ዩክሬንና መካከለኛው ምስራቅ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ትኩረቶች
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 5 2017
ያውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ሰኞ በሉክሰምበርግ ባካሄዱት መደበኛ ስብሰባ አሁንም በዩክሬንና የመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታ ላይ በስፋት ተወያይተው አቋሞችን ውስደዋል ውሳኔዎችን አስተላለፈዋል። በህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ሚስትር ጆሴፍ ቦሪየል የተመራው ይህ ስብሰባ፤ በዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ስለወቅታዊው የጦርነቱ ሁኔታ መግለጫ የቀረበለት ሲሆን፤ ሚኒስትሮቹ ከብርታኒያው የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ሚስተር ዳቪድ ላሚይ ጋርም ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።
ሚኒስትሮቹ በዩክሬን እየደረሰ ስላለው ጥቃትና ሊቀጥል ስለሚገባው ድጋፍ
ሚኒስትሮቹ ሩሲያ በዩክሬን ላይ በተለይ በሀይልና የወደብ መሰረተ ልማቶች ላይ እያደረሰች ባለው ጥቃት ላይ በሰፊው ተወያይተው ለዩክሬን የሚሰጠው ሁለንተናዊ ድጋፍና እርዳታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተስማሙ መሆኑ ተገልጿል። የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊና የሰበባው መሪ ሚስተር ጆሴፍ ቦርየል ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫም፤ ሩሲያ በዩክሬን በሰላማዊ ሰዎች ላይ፤ በሀይልና ወደብ መሰረተ ልማቶች ላይ እያደረሰች ያለውን ውድመት በመጥቀስ፤ በምንም አይነት ቢሆን ይህ እንዲቀጥል ሊፈቀድ እንድማይገባው፤ “ ሚስተር ፑቲን የዓለምን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ እንዲጥሉ ወይንም ክረምቱን እንደ ጦር መሳሪያ እንዲጠቀሙ መፈቀድ የለበትምም” በማለት ሚኒስትሮቹ የህብረቱን የዩክሬንን ወታደራዊ እርዳታ ሚሽን ተልኮ ለሁለት አመታት ለማራዘም የተስማሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የሚኒስትሮቹ ውይይትና ውሳኔ
ሚኒስትሮቹ የመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታ እየተባባስ መሄዱ ያሳሰባቸው እንደሆነና በጥልቀት እንደተወያዩበትም ተገልጿል። ሚስተር ቦርየል በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት የመካከለኛው ምስራቅን ሁኔታ ሲገልጹ “ መካክለኛው ምስራቅ ወደ ሙሉ ጦርነት ለመግባት አፋፍ ላይ ነው። ተጨማሪ ውጥረት፣ ግድያ፤ ውድመት፤ ወታደራዊ ግጭት፤ ሁሉም እይተዩ ነው” በማለት በጋዛም፤ በሊባኖስም አሁኑኑ የተኩስ ማቆም ስምምነት መደረግ ይኖርበታል ብለዋል።
የእስራኤል ሌላ የቀይ መሰመር ጥሰት
እስራኤል በሊባኖስ በሚኘው የተተባበሩትመንግስታት የሰላም አስከባሪ ሀይል ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ሚኒስትሮቹ በሙሉ ድምጽ ያወገዙ መሆኑንን ያወሱት ሚስተር ቦርየል፤ የእስራኤል እርምጃ ሌላ የቀይ መስመር ጥሰት መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሊባኖስ ጉዳይ አሳስቢና ችላ ሊባል የማይገባው መሆኑን በማስገንዘብም፤ “ ሊባኖስም ቤይሩትም በቦምብ እየተደበደቡ ነው። ሁኔታው ሊባኖስን ሌላ ጋዛ እንዳያደርጋት ያሰጋልም” በማለት ሚኒስትሮቹ ይህንን ሁኔታ የተገንዘቡት መሆኑን አስታውቀዋል። በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ሁሉም በሊባኖስና፤ እስራኤል በኢራን ላይ ልትወስደው ስለትምትችለው እርምጃ እያሰበ፤ በጋዛ ያለውን ከፍተኛ ሰባዊ ቀውስና እረሀብ ችላ እንዳይለው ያሰጋል” በማለት ያውሮፓ ህብረት ግን ለፍልስጤም መርጃ ድርጅትና ለጋዛ የሚሰጠውን ሰባዊ እርዳታ እንዲቀጥል ሚኒስትሮቹ የወሰኑ መሆኑን ሚስተር ቦርየል አክለው አስታውቀዋል፡፤
የአውሮፓ ህብረትና ብርታኒያ ከብሬክዚት በኋላ
የውጭ ጉዳይ ሀላፊው፤ ብርታኒያ ህብረቱን ክለቀቀች ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ በስብሰባቸው ከተገኙት የብርታኒያ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ሚስተር ዳቪድ ላሚይ ጋር ውይይት መደረጉንና ሁለቱ ወገኖች በሚስማሙባቸው አጀንዳዎች ላይም በጋራ ለመስራት የተስማሙ መሆኑን አስታውቀዋል፤ “ በጋዛ የተኩስ ማቆም ጥያቄ አንድ አይነት አቋም ነው ያለን። በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ለማርገብና ሰላም ለማምጣት ብርታኒያና የአውሮፓ ህብረት የሁለት መንግስታት የመፍትሄ ሀሳብ ብቸኛው መውጫ መንገድ መሆኑን ያምናሉ” በማለት ብቸኛው አማራጭም ይህ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአፍርካ ቀንድ በተለይም በሶማሊያና ሱዳን ወቅታዊ ሁኒታዎች ላይ የሀሳብ ልውውጥ የተደረገ ስለመሆኑ ከመገለጹ በስተቀር፤ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ ስለተደረጉ ውይይቶችም ሆነ የተላለፉ ውሳኔዎች ግን ፤ ከስብሰባው በወጡ መግለጭዎችም ይሁን በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የተባለ ነገር የለም።
ገበያው ንጉሴ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ