1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልተሰማው የደንጣ ዱባሞ ማኅበረሰብ ደምፅ

ረቡዕ፣ መጋቢት 25 2016

አቶ አበበ እና መምህር ሰለሞን አሁን ላይ እየተባባሰ ይገኛል ያሉትን ጥቃት ለማስቆም ለአካባቢው አስተዳደር ፣ ለፌዴራሉ መንግሥትና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን / ኢሰመኮ/ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4eON6
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳድር ዋና ከተማ ሆሳዕና በከፊል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳድር ዋና ከተማ ሆሳዕና በከፊልምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ያልተሰማው የደንጣ ዱባሞ ማህበረሰብ ደምፅ

 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩት አበበ አዴሎ በሃድያ ዞን የሚገኘውህዳጣን የደንጣ ዱባሞ ማህበረሰብ አባልመሆናቸውን ይናገራሉ ፡፡ በዞኑ ሶሮ ፣ ምዕራብ ሶሮ እና ዱና ወረዳዎች ውስጥ ተሰባጥሮ የሚገኘው የደንጣ ማህበረሰብ የራሱ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤዎች እንዳሉት አቶ አበበ ያስረዳሉ ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚህ ማህበረሰብ ላይ እየደረሰ የሚገኘው የሰብአዊ መብት ጥቃት አሁን ላይ እየተባባሰ መምጣቱን  ነው ለዶቼ ቬለ  የገለጹት ፡፡

“ የደንጣ ማህበረሰብ እርሻ እንዳያርስ ፣ ንግድ እንዳይነግድ እየተደረገ ይገኛል “ ያሉት አቶ አበበ “ በገጠር እና በከተማ በሚገኙ የማህበረሰቡ አባላት ላይ እሥር እና ድብደባ  እየተፈጸመ ይገኛል ፡፡ ደብደባውን እየፈጸሙ የሚገኙት ከቤራ በሚል በኢመደበኛ የተደራጁ ወጣቶች ናቸው ፡፡ ከወጣቶቹ በተጨማሪ የወረዳው የፀጥታ አባላት 14 የማህበረሰቡን አባላት አሥሮ ይገኛል  ፡፡ ከታሰሩት ውስጥ በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ጥርሳቸው የወለቀ ይገኙበታል “ በማለት ተናግረዋል ፡፡

የተበተነው የልማት ማህበሩ ጉባዔ  

የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህርና ሌላው የደንጣ ማህበረሰብ አባል መሆናቸው የጠቀሱት ሰለሞን ሱሎሬ የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ከፌዴራል የበጎ አድርጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በተገኘ ፍቃድ የደንጣ ዱባሞ ልማት ማህበር መመሥረታቸውን ይናገራሉ ፡፡ ይሁንእንጂ ማህበሩ ጉባዔውን ለማካሄድ የጠራው ስብሰባ ከቤራ በሚል በሃድያ ብሄር ስም በኢመደበኛ በተደራጁ ወጣቶች እንዲበተን መደረጉን መምህር ሰለሞን ገልጸዋል ፡፡

የተደራጁት ወጣቶች ማህበሩ ጉባኤውን እንዳያካሄድ “ ደንጣ ዝም በል “ የሚል እየጨፈሩ በመረበሽ ጉባኤው እንዳይካሄድ ማድረጋቸውን  የጠቀሱት መምህር ሰለሞን “ ተወልደን ያደግንብት አካባቢ በመሆኑ እንደዚህ አይነት ጥቃት ይደርስብናል የሚል ግምት አልነበረንም “ ብለዋል፡፡

አቶ አበበ እና መምህር ሰለሞን አሁን ላይ እየተባባሰ ይገኛል ያሉትን ጥቃት ለማስቆም ለአካባቢው አስተዳደር ፣ ለፌዴራሉ መንግሥትና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን / ኢሰመኮ/ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ተናግረዋል ፡፡

“ የሽብር ተግባር  “

በማህበረሰቡ ላይ እየተፈጸመ ይገኛል በተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ዶቼ ቬለ በሃድያ ዞን የሶሮ ወረዳአስተዳደርን ጠይቋል ፡፡ በወረዳው በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥቃት እልተፈጸመም ያሉት የወረዳው  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ዶቶሬ ለጊዜው የቁጥር መረጃ ባይኖራቸውም በወረዳው የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ተደርሶባቸዋል ያሏቸው  ሰዎች መታሰራቸውን አረጋግጠዋል  ፡፡

የዳንጣ ማሕበረሰብ አባላት በብዛት ከሚኖሩባቸዉ አካባቢዎች አንዱ የሐድያ ዞን ነዉ
የቀድሞዋ የሐድያ ዞን ያሁንዋ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልላዊ መስተዳድር ዋና ከተማ የሆሳዕና አዉራ ጎዳና ምስል Hadeya zone communication affairs

ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩት በወረዳው በተለይም በጊምቢቾ ከተማ የሽብር ቡድንን በመምራታቸውና በመሳተፋቸው መሆኑን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው “ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉት በተጨማሪ ለጊዜው ከአካባቢው የተሰወሩ እንዳሉም ታውቋል ፡፡ የወረዳው የፀጥታ አባላት ያመለጡትን ለመያዝ ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡ ታሳሪዎቹ ምን በመፈጸማቸው ነው በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩት በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ “ ደምፅ አልባ መሳሪያ በመያዝ በከተማው ረብሻ በማሳነሳታቸው ነው “ ብለዋል ፡፡

የማህበረሰቡ አቤቱታ

ዶቼ ቬለ ከደንጣ ዱባሞ ማህበረሰብ አባላት እያቀረቡ በሚገኘው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልንም ሆነ የፌዴራል የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ በአንጻሩ የማህበረሰቡን አቤቱታ መቀበሉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን / ኢሰመኮ / በጉዳዩ ላይ መረጃ እና ማስረጃዎችን እያሰባሰበ እንደሚገኙ አስታውቋል ፡፡ “ ኮሚሽኑ አቤቱታውን ተቀብሎ እየመረመረ ይገኛል ” ያሉት በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ሃላፊ አቶ ኢማድ አብዱልፈታህ በቀጣይ የምርመራ ውጤቱ ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ የሚደረግ ይሆናል “ ብለዋል ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ሶሮ ፣ ምዕራብ ሶሮ ፣  ዱና እና በከምባታ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ውስጥ የሚኖረው የደንጣ ማህበረሰብ በ1996 ዓም የብሄር ዕውቅና ይሰጠኝ ሲል ለአገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመልከቶ ነበር ፡፡ ለዓመታት ጥያቄውን ሲመረምር የቆየው ፌዴሬሽኑ ዳንጣ በብሄር ሳይሆን በማህበረሰብ ደረጃ ዕውቅ እንዲኖረው ሲል በ2010 ዓም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ