1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችዓለም አቀፍ

አወዛጋቢው ወደ ዩክሬን የምድር ጦር የመላክ ሃሳብ

ረቡዕ፣ የካቲት 20 2016

በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ዕለት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ 20 የሚሆኑ የአውሮጳ ሃገራት መሪዎች ጋር የተወያዩት ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ በወታደር ኃይልም የማጠናከር ሃሳብ አቅርበዋል። ሆኖም ካልነጠፈው የጦር መሣሪያ ድጋፍ ጎን ለጎን ወደ ዩክሬን እግረኛ ጦር ስለመላክ በቀረበው ሃሳብ ተባባሪዎቹ ሃገራት አልተስማሙም።

https://p.dw.com/p/4cz6d
የፓሪሱ ዓለም አቀፍ ስብሰባ
ለዩክሬን ስለሚደረገው ድጋፍ ፓሪስ ላይ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባምስል Stephane Lemouton/abaca/picture alliance

«ኔቶ ወታደር የመላክ ዕቅድ የለኝም ብሏል»

ባልተቋጨው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የአውሮጳ ሃገራት ለኪየቭ በሚሰጡት ድጋፍ ላይ ምክክራቸው ቀጥሏል። በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ዕለት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ 20 የሚሆኑ የአውሮጳ ሃገራት መሪዎች ጋር የተወያዩት ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ በወታደር ኃይልም የማጠናከር ሃሳብ አቅርበዋል። በዚህ ፓሪስ ፈረንሳይ በተካሄደው ለዩክሬንየሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ላይ ባተኮረው ዓለም አቀፍ ስብሰባ የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስን ጨምሮ የአውሮጳ ሃገራት መሪዎች እና የመንግሥት ተወካዮች ተገኝተዋል። ሆኖም ካልነጠፈው የጦር መሣሪያ ድጋፍ ጎን ለጎን ወደ ዩክሬን እግረኛ ጦር ስለመላክ በቀረበው ሃሳብ ተባባሪዎቹ ሃገራት አልተስማሙም። በትናንትናው ዕለትም ጀርመን፣ ስፔን እና ፖላንድ በይፋ እግረኛ ጦር ወደ ዩክሬን እንደማይልኩ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያም እግረኛ ጦር የመላኩን ሃሳብ እንደማይስማሙበት ገልጸዋል።

የኔቶ አባል ሃገራት ሰንደቅ ዓላማዎች
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን አባል ሃገራት ሰንደቅ አላማዎች ምስል Teri Schultz/DW

ተጓዳኞቹ የሆኑት የአውሮጳ ሃገራትን አቋም ተከትሎም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ኔቶም እግረኛ ወታደሮችን ወደዩክሬን የመላክ ዕቅድ እንደሌለው ይፋ አድርጓል።  ኔቶ እና ተባባሪዎቹ ለዩክሬን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ወታደራዊ ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን ያመለከቱት የድርጅቱ ባለሥልጣን እግረኛ ተዋጊ ሠራዊት ግን ለመላክ አለመታቀዱን መናገራቸው ተዘግቧል። የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭም አውሮጳውያን በዚህ ጉዳይ ከመወሰናቸው አስቀድሞ አእምሯቸውን እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል። የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበው የፈረንሳይ እግረኛ ጦር ወደ ዩክሬን የመላክ ሃሳብ ዓለምን ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚጋብዝ እንዳይሆን ማስጠንቀቂያ እየቀረበበት ነው።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ