1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ማጣራቱ ተግዳሮት ገጥሞት ይሆን?

ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2016

ከዚሁ ጋር አያይዘው አስተያየታቸውን የሰጡን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ፤ “እኛ ሚያዚያ ውስጥ ባወጣነው ባለስድስት ነጥብ መግለጫችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሁን አጋጥሞኛል ያለውን ስጋትን ሚያጠናክር ነው

https://p.dw.com/p/4fqit
እዉቁ ፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ የተገደሉት ባለፈዉ ሚያዚያ መጀመሪያ መቂ ዉስጥ ነዉ
በጥይት ተደብድበዉ የተገደሉት የኦሮሞኖ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ ባለሥልጣን በቴ ኡርጌሳምስል Private

የፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ማጣራቱ ተግዳሮት ገጥሞት ይሆን?

 

ባለፈው ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ በትውልድ ቀዬያቸው መቂ ዉስጥ በጥይት ተደብደዉ የተገደሉትየኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)ከፍተኛ ባለሥልጣን  በቴ ኡርጌሳ ግድያን ለማጣራት የሚደረገዉ ምርመራ እንቅፋት ገጥሞታል እየተባለ ነዉ።የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሚያደርገውን ምርመራ እክል አጋጥሞታል በመባሉ የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች ስጋታቸውን ገልፀዋል።የተለያዩ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ደግሞ ምርመራዉ ፍትህን የሚያረጋግጥና ገለልተኛ ሊሆን ይገባዋል።የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሥለ ግድያዉ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ የሁሉንም ትብብር መጠየቁ ይታወሳል፡፡

 

የሰብዓዊ ድርጅቱ የምርመራ ሂደት መፈተን

 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግድያው ላይ እያደረገ ነው የተባለውን ገለልተኛ ምርመራ እክል ገጥሞታል የሚል መረጃ መውጣቱን ተከትሎ የፍትህ አሰጣጡ ላይ ስጋቶች በርክተዋል፡፡ከዚሁ ጋር አያይዘው አስተያየታቸውን የሰጡን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ፤ “እኛ ሚያዚያ ውስጥ ባወጣነው ባለስድስት ነጥብ መግለጫችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሁን አጋጥሞኛል ያለውን ስጋትን ሚያጠናክር ነው፡፡ በወቅቱ በቴ ስያዝ የነበሩትን ሁኔታዎች ባብራራንበት መግለጫችን በወቅቱ በስፍራው የነበሩና እንደ ማስረጃ ልጠቅሙ ሚችሉ ነገሮች መሰወራቸውን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን አቶ በቴ ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው ሳይቀበር መረጃ እንደማሰባሰባቸው አሁንም ያላቸውን መረጃ ለህዝብ ይፋ ያደርጋሉ ብለን ነው የምንጠብቀው” ብለዋል፡፡

የምርመራው ሂደት ለዴሞክራሲ ያለው አንድምታ

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በፊናቸው ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአቶ በቴ ግድያ ላይ የሚደርገው ምርመራ እክል ገጥሞታል የሚል መረጃ መውጣቱ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚፈትን ብለውታል፡፡ “ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ የዜጎች መብት በተሻለ ሁኔታ እንዲከበር የተፈጠረ ቡድን እንደመሆኑ እንቅስቀሴው እነዲገደብ መደረግ አልነበረበትም፡፡ ይህ ደግሞ አሳሳቢ ጉዳይ የሚሆነው የህግ የበላይነቱን ማነው በዋናነት የሚበላሸው የሚለውን ስጋት ያጭራል፡፡ ይህ ደግሞ ገለልተኛ ሆነው ስራቸውን የሚሰሩ ተቋማት በዚያው መሰረት ስራቸውን እንዳይሰሩ ከዚያ የመሸሽ ሁኔታን ነው የሚያሳየው” ብለዋል፡፡

የበቲ ኡርጌሳ ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ኦነግ ግፊት እያደረገ ነዉ
የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር ዳዉድ ኢብሳምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአቶ በቴ መገደልን ተከትሎ በማግስቱ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ የግድያው ሁኔታ በገለለልተኝነት እስኪጣራ ድረስ በግምት ወደ አንድ አካል የሚጠቁሙ ውንጀላዎች መቆም እንዳለባቸው አሳስቦ፤ ሙሉና ገለልተኛ የምርመራ ውጤት በጸጥታ ተቋማት እንደሚደረጉ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ በዚያውም በግድያውም የተጠረጠሩት 13 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መጀመሩም ተነግሮ ነበር፡፡ የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ይህን አስመልክቶም በሰጡት አስተያየት፤ “ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ከተባሉት ውስጥ የአቶ በቴ ታናሽ ወንድም እና አንድ የአጎታቸው ልጅ እንደሚገኙ ከቤተሰብ ከማረጋገጣችን ውጪ እነማን እንደሆኑና ለፍርድ መቅረባቸውን ምንም መረጃ የለንም” ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ ቀጣይ ውጥን

ዶይቼ ቬለ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያ ላይ እያደረገ ያለው የምርመራ ሂደት እክል ገጥሞታል የሚል መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ጥያቄ ያቀረበላቸው አንድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍተኛ አመራር አሁን ምርመራው ስላልተጠናቀቀ ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየት እንደማይሰጡ ገልጸው “ኢሰመኮ መረጃ የሚያሰባስብበት የተለለያዩ ስልቶች ስላሉት ያንኑን ይከተላል” ብለዋል፡፡

ይህ መረጃ መሰማቱን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲው በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ግድያ እያደረገ ያለውን ገለልተኛ ምርመራ እክል ልገጥመው አይገባም በማለት አቋሙንና ስጋቱን መግለጹ ይተወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ