የፀረ-ቦኮ ሐራም ዘመቻና ጥፋቱ | አፍሪቃ | DW | 24.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የፀረ-ቦኮ ሐራም ዘመቻና ጥፋቱ

ትንሺቱ መስጊድ በቅጽበት ወደ ደም፤አስከሬን፤ወደ አካል ቁርጥራጭ፤ ወደ ፍርስራሽ-ክሳይ ክምርነት ተለወጠች።እና የተራፊዎች ጩኸት-ዋይታ፤ ጫጫታ አረበባት።«ቦኮ ሐራምን አጠፋሁ» ይል-ይሆናል አብራሪዉ።የመንግሥት ባለሥልጣናትን ግን «የኛ ጦር አላደረገዉም» ነዉ-ያሉት።ብቻ በቅፅበት የ36 ሰላማዊ ሰዎች አስከሬን ተለቀመ።

የናይጄሪያዉ ፕሬዝዳንንት ጉድላክ ጆናተን ሰሜናዊ ናይጄሪያን ከአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቦኮ ሐራም «እንደሚያፀዱ» ቃል ገብተዋል።የፕሬዝዳንቱን ቃል ገቢር ለማድረግ የዘመተዉ ጦር በመቶ የሚቆጠሩ የቦኮ ሐራም ተዋጊዎችን መግደል፤በሺ የሚቆጠሩ መማመረኩን አስታዉቋል።የተገደሉና የተማረኩት በሙሉ አሸባሪዎች መሆን-አለመሆናቸዉ ግን ግልፅ አይደለም።ግልፅ የሆነዉ ቦኮ ሐራምን በጥፋቱ ዘመቻ ሰላማዊ ሰዎችም መገደል፤ መቁሰላቸዉ ነዉ።

አባዳም።ኒጂዠርን ከናጄሪያ ጋር የምታዋስን ትንሽ የድንበር ከተማ ናት።የዛሬ-ሳምንት የዛሬን ዕለት አንድ የመንደሪቱ አዛዉንት ይሞታሉ።መንድረተኛዉ የሟቹን አስከሬን ይዞ-ከመንደሪቱ መስጊድ ይታደማል-ለስግደት (ለሶላተል ጀናዛ)-ነዉ ትክክለኛ ስሙ።በስግደቱ መሐል የትንሺቱ መንደር ትንሽ መስጊድ በትልቅ ፍንዳታ ተፈረካከሰች።ቦምብ ነዉ።የናይጄሪያ የጦር ጄት የጣለዉ ቦምብ።

ትንሺቱ መስጊድ በቅጽበት ወደ ደም፤አስከሬን፤ወደ አካል ቁርጥራጭ፤ ወደ ፍርስራሽ-ክሳይ ክምርነት ተለወጠች።እና የተራፊዎች ጩኸት-ዋይታ፤ ጫጫታ አረበባት።«ቦኮ ሐራምን አጠፋሁ» ይል-ይሆናል አብራሪዉ።የመንግሥት ባለሥልጣናትን ግን «የኛ ጦር አላደረገዉም» ነዉ-ያሉት።ብቻ በቅፅበት የ36 ሰላማዊ ሰዎች አስከሬን ተለቀመ።

ሲስላክ የተሰኘዉ የሰብአዊ መብት ተማጓች ድርጅት ባልደረባ ኮላ ባኖዎ እንደሚሉት የአባዳምዉ አይነት ጥፋት ያንዴ-የሁለቴ አጋጣሚ አይደለም።-የሁሌም እንጂ።

«በየዜና እዉጃዉ አምስት መቶ፤ ሰወስት መቶ ሰዉ ተገደለ ሲባል እንሰማለን።ሟቾቹ እነማን እንደሆኑ ግን ማንም አይነግረንም።በተለይ በገጠር መንደሮች እነዚሕ (የቦኮ ሐራም) ሰዎች በሠላማዊዉ ሕዝብ መሐል ተሠግስገዉ ይኖራሉ።በየመንደርተኛዉ ቤት ይሸሸጋሉ፤ አንዳንዴ ሰላማዊ ሰዎች የተጠለሉበት የአካባቢ መስተዳድሮች ቅጥር ግቢን ይይዛሉ።ሠላማዊዉ ነዋሪ ማምለጫ ሥፍራ የለዉም።እነዚሕ አካባቢዎች በመንግሥት ሕይል ሲመቱ ሰላማዊዉ ሰዉም ይገደላል።»

በፕሬዝዳናንት ጆናታን ጠቅላይ አዛዥነት ቦኮ ሐራምን «የየመመንጠሩ» ዘመቻ «ተፋፍሞ» ቀጥሏል።ከናጄሪያ በተጨማሪ የቻድ፤የኒዠር እና የካሜሩን ወታደሮች በከፈቱት «መብረቃዊ» ጥቃት ድል በድል እየተረማመዱ መሆናቸዉን የየጦሩ አዛዦች ከየጦር ግንባሩ ይዘግባሉ።ካሜሪኖች ሰማንያ ስድስት የቦኮ ሐራም ሸማቂዎችን ገደልን ሲሉ፤ ቻዶች 117 ይላሉ።ናጄሪያዎች ሰዎስት መቶ።ምርኮዉም ብዙ ነዉ።የኒዠር ጦር መቶ ስልሳ ማረኩ ይላል።የካሜሩን ከሺሕ በላይ።

የናይጄሪያና የተባባሪዎቿ ሐገራት ጦር የሚያንዠቀዝቀዉን የድል ዜና በነፃ ወገኖች ማረጋገጥ አይቻልም።ለወትሮዉ ጥቃት በሚፈፀምበት አካባቢ የዓይን ምስክሮችን የማነጋገር ዕድል የነበረዉ የሠብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሁዩማን ራይትስ ዋች አንኳ አሁን ሥለ ጉዳዩ ምንም አይነት መረጃ የለዉም።የድርጅቱ አጥኚ ማዉሲ ሴጉ እንደሚሉት በዘመቻዉ በሠላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ግፍ መፈፀሙን መገመት ግን አይገድም።

«ሰሜን-ምሥራቅ ናጄሪያ ዉስጥ ወታደራዊ ዘመቻዉ እንደቀጠለ ነዉ።ዘመቻዉ ግልፅ ባለመሆነ በጣም አሳሳቢ ነዉ።አካባቢዉን የሚያስሰዉ የቻድ ጦር የሠብአዊ መብት ረገጣ ይፈፅማል ከሚል ወቀሳ የፀዳ አይደለም።እርግጥ ነዉ የናጄሪያ ጦር በሠላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ግፍ እንደሚፈፅም ከዚሕ ቀደም ከነበረዉ ታሪኩ በግልፅ ይታወቃል።የቻድ ጦርም ቢሆን ሰብአዊ መብትን በተመለከተ በጣም አጠያያቂ ታሪክ ነዉ ያለዉ።»

ከወደ ካሜሩንም ሥለ ሠብአዊ መብት ጥሩ ዜና የለም።ሬድሐክ የተሰኘዉ የሠብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዳጋለጠዉ የካሜሩን ጦር ሥለ ቦኮ ሐራም መረጃ አገኛለሁ በሚል በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን አንዲት አነስተኛ ክፍል ዉስጥ «አሽጎ» ሲደበድብ ነበር።ጦሩ ሰላማዊ ሰዎቹን አግቷል በተባለበት አካባቢ ሐምሳ ሰዎች በጅምላ የተቀበሩበት ሥፍራ ተገኝቷል።የካሜሩን ጦር ቃል አቀባይ ወቀሳዉን አልተቀበሉትም።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic