1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአውሮጳ

የ2024 የተፈጥሮ ሳይንስ የኖቬል ተሸላሚዎች እና የምርምር ስራዎቻቸው

ረቡዕ፣ ጥቅምት 6 2017

በየዓመቱ የላቀ የምርምር ስራዎችን ላበረከቱ ሊቃውንት የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት፤ በዘንድርው ዓመትም በኬሚስትሪ፣ በፊዚክስ እና በህክምና ሳይንስ ዘርፎች ለሰባት ተመራማሪዎች ሽልማት ተሰጥቷል። ለዘመኑ ቴክኖሎጅ ለሰውሰራሽ አስተውሎት መንገድ የጠረገው የማሽን መመር ለመጀመሪያ ጊዜ በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ግኝት ሆኗል ።

https://p.dw.com/p/4lqzI
Wirtschaftsnobelpreis - Medaille
ምስል dpa

የ2024 የተፈጥሮ ሳይንስ የኖቬል ተሸላሚዎች እና የምርምር ስራዎቻቸው

በየዓመቱ የላቀ የምርምር ስራዎችን ላበረከቱ  ሊቃውንት  የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት፤ በዘንድርው ዓመትም በተፈጥሮ ሳይንስ ማለትም በኬሚስትሪ፣ በፊዚክስ እና በህክምና ሳይንስ ዘርፎች ለሰባት ተመራማሪዎች ሽልማት ተሰጥቷል።
ባለፈው ሳምንት  በጎርጎሪያኑ ጥቅምት 7፤ 2024 በተከናወነው የኖቤል ሽልማት የመጀመሪያው ተሸላሚ ዘርፍ  የህክምና ወይም የፊዚዮሎጅ ዘርፍ ነበር። እንደ ኖቤል ሽልማት ኮሚቴው  በዚህ ዘርፍ አሜሪካውያኑ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ጋሪ ሩቭካን እና ቪክቶር አምብሮስ በዘርፉ  የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል። የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎቹ ጋሪ ሩቭኩን እና ቪክቶር አምብሮስ ሽልማቱ የተሰጣቸው ፤በሰውነት ህዋሳት ውስጥ የዘረመል እንቅስቃሴን የሚቆጣጠሩ «ማይክሮ አር ኤን ኤ»/micro RiboNucleic Acid/  የተባሉ ሞለኪውሎችን በመተንተን  መሆኑን የኖቤል ጉባኤው ዋና ፀሀፊ ፕሮፌሰር ቶማስ ፐርልማን ገልፀዋል።
«በካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት የሚገኘው የኖቤል ጉባኤ የ2024 የኖቤል ሽልማትን በፊዚዮሎጂ ወይም በሕክምና ቪክቶር አምብሮስን እና ጋሪ ሩቭኩን በማይክሮ አር ኤን ኤ ግኝት እና በዘረመል ቁጥጥር ላይ ባለው ሚና በጋራ ለመሸለም ወስኗል።»

የኖቤል ኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ኦሌ ካምፔ ፤ግኝቱን «በዘረ መል ቁጥጥር ውስጥ አዲስ መስክ የከፈተ ትንሽ ሞለኪውል» ሲሉ ገልፀውታል። ከካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት አንድራስ ሲሞን፣ በበኩላቸው  ግኝቱ መሰረታዊ ነው ይላሉ።«ይህ መሠረታዊ ግኝት ነው፣ እና መሠረታዊ ግኝቶች ብዙውን ጊዜ እውቅና ለመስጠት ጊዜ ይወስዳሉ፣ እና በእውነቱ በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው። እናም በዚህ  አመት የዚህን ልዩ ግኝት አስፈላጊነት እውቅና ሰጥተናል።»ብለዋል።

 የማይክሮ አር ኤን ኤ ግኝት ለዘረመል ቁጥጥር 

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ተመሳሳይ ቅጂ ያላቸው የሰዎች ልዩ የዘረመል ኮድ  ወይም የሰዎች ዲኤንኤ/DNA/Deoxyribonucleic Acid/፤-በሰውነታችን ውስጥ ባሉ በእያንዳንዱ ህዋሳት  ኒውክሊየስ ውስጥ ይገኛል። የሁለቱ ሊቃውንት አዲሱ ግኝት እነዚህ የሰውነት ሕዋሳት ምን ማድረግ እንዳለበቸው መመሪያ ሰጭ  ሆኖ ያገለግላል።
«ካይኖሀብዳይትስ ኤለጋንስ» /Caenorhabdits elegans/ በተባለው የክብ ትል እድገት ላይ ባተኮረው ጥናታቸው፤ ሁለቱ የሳይንስ ሊቃውንት «ማይክሮ አር ኤን ኤ» የሚባሉትን እና በዘረመል ቁጥጥር ላይ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱትን ሞለኪውሎች ምድብ አግኝተዋል። እነዚህ ሞሎኪዩሎች  ህዋሳት/cells / መቼ እና እንዴት እንደሚላመዱ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ተገልጿል።

አሜሪካውያኑ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ጋሪ ሩቭካን እና ቪክቶር አምብሮስ
በህክምና ወይም በፊዚዮሎጅ ዘርፍ አሜሪካውያኑ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ጋሪ ሩቭካን እና ቪክቶር አምብሮስ የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል።ምስል Christine Olsson/AP/picture alliance

የዚህ ሞሎኪዩል መገኘትም በሥነ-ህይወት መሰረታዊ አሰራር ላይ ያነበረውን ግንዛቤ የለወጠ መሰረታዊ የሳይንስ ግንዛቤ ነው ተብሏል። የሊቃውንቱ ግኝት የሕዋስ ተግባራትን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል በማሳወቅም ፣ ለወደፊቱ እንደ ስኳር እና ካንሰር ያሉ በሽታዎችን ለማከም የሚያስችሉ መድኃኒቶችን ለማዘጋጀት ሊረዳ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
 «አር ኤን ኤ» ከዚህ ቀደም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት  ክትባት ለማዘጋጄት ጥቅም ላይ ላይ ውሏል። በወቅቱም ከ SARS-CoV-2 ተዋህሲ ትንንሽ የዘረመል ኮድ ላይ በመመስረት ተመሳሳይ ፕሮቲኖችን በማዘጋጄት በአንፃራዊነት ክትባቱ በፍጥነት ሊሰራ ችሏል። ይህ ክትባትም የሰው ልጅ በሽታ የመከላከል ስርዓት ለትክክለኛውን ተዋህሲ  ለመዋጋት ዝግጁ የሆኑ ፀረ እንግዳ አካላትን ለመፍጠር ረድቷል።
በኤም አር ኤንኤ  ቴክኖሎጂ ክትባትን በማዳበር በሰሩት ስራም ካታሊን ካሪኮ እና ድሩ ዌይስማን የተባሉ ተመራማሪዎች ባለፈው አመት በዘርፉ ሽልማት አግኝተዋል።
ያም ሆኖ ያለፈው ዓመት ሽልማት በቀጥታ ሕክምና ላይ ለተተገበረ የመከላከያ ክትባት ሥራ እውቅና ለመስጠት ሲሆን፤ የዚህ ዓመቱ ሽልማት ግን በይበልጥ ምርምር ላይ ያተኮረ ነው።

በፊዚክስ ዘርፍ የኖቬል ተሸላሚዎች እነማን ናቸው?

ባለፈው ሳምንት  በተካሄደው የኖቬል ሽልማት ፊዚክስ ሌላው የተፈጥሮ ሳይንስ  የሽልማት ዘርፍ ነበር።በዚህ ዘርፍ አሜሪካዊው ሳይንቲስት ጆን ሆፕፊልድ እና ብሪቲሽ-ካናዳዊ ጂኦፍሪ ሂንተን ያለፈው ማክሰኞ በጎርጎሪኑ ጥቅምት 8 ቀን 2024 ዓ/ም የኖቬል ተሸላሚ መሆናቸውን  ኮሚቴው ገልጿል።ሊቃውንቱ የኖቬል ሽልማቱን ያገኙትት ለሰው ሰራሽ አስተውሎት እድገት መንገድ በጠረገው የማሽን መማር ግኝቶች እና ፈጠራዎች መሆኑን የስዊድን የሮያል የሳይንስ አካዳሚ ዋና ጸሐፊ፡ሶት ሃንስ ኤሌግሬን ገልፀዋል።
«የሮያል የስዊድን የሳይንስ አካዳሚ ዛሬ ፤ ለጆን ሆፕፊልድ ከአሜሪካ ፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ እና ለጄፍሪ፣ሂንተን  ከካናዳ ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በሰው ሰራሽ ነርቭ አውታሮች፤ ማሽን እንዲማር ላደረጉት መሠረታዊ ግኝቶቻቸው እና ፈጠራዎቻቸው  የ2024 የፊዚክስ የኖቤል ሽልማትን ለመስጠት ወስኗል።»ብለዋል።

አሜሪካዊው ሳይንቲስት ጆን ሆፕፊልድ እና ብሪቲሽ-ካናዳዊ ጂኦፍሪ ሂንተን
በፊዚክስ የሽልማት ዘርፍ አሜሪካዊው ሳይንቲስት ጆን ሆፕፊልድ እና ብሪቲሽ-ካናዳዊ ጂኦፍሪ ሂንተን የ2024 የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል።ምስል Christine Olsson/TT News Agency via AP/picture alliance

ይህ ቴክኖሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ የኖቬል ሽልማትያስገኘ ሲሆን፤ሽልማቱን የሰጠው  የስዊድን የሮያል የሳይንስ አካዳሚ ሁለቱ ሊቃውንት “ፊዚክስን እንደ መሳሪያ  በመጠቀም ለማሽን መማር  መሰረት የሆኑ ዘዴዎችን በመፍጠር በሳይንስ፣ በምህንድስና እና በዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ አብዮት አምጥዋል። ብሏል።

በቶሮንቶ ዩንቨርስቲ ኢምሪተስ ፕሮፌሰር የሆኑት የ76 አመቱ ትውልደ እንግሊዛዊው ሂንተን ፤ የመረጃዎችን ይዘት ወዲያውኑ ለማግኘት እና በምስሎች ላይ የተወሰኑ አካላትን የመለየት ተግባርን የሚያከናውን ዘዴን ፈልስፈዋል።ለዚህም መነሻ የሆናቸው የሰው ልጆች አእምሮ መሆኑን ገልፀዋል።
የ2024 የፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚው ጂኦፍሪ ሂንተን ፣ ባለፈው ዓመት በአንድ የቴክኖሎጂ ኮንፈረንስ ላይ  እንደገለፁት ሰው ሰራሽ የነርብ መረብ ከእውነተኛው የሰውልጆች የነርብ መረብ ጋር ልዩነቱ ትንሽ ነው ። «እኛ ልክ እንደ ማሽን  ነን። እኛ ድንቅ ነን፣ በማይታመን ሁኔታ የተወሳሰበ ማሽንም ነን፣ ነገር ግን ትልቅ የነርቭ መረብ ነን ።ስለዚህ  የሰውሰራሽ ነርቭ መረብ እኛ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም።»

ምርምሩ ለሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ መንገድ ጠርጓል

በጎርጎሪያኑ 1980ዎቹ ፣ ጆን ሆፕፊልድ እና ጂኦፍሪ ሂንተን የመረጃዎችን ለመለየት ፊዚክስን በመጠቀም ለዛሬው የሰውሰራሽ አስተውሎት መድረክ መንገድ ጠርገዋል። የሊቃውንቱ ስራ አሁን ማሽኖች መማር እና ማስታወስን እንዲለማመዱ አስችሏል።ከዚህ ቀደም ግን የሰው ልጆች አእምሮ እነዚህን ተግባራት በማከናወን ብቸኛው ነበር።
 የፊዚክስ የኖቤል ኮሚቴ አባሉ ዴቪድ ሃቪላንድ በሽልማቱ ወቅት እንደገለፁት፤የነ ሂንተን ዘዴ በሰው ሰራሽ መንገድ ማሽኖችን ማሰልጠን ያስችላል።
« ሰው ሰራሽ የነርቭ ትስስርን ችግር መኖሩን ወይም እጢዎች እንዳሉ በሚታወቁባቸው  ምስሎች ላይ ማሰልጠን ይችላል። መጀመሪያ ትስስሩን ማስልጠን፤ ከዚያም በምስሎቹ ውስጥ ችግሩን ለማግኘት በጣም ፈጣን እና ቀልጣፋ ይሆናል። ወይም በፍጥነት ሊሰራ እና በምርመራ ወቅት  ሀኪሙ የበለጠ እርግጠኛ እንዲሆን ለመርዳት ይችላል።» ብለዋል።
የሕክምና ምስል ጥናት ሰውሰራሽ አስተውሎት  ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረበት አንድ ዘርፍ ብቻ ነው።ቴክኖሎጅው አሁን በተለያዩ መስኮች ቁልፍ ሚናዎችን ይጫወታል።

ያም ሆኖ ከአስደናቂ የሳይንሳዊ ግኝቶች እስከ ቀልጣፋ አስተዳዳር ድረስ የሚያገለግለው የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ፤የሰው ልጅ በራሱ ፈጠራ ተበልጦ ከውድድር ውጭ ሊሆን  ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩንም ተሸላሚው ጂኦፍሪ ሂንተን ገልፀዋል።
የሰውሰራሽ አስተውሎት አባት ተብለው የሚጠሩት ሂንተን፤ ቴክኖጂው ለወደፊቱ የሚያደርሳቸውን አደጋዎችን በበለጠ ነፃነት ለመናገርም ባለፈው አመት ይሰሩበት ከነበረው የጎግል ኩባንያ ስራ ለቀዋል።ይህም በበርካታ  መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።ቀደምት እንደመሆናቸው ስለ ቴክኖሎጂው አደጋ በቀላሉ ለማስገንዘብ ይችሉ ዘንድም ባለፈው ዓመት አዲስ የመረጃ ድር ከፍተዋል።

የሰው ሰራሽ አስተዉሎት ቴክኖሎጅ የወደፊት ስጋት

ሂንተን ከካሊፎርኒያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  «ከእኛ የበለጠ ብልህ መሆን ምን እንደሚመስል ምንም ልምድ የለንም።እንደ ጤና አጠባበቅ ባሉ ዘርፎች ቴክኖሎጂው በብዙ መልኩ ግን ድንቅ ይሆናል።ነገር ግን ስለሚከሰቱ በርካታ መጥፎ  ውጤቶች መጨነቅ አለብን። በተለይ የእነዚህ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ የመሆን ስጋት ።»ብለዋል።

ሂንተን ኮምፒውተሮች እሳቸውና ሌሎች ባለሙያዎች ከጠበቁት ፍጥነት ቀድመው ከሰዎች የበለጠ ብልህ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመገንዘብ፤ በ2023 ዓ/ም ጎግልን ቢለቁም በኩባንያው በኃላፊነት ስሜት መስራታቸውን ተናግረዋል።
ባደረጓቸው አንዳንድ ጥናቶች መጸጸታቸውን የገለፁት ሂንተን፤ ነገር ግን በወቅቱ በነበረው መረጃ ላይ እርምጃ እንደወሰዱ ከዚህ ቀደም ገልፀዋል።
በኖቤል ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም «በተመሳሳይ ሁኔታዎች እንደገና ተመሳሳይ ነገር አደርጋለሁ። ነገር ግን በመጨረሻ ከእኛ  የበለጠ ብልህ የሆኑ ስርዓቶች  ሊቆጣጠሩት  ስለሚችሉ በአጠቃላይ በሚያመጣው መዘዝ እጨነቃለሁ።»ብለዋል።

በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት የ91 አመቱ ሆፕፊልድ፤በበኩላቸው  በመረጃ ውስጥ ምስሎችን እና ሌሎች  ምስል ነክ ውሂቦችን ማከማቸት እና መልሶ መገንባት የሚያስችል አጋዥ ማህደረ ትውስታ ፈጠረዋል።
ሁለቱም ወላጆቻቸው የፊዚክስ ሊቃውንት የነበሩት ሆፕፊልድ፤ በፊዚክስ ዘርፍ የ2019 የቤንጃሚን ፍራንክሊን ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበሩ።በዚህ  ወቅት  እንደገለፁት ሳይንቲስት ወይም መሐንዲስ ከመሆን በቀር ሌላ ምንም ነገር አስበው አያውቁም።
ሆፕፊልድ የሰውሰራሽ አስተውሎት  እምቅ እና ገደብ የለሽ አቅም የሚረብሽ ነገር እንዳለው በመግለጽ የሂንተንን ስጋት ተጋርተዋል።
የፊዚክስ የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኤለን ሙንስ በበኩላቸው በማሽን መማር እና በሌሎች የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ላይ   ስጋቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።
«የማሽን መማር ትልቅ ጥቅም ቢኖረውም፤ ፈጣን እድገቱ የወደፊት እጣ ፈንታችን ላይ ስጋት ደቅኗል። ስለሆነም የሰው ልጆች በጋራ በመሆን ይህንን አዲስ ቴክኖሎጂ ደህንነቱ በተጠበቀ፣ በሥነ-ምግባር በታነፀ እና ለሰው ልጅ የላቀ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ የመጠቀም ሃላፊነት አለባቸው።»ብለዋል።
በፊዚክስ ዘርፍ ባለፈው ዓመት  ፒየር አጎስቲኒ፣ ፌሬንክ ክራውስዝ እና አን ኤል ሁሊየር ፤ በአተሞች ውስጥ የሚከሰቱ ለውጦችን በቅፅበት ለመመልከት የሚያስችል እና የበሽታ ምርመራ ስራን ሊያሻሽል የሚችል እጅግ አጫጭር የብርሃን ፍንጣቂዎችን በመፍጠር የኖቬል ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
ከኖቤል ሽልማቶች መካከል ትልቁን ቦታ በሚይይዘው የፊዚክስ ዘርፍ ፤ከዚህ ቀደም  ሽልማት ካገኙት መካከል እንደ አልበርት አንስታይን፣ ኒልስ ቦህር እና ኤንሪኮ ፈርሚ ያሉ ታዋቂ ሳይንቲስቶች ይገኙበታል።

በኬሚስትሪ ዘርፍ የዘንድሮ የኖቬል ተሸላሚዎች

ሌላው የኖቬል ሽልማት ከሚሰጥባቸው የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች አንዱ የኬሚስትሪ ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ ፤የኖቬል ኮሚቴው ዴቪድ ቤከር፣ ዴሚስ ሃሳቢስ እና ጆን ኤም ጃምፐርን በዘርፉ የ2024 የኖቤል ተሸላሚ አድርጎ መርጧል። 
የስዊድን የሮያል የሳይንስ አካዳሚ ዋና ጸሐፊ፡ሶት ሃንስ ኤሌግሬን እንደገለፁት፤ሶስቱ ሊቃውንት የተሸለሙት በፕሮቲኖች ላይ ባደረጉት ምርምር ነው።
«የሮያል የስዊድን የሳይንስ አካዳሚ ዛሬ በኬሚስትሪ የ2024 የኖቤል ሽልማትን ግማሹን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በኮምፒውቲሽናል ፕሮቲን ንድፍ ለዴቪድ ቤከር፣ ግማሹን ደግሞ፤ በብሪታንያ  ከጎግል ዲፕ ማይንድ ለዴሚስ ሃሳቢስ እና ለጆን ጃምፐር በፕሮቲን አወቃቀር ትንበያ ስራቸው በጋራ ለመስጠት ወስኗል።»ብለዋል።

ዴቪድ ቤከር፣ ዴሚስ ሃሳቢስ እና ጆን ኤም ጃምፐር የ2024 በኬሚስትሪ የኖቤል ተሸላሚዎች
በኬሚስትሪ ዘርፍ ፤የኖቬል ኮሚቴው ዴቪድ ቤከር፣ ዴሚስ ሃሳቢስ እና ጆን ኤም ጃምፐርን በዘርፉ የ2024 የኖቤል ተሸላሚ አድርጎ መርጧል። ምስል Christine Olsson/AP Photo/picture alliance

ይህ ምርምር  ህክምናን እና የአዳዲስ መድሃኒቶችን አሰራር በእጅጉ እንደሚቀይር ተስፋ ተጥሎበታል።
በሰዎች ህይወት እንዲሁም በምድር ላይ ባሉ ህይወት ባላቸው ፍጥረታት ሁሉ ፣ ፕሮቲኖች በመላው የህዋሳት ተግባር፣ እንቅስቃሴ እና መዋቅር ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።
በጣም ቀላል የሚባሉት  አሚኖ አሲዶች  እንኳ  በፕሮቲን የግንባታ ሰንሰለቶች የተሠሩ ናቸው።እነዚህ አሚኖ አሲዶች በሰውነት ውስጥ ውስብስብ በሆነ ባለ ሶስት አቅጣጫ መዋቅሮች የታጠፉ ናቸው።በዚህ ሁኔታ በሰው ልጆች አካል ውስጥ በሚገኙ ወደ 20,000 የሚጠጉ ፕሮቲኖች ፤ እያንዳንዳቸው በጣም የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ።ስለዚህ ፕሮቲን በሆነ መንገድ ስራው ከተሳሳተ  በሽታ እና የአካል ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም ነው ፕሮቲኖች እንዴት እንደሚዋቀሩ መተንበይ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በሕክምና ውስጥ ግብ ሆኖ የቆየው።

የዘንድሮ የኬሚስትሪ ሽልማት ግማሹ ለዴሚስ ሃሳቢስ እና ለጆን ጃምፐር የተሰጠው ይህንን ግብ «አልፋ ፎልድ» በተባለ የሰውሰራሽ  አስተውሎት ፕሮግራም ጋር በማስተሳሰራቸው ነው። የኬሚስትሪ የኖቤል ኮሚቴ አባል ፤ፐርኒላ ዊትቱንግ-ስታፍሼዴ፣ ይህ አወቃቀር እንደ ሌሎች መረጃዎች በጎግል ፍለጋ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። «አሁን  የአሚኖ አሲዶችን አወቃቀር ቅደም ተከተል መውሰድ ይችላሉ። በመርህ ደረጃ በጎግል ፍለጋ ያድርጉ። እናም የፕሮቲን አወቃቀር ይገኛል.»ብለዋል።

ፕሮቲኖችን  በመረዳት  አዳዲስ ፕሮቲኖችን መንደፍ

እንደ ተመራማሪዎቹ ወደ ተወሰኑ ፕሮቲኖች የሚያመሩ ሂደቶችን መረዳት ደግሞ ለተለዩ ተግባራት አዳዲስ ፕሮቲኖችን ለመንደፍ ያስችላል። ይህም.ለወደፊቱ በህክምና እና በሌሎች በርካታ መስኮች ላይ  ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል።ይህንን ልዩ እና  አዲስ ፕሮቲን ለመጀመሪያ ጊዜ የነደፉት የ2024 የኬሚስትሪ የኖቤል ተሸላሚው ዴቪድ ቤከር ናቸው። ተመራማሪው ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ብዙዎችን ፈጥረዋል።ቤከር እንደገለፁት ስራቸው ያተኮረው ችግር  መፍታት ላይ ነው። «ሥራው በጣም ያተኮረው ችግሮችን በመፍታት ላይ ነው። እና አዲስ ፕሮቲን ስንቀርጽ ሁልጊዜ ፤የትኛውን የሕክምና ችግር ወይም የትኛውን የአካባቢ ችግር ለመፍታት እየሞከርን ነው ብለን እናስባለን።.»ብለዋል።

ቤከር እነዚያን ችግሮች ለመፍታት ያደረጉት ጥረት አሁን በኬሚስትሪ የ2024 የኖቤል ሽልማት ግማሹን አስገኝቶላቸዋል።
በኬሚስትሪ ዘርፍ ባለፈው ዓመት የ2023 ዓ/ም የኖቤል ሽልማት ያገኙት  አሌክሲ ዬኪሞቭ፣ ሉዊስ ብራስ እና ሙንጊ ባዌንዲ የተባሉ ሶስት ሳይኒቲስቶች ሲሆኑ፤ ሽልማቱን ያገኙት በ«ኮሎይድል ኳንተም  ነጠብጣቦች ውህደት ላይ በሰሩት ግኝት ነው። 
ከጎርጎሪያኑ 1901 ዓ/ም ጀምሮ በስዊድናዊው አልፍሬድ ኖቬል ስም በየዓመቱ የሚዘጋጄው የኖቬል ሽልማት፤ ለአሸናፊዎቹ 11 ሚሊዮን የስዊድን  ክሮነር ወይም 1 ነጥብ 1 የአሜሪካን ዶላር በጋራ ወይም በተናጠል ይሰጣል።


ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

 

,