1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደራሼ ከጥቃቱ በኋላ አልተረጋጋም

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2014

በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የታጠቁ የተባሉ ቡድኖች የክልሉን ልዩ ኃይል የቀጠና አዛዥ፣ የልዩ ወረዳውን ዋና አስተዳዳሪና በፌደራል ፀጥታ አባላት ላይ የግድያ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ አካባቢው የሥጋት ድባብ እንዳጠላበት ነው። በአካባቢው በተከሰተው አለመረጋጋት የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ ካቆሙ ሳምንት ማስቆጠራቸው ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/4Am1C
Karte Sodo Ethiopia ENG

መከላከያ ሰራዊት ፀጥታ ለማስፈን ተሰማርቷል

በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የታጠቁ የተባሉ ቡደኖች የክልሉን ልዩ ኃይል የቀጠና አዛዥ፣ የልዩ ወረዳውን ዋና አስተዳዳሪና በፌደራል ፀጥታ አባላት ላይ የግደያ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ አካባቢው አሁንም የሥጋት ድባብ እንዳጠላበት ይገኛል። በአካባቢው በተከሰተው አለመረጋጋት የተነሳ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ ካቆሙ ሳምንት ማስቆጠራቸውን የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ (DW)  ተናግረዋል። የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የልዩ ወረዳውን ሰላም ለመመለስ የአገር መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ተረክቦ ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ዐስታወቀዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በደራሼ ልዩ ወረዳ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የተከሰተው አለመረጋጋት ወደ ቦታው የተመለሰ አይመስልም። አለመረጋጋቱ የተፈጠረው በልዩ ወረዳው ሆልቴ በተባለ ቀበሌ የታገቱ የውጭ አገር ጎብኚዎችን ለማስለቀቅ በተንቀሳቀሰው የፀጥታ ኃይል ላይ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው። በጥቃቱ ከሁለቱም በኩል ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸው የሚናገሩት በልዩ ወረዳው የጊዶሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አንድ የዐይን እማኝ ከዚያ ወዲህ በወረዳው የሚገኙ የመንግሥት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደተዘጉ ይገኛል ብለዋል።

ዶቼ ቬሌ በልዩ ወረዳው የፀጥታ ሁኔታና በአገልግሎቶች መቋረጥ ዙሪያ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤትንም ሆነ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ኃላፊዎችን ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም። ይሁን እንጂ የክልሉ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዴ በልዩ ወረዳው የታጠቁ ኃይሎች በክልልና በፌዴራል የፀጥታ አካላት ላይ አደረሱ ያሉት ጥቃት በክልሉ ለሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያ ገልፀዋል። በቀጣይ የልዩ ወረዳውን ሰላም ለማረጋገጥ የአገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ተረክቦ ከክልሉ ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኃላፊው ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትንም በሕግ የመጠየቅ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

በደቡብ ክልል ቀደም ሲል «የሰገን ሕዝቦች ዞን» ተብሎ ይጠራ የነበረውና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ተዋቅሮ የነበረው መስተዳድር በአዋጅ ከፈረሰ ወዲህ አካባቢው ሰላም እንደራቀው ይገኛል። ከመዋቅሮቹ አንዱ በሆነው የደራሼ ልዩ ወረዳ ውስጥ በተነሳው በዞን መዋቅር የመደራጀት ጥያቄና ከአጎራባች ኮንሶ ዞን ጋር ያለው የወሰን አለመግባባት አሁን በልዩ ወረዳው ለሚታየው የሰላም እጦት ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ