሊቨር አዲስ መስራችና ሀላፊ አቶ ፈለግ ፀጋዬ አጫዉቶናል። 
በኢንተርኔት ግንኙነት የሚሰራው ይህ መተግበሪያ በተንቀሳቃሽ ስልክ በነፃ የሚጫን ነው።ያም ሆኖ የኢንተርኔትና የመብራት መቆራረጥ በከተማዋ የደንበኞችን አድራሻ በቀላሉ ለማግኜት መቸገር፣ለአገልግሎቱ ፈተናዎች ናቸው።ይህንን ችግር ለመፍታት ከደንበኞች ጋር የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የኦን ላይን ገበያ ያልተለመደ በመሆኑም አገልግሎቱን ማስለመድም ሌላው ችግር ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን መተግበሪያው ጥቅሙ የበለጠ እየታወቀ የመጣ ሲሆን በተለይ ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ የተጠቃሚው ቁጥርና ፍላጎት ጨምሯል።እንደ ግብይት ሀላፊዋ፤በወረርሽኙ ሳቢያ ገበያ ለተቀዛቀዘባቸው ሆቴሎችና ምግብ ቤቶችም ጥሩ የገበያ ዕድል ተፈጥሯል።
«ለአብዛኛዎቹ «ሬስቶራንቶች» ይህ «ዴሊቨሪ ሲስተም» ጠቅሟቸዋል ብለን ነው የምናስበው።ከነሱ ካገኘነው «ፊድ ባክ» አንፃር።» በማለት ከገለፀች በኋላ ምክንያቱን ስታብራራ «ብዙ ደንበኛ የሚመጣበት ጊዜ አይደለምና» ብላለች።
በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ መተግበሪያው ከምግብ በተጨማሪ ቤት አብስሎ መመገብ ለሚፈልግ ሰው ሽንኩርት፣ቲማቲምና ሌሎች አስቤዛዎችን በአጋርነት አብረው ከሚሰሩ የገበያ መደብሮች ሸማቾች ቤት ድረስ የማቅረብ አገልግሎትም ጀምሯል።አቶ ዮሴፍ ይህ አገልግሎት በሁለት መንገድ ጠቃሚ ነው ይላሉ።
«አሁን እንደ ልብ በማይወጣበትና በሚያስፈራው ጊዜ ያ «ሰርቪስ» መምጣቱ አንደኛ ጊዜ ይቆጥባል ሁለተኛ ከአደጋው ራስን መጠበቅ ይቻላል»ዴሊቨር አዲስ ከ60 በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን እንደ ወይዘሪት ሜሮን እንዲህ አይነቶቹ የቴክኖሎጅ ውጤቶች የዕለት ተዕለት ህይወትን ከማቃለል ባሻገር ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ስለሚያግዝ፤ መንግስትም ይሁን የግል ድርጅቶች ለፈጠራ ባለሙያዎች ድጋፍ ሊሰጡ ያስፈልጋል። 
ፀሐይ ጫኔ 

ነጋሽ መሀመድ