1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨቅላ ሕጻናት ሞት መንስኤ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2016

ምርምሩ የሚካሄደው ከሞቱ ህፃናት አስክሬን ላይ ናሙናዎችን በመውሰድ እንደሆነ የሚገልጹት በሀረርጌ የጤና ምርምር ተመራማሪ እና የፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ሀሌሉያ ልዑልሰገድ እስከ አሁን ስድስት ሺህ ከሚሆኑት ላይ ናሙናዎችን ወስዶ በላብራቶሪ የመመርመር እና ውጤት የመተንተን ስራ መስራቱን ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4jgYe
በሀረርጌ የጤና ምርምር ተመራማሪ እና የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሀሌሉያ ልዑልሰገድ
በሀረርጌ የጤና ምርምር ተመራማሪ እና የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሀሌሉያ ልዑልሰገድምስል Messay Teklu/DW

የሕጻናት ሞት መንስኤዎች ምንድናቸው?

ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ  በሀገሪቱ የህፃናት ሞት ምክንያት ላይ ምርምር ማካሄድ ላይ ያተኮረውን የህፃናት ጤናና የጨቅላ ሕጻናት ሞት መንስኤን በተመለከተ በእንግሊዝኛ ምፅፃሩ CHMPS የተባለውን ምርምር ሲያከናውን ቆይቷል።

ከፍተኛ የህፃናት ሞት ምጣኔ ባለባት ኢትዮጵያ መተግበር የጀመረው ይህ ምርምር ለህፃናቱ በጨቅላ እድሜ መቀጨት መንስኤዎችን ከመለየት ባለፈ ለመፍትሄ የሚረዱ በዘመናዊ የምርምር ሂደት የተዘጋጁ መረጃዎችን በማውጣት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ ተገልፃል።

የህፃናት ጤናና የጨቅላ ሕጻናት ሞት ምክንያት ላይ ምርምር

 ምርምሩ የሚካሄደው በተለያየ ምክንያት ከሞቱ ህፃናት አስክሬን ላይ ናሙናዎችን በመውሰድ እንደሆነ የሚገልጹት በሀረርጌ የጤና ምርምር ተመራማሪ እና የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሀሌሉያ ልዑልሰገድ እስከ አሁን ስድስት ሺህ ከሚሆኑት ላይ ናሙናዎችን ወስዶ በላብራቶሪ የመመርመር እና ውጤት የመተንተን ስራ መስራት መቻሉን ተናግረዋል ።

 ዶ/ር ሀሌሉያ ልዑልሰገድ የቻምፕስ ምርምር ኢትዮጵያን ጨምሮ ከፍተኛ የሆነየህፃናት ሞት ምጣኔ ባለባቸው ሰባት ሀገራት እንደሚተገብር ጠቅሰው በእነዚህ ሀገራት የህፃናቱን ሞት ምክንያት የሚገልፅ በቂ መረጃ የለም ብለዋል። " በነዚህ ሰባት ሀገራት ላይ ያለው የመረጃ ሁኔታ በቂ የላብራቶሪ እና የሰው ኃይል ካለመኖሩ አንፃር ህፃናት ለምንድነው የሚሞቱት የሚለው በደንብ አልተጠናም ፤ አልተተነተነም"

ቻምፕስ የተሰኘው ጥናት የዘመነ የምርመራ ሁኔታ ማምጣቱን የሚገልፁት ዶ/ር ሀሌሉያ የማህብረሰቡን እሴት በጠበቀ መልኩ  ከሞቱ ህፃናት አስክሬን የተለያዩ ናሙናዎችን በመውሰድ በሀገሪቱ ካሉ ዘመናዊ ላብራቶሪዎች አንዱ በሆነው ማዕከል እንደሚተነተን አስረድተዋል። 

የጥናቱ ሂደት በራሱ ከባድ ነው የሚሉት ተመራማሪው ትብብር የሚያደርጉ ብዙ ወላጆች መኖራቸውን እና እስከ አሁን ስድስት ሺህ ያህል ከሚሆኑ ህፃናት የተለያዩ ናሙናዎች በመውሰድ ትንተና ማካሄድ መቻሉን ገልፀዋል።.

በሀረርጌ የጤና ምርምር ተመራማሪ እና የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሀሌሉያ ልዑልሰገድ
በሀረርጌ የጤና ምርምር ተመራማሪ እና የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሀሌሉያ ልዑልሰገድምስል Privat

ልጆች ከሞቱ በኃላ በ24 ሰዓት ውስጥ ነው ቤየሰብ ጋር ቀርበን አስረድተናቸው ፍቃዳቸውን ተጠይቆ ፣ እያንዳንዱ የምንሰራው ነገር ተነግሯቸው ፈርመው ነው ወደ ጥናቱ የምንሄደው ። ልጅ ለሞተበት ቤተሰብ ይሄ 24 ሰዓት ከባድ ቢሆንም በሚገርም ሁኔታ ብዙ ወላጆች ደስተኛ ሆነው ወደ ጥናቱ ይገባሉ"

የምርምሩ ግኝቶች

ጥናቱ ተፀንሰው ከሰባት ወራት በላይ ያስቆጠሩ ነገር ግን ሞተው የሚወለዱት እንዲሁም እስከ አምስት አመት እድሜ ባለ ጊዜ የሚሞቱ ህፃናትን እንደሚያካትት የሚያስረዱት ዶ/ር ሀሌሉያ ተፀንሰው ከሰባት ወር በላይ ባሉት ጊዜያት በሙቱት ላይ በተካሄደ የእስካሁኑ ጥናት የተለዩ ያሏቸውን የሞት ምክንያቶች አስተድተዋል።

ተመራማሪው ከተወለዱ ቀን አንስቶ እስከ አንድ ወር ባለው ጌዜ በሚሞቱ ህፃናት ላይ በተካሄደው ምርምር ተገኙ ያሏቸውን የሞት ምክንያቶችን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ከአንድ ወር ጀምሮ እስከ አምስት አመት ባለው እድሜ በሚካተቱ ህፃናት ላይ ለሚያጋጥመው ሞት ምርምሩ የለያቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረዋል።

በህፃናቱ ሞት ምክንያት ላይ አተኩሮ በዘመናዊ መንገድ በሚካሄደው ምርምር የሚገኙ ጥሬ መረጃዎችን እና የተተነተኑ ውጤቶችን የአለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በኢትዮጵያም ከጤና ሚንስትር ጀምሮ በየደረጃው ላሉ ተቋማት እንደሚያጋሩ ዶ/ር ሀሌሉያ ጠቁመዋል።

በህፃናቱ ላይ የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ ኃላፊነት አለባቸው ያሏቸው የህክምና ተቋማት አስፈላጊው ዝግጅት ሊኖራቸው እንደሚገባም ዶክተር ሀሌሉያ አስገንዝበዋል።

መሰል ምርምሮችን ማካሄድ ሰፊ ልፋትና ትልቅ ሀብት እንደሚጠይቅ የሚናገሩት ዶ/ር ሀሌሉያ መንግስትም እነዚህን በምርምር የሚገኙ ውጤቶች እንደ ሀብት ወስዶ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

በሀረርጌ የጤና ምርምር እየተተገበረ የሚገኘው ይህ ጥናት በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች እና በጤናው ዘርፍ የሚገኙ የተለያዩ ምሁራን የሚሳተፉበት ትልቅ ጥናት መሆኑም ተገልጧል ።

"ጥራቱን የጠበቀ ላብራቶሪ ማቋቋምን  እና ዘመኑን የሚመጥኑ ዓይነት ምርምሮችን የማካሄድ አላማን ይዞ ወደ ስራ የገባ ፕሮጀክት ነው።" ተመራማሪው
"ጥራቱን የጠበቀ ላብራቶሪ ማቋቋምን  እና ዘመኑን የሚመጥኑ ዓይነት ምርምሮችን የማካሄድ አላማን ይዞ ወደ ስራ የገባ ፕሮጀክት ነው።" ተመራማሪውምስል Messay Teklu/DW


ሀረርጌ የጤና ምርምር እና ቻምፕስ

ሀረርጌ የጤና ምርምር በእንግሊዝኛ ምዕፃሩ HHR በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እና ለንደን ስኩል ኦፍ ሀይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜድስን መካከል በምስራቅ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የምርምር ስራን ማበልፀግ ፣ ጥራቱን የጠበቀ ላብራቶሪ ማቋቋምን  እና ዘመኑን የሚመጥኑ ዓይነት ምርምሮችን የማካሄድ አላማን ይዞ ወደ ስራ የገባ ፕሮጀክት ነው።

በህፃናት ጤናና ሞት መከላከል ክትትል ወይም ቻምፕስ- የሁለቱ ተቋማት ትብብር ወደ ስራ ሲገባ ከተገበረው ፕሮግራም ቀዳሚው ነው። የምርምር ስራው በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የሚገኙትን ቀርሳ እና ሀረማያ እንዲሁም ሀረርን ባካተቱ ሶስት ሳይቶች ከሚኖረው ማህበረሰብ ጥናቱ እንደሚካሄድ ተገልጿል ።

በሀረርጌ የጤና ምርምር የፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ሀሌሉያ ለጥናት የተመረጠው ሳይት በነዋሪው ቁጥር ብዛት እንዲሁም የገጠር እና የከተማውን ነዋሪ ያካተተ በመሆኑ የአገሪቱን ሁኔታ የሚወክል እንደሆን አስረድተዋል። 
መሳይ ተክሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር