የጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ህገ-ወጥ ንግድ | ባህል | DW | 30.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ህገ-ወጥ ንግድ

የአሸባሪ ቡድን ድርጅቶች በመካከለኛዉ ምሥራቅ የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በመዝረፍና በከፍተኛ ገንዘብ በማግኘት ላይ መሆናቸዉ ተመልክቶአል። ይህን ጥንታዊ ቅርስ ከሚገዙት ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርስ አድናቂዎች እና ሰብሳቢዎች መካከል ደግሞ ጀርመናዉያንም እንደሚገኙበት ተመልክቶአል።

ይህ የተዘረፈ እቃ መሸጡና አሸባሪዎች እንዲጠቀሙበት የሆነበት ዋና ምክንያት ደግሞ በቅርስ ዝዉዉር ላይ ያለዉ ልል የሆነዉ የዓለም ዓቀፉ ህግ ነዉ፤ ሲሉ ምሁራን ያላቸዉን አስተያየት ይሰጣሉ። የዕለቱ ዝግጅታችን በመካከለኛዉ ምሥራቅ የእርስ በርስ ጦርነት በሚታይባቸዉ ሃገራት እየተሰረቀ ስለሚወጣዉ ጥንታዊና ታሪካ ቅርስ ዘገባ ይዞአል

በመካከለኛዉ ምሥራቅ በሚገኙ ሃገራት የሚንቀሳቀሰዉና እራሱን እስላማዊ መንግሥት ሲል የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን በአካባቢዉ ላይ የሚዘርፋቸዉን ጥንታዊ ቅርሶች በመሸጥ ትልቅ የገንዘብ ምንጭ ማግኘቱ ተመልክቶአል። ይህን ቅርስ ከሚገዙት የምዕራባዉያ ሀገራት የጥንት ታሪካዊ ቁሳቁስ ሰብሳቢዎች መካከል ጀርመናዉያንም የገኙበታል።
ልዩና ዉብ በመሆንዋ የምትታወቀዉ የሶርያዋ ፓልማይራ ከተማ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት በ« UNESCO» መዝገብ ዉስጥ የተካተተች ታሪካዊ ቦታ ናት። በቱሪስት መስብዕነትዋ ትታወቅ እና እንደ ኮከብ ታበራ የነበረችዉ ይህች ከተማ ታድያ «እራሱን እስላማዊ መንግሥት» እያለ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ዛሬ በእጁ ከአስገባት በኋላ በጨለማ ተዉጣለች።
አሸባሪ ቡድኑ በሶርያ እና በኢራቅ እድሜ ጠገብ ከተሞችን ከተቆጣጠረ በኋላ ያለምንም ሃሳብና እዉቀት በከተማዋ በጥበቃ ሥር የነበሩ ጥንታዊ ቅርሶችን መዝረፍ ጀመረ ። ዘረፋዉን የሚያካሂዱት ደግሞ ቅርሱ ያለበትን ቦታ በማፈንዳትና እስከ 10 ሜትር ጥልቀት ዉስጥ የተቀመጠ ነገርን በቦልዶዘር ማለትም በመቆፈርያ መኪና ቆፍሮና ሰብሮ በመግባትም ጭምር ነዉ። ታድያ አሸባሪ ቡድኑ የጥንታዊ ሥልጣኔ ግዛትን ማለትም የ«ሜሶፖታምያ» በጃቸዉ መዉደቅ የገንዘብ ዋንኛ ምንጭ ሆኖላቸዋል። አሸባሪ ቡድኑ ሜሶፖታምያ ጥንታዊ የስልጣኔ ግዛት የሚገኙትን ጥንታዊ ታሪካዊና ቁሳቁሶች በመዝረፍ ወደ ዓለም አቀፉ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሳቅርሶች መገበያያ መድረክ በማቅረብ በርካታ ገንዘብን ያገኙበታል። በዚህ ገበያ ከሚቀርቡት ቅርሶች መካከል ደግሞ አነስተኛ እና ዉብ የሆኑ ጥንታዊ ቅርሳ ቅርጾች፤ የመጫወቻ እቃዎች ፤ ጌጣጌጦች ይገኙበታል። አሸባሪ ቡድኑ ጥንታዊ ቅርሳቅርሶች የሚገኙበትን ቦታ በፍንዳታ ሰብሮና ቆፍሮ ከገባ በኋላ ለማዉጣት ያልቻለዉን አልያም ገንዘብ አያስገኝም አይጠቅምም ያለዉን ጥንታዊ ታሪካዊ ቅርስ ሰብሮ ይሄዳል፤ አልያም ያለምንም ጥንቃቄ ለዝናብና ለፀሐይ አጋልጦት ይተወዋል።

ለምሳሌ ከሶርያ በብዙኃን መገናኛ ድረ-ገፅ የተለቀቀ ቪዲዮ በሶርያ አንድ ታሪካዊ እና ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶችን የያዘ ቦታ እንዴት ሲመዘበር እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ቪዲዮዉ ላይ የሚታዩት የተዘረፉት ታሪካዊ እቃዎች፤ ከጥቂት ግዝያት በኋላ ጀርመን ላይ በሽያጭ ሊገኙ ይችላሉ። ለምሳሌ በጀርመን ሙኒክ ቁሳቁስን በጨረታ ሽያጭ በሚያቀርበዉ መደብር ፤ በዝያ የጥንታዊ የቁሳቁስ መሸጫ መደብር ዉስጥ ለሽያች ከቀረቡት ቁሳቁሶቹ መካከል የሮማዉያን እና የግሪካዉያን እድሜ ጠገብ ቅርሶች ይገኛሉ። እንዲሁም ጦርነት ከሚታይባቸዉ ከሶርያ እና ከኢራቅ የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶችም ይገኑበታል። አብዛኞቹ ቁሳቁሶች ደግሞ ከግል ስብስቦች የተገኙ ይመስላሉ። ለምሳሌ በመደብሩ ለሽያጭ የቀረበ አንድ 5000 ዓመት እድሜ እንዳለዉ የተነገረለት የጦር ተሽከርካሪ ናሙና ከመካከለኛዉ ምስራቅ ሃገራት መገኘቱ ብቻ ነዉ የተጠቀሰዉ።የጥንታዊ ቁሳቁስ ጉዳይን የሚያዉቁት የከርሰ ምድር ጥናት ባለሞያ ጀርመናዊዉ ሚሻኤል ሙለር የዚህ ጥንታዊና ታሪካዊ እቃ መገኛ ቦታ እንዳይታይ ተደረጎ ጠፋቶአል ሲሉ አስረግጠዉ ይናገራሉ። ሚሻኤል ነገሩ ይሄ ብቻ አይደለም ይላሉ በመቀጠል፤
«የጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ግብይት የሥነ-ቅሪት ተመራማሪዎች መረጃን እና ቦታን እንዲሁም በዉስጣቸዉ የያዙትን ቅርሶች ከማዉደሙ ሌላ ለሽብርተኝነት የገንዘብ ምንጭ ነዉ። ስለዚህ እዚህ የቅርሳቅርስ ንግድ ጉዳይ የብዙ ሰዉ ደም እንሚፈስበት ልናዉቀዉ የሚገባ ዋና ጉዳይ ነዉ»
በመካከለኛዉ ምስራቅ እየተሰረቁ ያሉት ጥንታዊ ቅርሶች የሰዉን ልጅ ጥንታዊ ታሪክ እና እድገትን የሚያሳዩ መዝገቦች ናቸዉ። የኢራቁ ጦርነትና የሶርያዉ የርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ከአካባዉ ላይ እየወጣ ያለዉ ቅርሳ ቅርስ የትየለሌ ሆንዋል። ጦርነቱ ከሚታይበት ከመካከለኛዉ ምስራቅ ሃገራት በየዕለቱ በቱርክ በኩል አልያልም በሊባኖስ ወይም ደሞ በዱባይ የባህር ወደብ በኩል በዚህ ንግድ በተሰማሩ ሰዎች በኩል ወደ ሌሎች ሃገራት ይሻገራል። ከዝያም በነጋዴዎች ወደ አዉሮጳ እና ወደ ዩኤስ አሜሪካ መግባት የሚችልበትን ማረጋገጫ ወረቀት አዘጋጅተዉ ወደ የሀገራቱ ያጓጉዙታል።

በሙኒክ ጥንታዊ ቁሳቁስ በጨረታ ለሽያጭ አቅራቢ መደብር ስለሚያቀርባቸዉ ቁሳቁሶች ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቦአል። ጥሩ ትርፍ የሚገኝበት ንግድ ለእስላማዊዉ መንግሥት ቡድን ያለምንም ድካም የሚያገኘዉ መጠቀሚያ መሳርዉ ነዉ። ቡድኑ የጀመረዉን የአሸባሪነት ትግል ለመቀጠል የገንዘብ ህልዉናዉን መሰረት ለማስያዝ ዘረፋዉን ይቀጥላል። በሶርያ ታሪካዊ ቦታ ኢድሊብም የታየዉ ሁኔታ ይህን ያመለክታል። በጎረቤት ኢራቅም ይኸዉ አሸባሪ ቡድን የጀመረዉን ጦርነት በማስታከክ ከብዙ ቦታዎች ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሳቅርሶች ተዘርፈዋል። በኢራቅ ባግዳድ አንድ ወታደራዊ አዛዥ ይህኑ ነዉ የሚመሰክሩት
«የአሸባሪዉ ቡድን የ IS የገንዘብ ምንጭ የሆኑ አንድ ከ 2000 እስከ 3000 እድሜ ያለዉ ከኢራቅ የተገኘ ጥንታዊ ቅርስ ለሽያጭ አቅርቦአል። ለምሳሌ ከሞዙል የተሰረቁ እጅግ ረጅም እድሜ ያላቸዉ ጥንታዊ ቅርሶች በጣም በከፍተኛ ገንዘብ ነዉ የሚሸጡት። ይህ የሽያጭ ገንዘብ ደግሞ በርገጠኝነት የአሸባሪ ድርጅቶች ሥራ ላይ ያዉሉታል።»

እንደ ጀርመኑ ጋዜጣ «ሱድ ዶቼ ሳይቱንግ»ና ኖርድ «ዶችን ሩንድ ፉንክ» እንደ ተሰኘዉ የብዙሃን መገናኛ ዘገባ የተሰረቀ አልያም የህገ-ወጥ ቅርሳቅርስ ብይት በዓለማችን ከህገ-ወጥ መሳርያ ንግድና እጽ ንግድ ቀጥሎ በሶስተኛነት የተቀመጠ የተደራጁ ወንጀለኞች የሚፈፅሙት ተግባር ነዉ። እንደዘገባዉ አንዱና ትልቁ የጥንታዊ ቅርሳ ቅርስ መሸጫ ማዕከል ደግሞ በጀርመንዋ ባቫርያ ግዛት ሙኒክ ከተማ ላይ ይገኛል።
ከሙኒኩ የጥንታዊ ቅርሳ ቅርስ መገበያያ መደብር ሌላ በብራስል በለንደን ከዓለም ዙርያ የተዘረፉ ቅርሳ ቅርሶች ንግድ የሚካሄድበት ዋና ማዕከልም አለ። በሙኒኩም ሆነ በብራስል እንዲሁም በለንደን በሚገኘዉ ግዙፍ የጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች መሸጫ መደብር ዉስጥ ለሽያች የሚቀርቡት ቁሳቁሶች ላይ በርግጥ ከየት አካባቢ እንደተገኙ የሚያሳይ የትክክለኛ ቦታ ስም ቀን አልተመዘገበባቸዉም። በዚህም በሙኒክም ሆነ በብራስል እንዲሁም በለንደኑ መደብር የሚገበዩ የጥንታዊና ታሪካዊ ቁሳቁሶስ አፍቃሪዎችና ሰብሳቢዎች የተሰረቀ ህገ ወጥ ነገር እጃቸዉ ላይ ከመገኘቱ ባሻገር፤ በእጅ አዙር የእስላማዊዎቹን ፅንፈኞች በአሸባሪነት ተግባራቸዉ እየረዱ መሆኑ እሙን ነዉ።

የጀርመንዋ የባህል ሚኒስትር ሞኒካ ግሩተርስ በጎርጎረሳዊ 2007 ዓ,ም የፀደቀዉንና የተሰረቁ ታሪካዊ ቅርሳ ቅርሶችን በሚያስገቡ ግለሰቦች ለፍርድ የሚያቀርበዉ ህግን ይበልጥ የሚያጠናክር አንድ አዲስ ህግ እንደሚፀድቅ ተናግረዋል። ሚኒስትሯ ባለፈዉ ሳምንት ይህን ይፋ ሲያደርጉ ባደረጉበት ንግግር ጀርመን የህገ ወጥና የታሪካዊ ቅርሳቅርሶች የተመቻቸች መነገጃ ቦታ እንዳትሆንም አስጠንቅቀዋል። በሌላ በኩል በጀርመን የወንጀል መቆጣጠርያ ቢሮ ሰራተኛ የሆኑት ሲልቪ ካርፊልድ በበኩላቸዉ ጀርመን በህገ ወጥ መንገድ ከዓለም የተሰበሰቡ ቅርሳቅርሶች መሸጫ ቦታ ናት ባይ ናቸዉ። እንደ ካርፊልድ ጦርነት ካለባቸዉ አካባቢዎች የተሰረቁ ባህላዊና ጥንታዊ ቅርሳቅሶች ጀርመን ዉስጥ በተደጋጋሚ ይታያሉ። እዚህ በጀርመን ጥንታዊ ቅርሶቹን ከየትና እንዴት እንደመጡ ከመመዝገብ ይልቅ ህጉ የአንድ ዶሮ እንቁላል መቼ እና የት መጣሉን የሚያሳይ የተሻለ የአመዘጋገብ ስርዓት ይታያል። እና ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ሲሉ ይጠይቃሉ፤
«ነገሩ እንዲህ ነዉ፤ ብዙ ታሪክን ካዘለ እና ዉድ ከሆነ ቅርሳቅርስ አጠባበቅ ይልቅ በጀርመን አንድ የዶሮ እንቁላል ከተጣለበት ቀን አንስቶ የት እንደተጣለ ስንት ግዜ እንደሆነዉ እንዲሁም ያጠባበቁ ሁኔታና የአመዘጋገቡ ሁኔታ የተሻለ ነዉ። እናም ተዋናዮቹ በየሀገሩ እንደሚሆነዉ ሁሉ የሆነ ክፍት ቦታ ባገኙበት አጋጣሚ በመጠቀም ስራቸዉን ይቀጥላሉ»

በጎርጎረሳዊዉ 1970 ዓ,ም በዓለም ዙርያ የሚገኙትን ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ይበልጥ ለመጠበቅ እና ከለላ ለመስጠት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት በ« UNESCO» አንድ አዲስ ህግ ፀደቀ። ጀርመን ይህንን ህግ ለመፈፀም በፊርማ የተስማማችዉ ደግሞ በጎርጎረሳዊዉ 2007 ዓ,ም ነበር። እንደ ጀርመን የባህል ሚኒስትር እንደ ግሩተርስ ጀርመን ይህን ህግ ከፈረመች በኋላ ከሌላ ሀገር በህገ ወጥ የገቡ ታሪካዊና ጥንታዊ ቁሳቁሶችን ለመመለስ ያፀደቀችዉ ሕግ የላላ ነዉ። ይኸዉም ታሪካዊ ቁሳቁስ የጠፋባቸዉ ሀገሮች በቅድምያ እንዴት እና የእቃዉን አይነት አሳዉቀዉ ጀርመን የእቃዉን ምንነት በይፋዊ ሰንጠረዥ ዉስጥ አካታ በስምንት ዓመት ግዜ ዉስጥ ይህን ታሪካዊ ቅርስ በተመለከተ ሌላ ሀገር የኔ ነዉ ብሎ እስካ ልመጣ ድረስ ብቻ ነዉ ጠፍቶብኛል ላለዉ ሃገር ሊመለስለት የሚችለዉ። በሌላ በኩል የተሰረቁ ጥንታዊ ታሪካዊ ቅርስ ሊመለስ የሚችለዉ የኔ ነዉ ያለዉ ሀገር ከሀገሩ ለመገኘቱ የሚያሳምን በቂ መረጃን ማቅረብ አለበት። በዚህም በእዉነት ይህን ታሪካዊ ቅርስ በርግጥ የኔ ንብረት ነዉ ያለዉ ሀገር ንብረቱን መልሶ ያገኛል ብሎ ማመኑ ጉምን የማፈስ ያህል መሆኑን ጀርመን ማይንዝ በሚገኘዉ በሮማዉያን ማዕከል የጥንታዊ ቁሳቁስ ጉዳይንና የከርሰ ምድር ጥናት ባለሞያ ሚሻኤል ሙለር ካርፐ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

የቅርሳ ቅርስ ንግድ ግብይትን በተመለከተ የጀርመን መንግሥት አንድ የህግ ለዉጥ በማድረግ የአሸባሪዉን ቡድን የገንዘብ ምንጭን ማድረቅ ይፈልጋል። ይህ ለወጥ የታቀደዉ የህግ ረቂቅ የቀረበ ሲሆን በመጭ የጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ,ም በሥራ ላይ እንደሚዉል ይጠበቃል። የጀርመንዋ የባህል ሚኒስትር ሞኒካ ግሩተርስ የተሰረቁ ጥንታዊ ቅርሶችን በተመለከተ አንድ የተለየ የአሰራር ዘዴ እንዲቀየስ ያሳስባሉ። መስርያ ቤታቸዉ በጀርመን ገበያ ላይ የሚታይ ማንኛዉም ጥንታዊ ታሪካዊ ቁሳቁስ በሕጋዊ መንገድ ከአንድ ሀገር የመምጣቱን እንዴትነት የሚያሳይ ህጋዊ መረጃ እንዲኖር ይፈልጋል። የጥንታዊ ቅርስ ጥናት ባለሞያዉ ሚሻኤል ሙለር በበኩላቸዉ ይህ በቂ አይደለም ባይ ናቸዉ። እንደ ሚሻኤል ማንኛዉም የተሰረቀ ወይም መረጃ የሌለዉ ታሪካዊ ቅርስን የያዘ ግለሰብ በህግ መቀጣት የሚያስችልም ህግ መዉጣትም አለበት። እስካሁን የነበረዉ አሰራር ግለሰቡ የያዘዉ ጥንታዊ ቅርስ ህጋዊነትን የሚያሳይ ማስረጃ ነበር የሚያቀርበዉ። መሆን ያለበት ግን የዛን ታሪካዊ ቁስ ህጋዊ አለመሆን የመንግስት ጉምሩክ መስርያ ቤት በማስረጃ ማቅረብ አለበት ባይ ናቸዉ።


እንደ ጀርመንዋ የባህል ሚኒስትር ግሩተርስ በህገ ወጥ መንገድ ጀርመን የገቡ ታሪካዊ ቅርሶችን ለየሀገራቱ ለመመለስ የሚያስችልበት ህግ እስካሁን ከባድ ችግርን ደቅኖአል። በጎርጎረሳዊዉ 2016 ዓ,ም ተግባራዊ የሚሆነዉ አዲስ ህግ ይህን ችግር ይቀርፋል የሚል እምነት አለ። ግን እስከዝያ በጀርመን የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ ቁሳቁስን የሚሰበስቡ ሰዎች ፖለቲከኞች ላይ ተፅእኖ አሳድረዉ ህጉ ተገቢራዊ እንዳይሆን ሙከራ እንዳያደርጉ ስጋት ደቅኖአል። ጀርመናዊዉ የጥንታዊ ቁሳቁስ ጉዳይንና የከርሰ ምድር ጥናት ባለሞያ ሚሻኤል ሙለር በበኩላቸዉ የጀርመን ፊደራል መንግሥት ጥንታዊና ታሪካዊ ቁሳቁስን የሚሰበስቡ ሰዎች ሊያስድሩ የሚችሉትን ተፅኖ ተቋቁሞ ህጋዊ ያልሆኑ አልያም የተሰረቁ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ወየሀገራቱ ለመመለስ ለማስመለስ በጎርጎረሳዊዉ 2007 ዓ,ም ከወጣዉ ህግ የተሻለ ህግ ይፀድቃል የሚል ተስፋ እንዳላቸዉ ገልፀዋል።

በመካከለኛዉ ምሥራቅ ሀገራት የሚታየዉን ዉጥረትና የርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ በመዉደም እና በመዝበር ላይ ያሉትን ጥንታዊ የሰዉ ልጅ ታሪክ ማህደሮች በተመለከተ ሰሞኑን የዶቼ ቬለ ጣብያ በተለያዩ ቋንቋዎች ሽፋን የሰጠበትን ርዕስ በለቱ የባህል ቅንብራችን ተከታተልን። ስለ ባህል ዝግጅታችን ያላችሁን አስተያየት አልያም ዘገባ እንድንሰራበት የምትጠቁሙን ባህላዊ ርዕስ ካላችሁ በደስታ እንቀበላለን። ዘገባዉን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን መከታተል ይቻላል።


ጄሲካ ፊሊፕ / አዜብታደሰ

ተክሌየኋላ

Audios and videos on the topic