1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽዋልኢድ ዓመታዊ በዓል በጥንታዊቷ ሐረር ከተማ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 10 2016

ለጥንታዊቷ ሀረር ከተማ ከወራት በፊት በዓለም አቀፉ የሳይንስ ፣ የትምህርት እና የባህል ድርጅት በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ/ UNESCO ሁለተኛ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የሽዋልኢድ ዓመታዊ በዓል የከተማይቱን የቱሪስት መዳረሻነት እድል ይበልጥ ያሰፋል የሚል እምነት አሳድሯል።

https://p.dw.com/p/4ewU8
የጥንታዊቷ ሐረር ከተማ መለያ ግንብ
የጥንታዊቷ ሐረር ከተማ መለያ ግንብምስል Mesay Teklu/DW

የሽዋልኢድ በዓል የከተማይቱን የቱሪስት መዳረሻነት ያሰፋል ተብሏል

ለጥንታዊቷ ሀረር ከተማ ከወራት በፊት በዓለም አቀፉ የሳይንስ ፣ የትምህርት እና የባህል ድርጅት በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ/ UNESCO ሁለተኛ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የሽዋልኢድ ዓመታዊ በዓል የከተማይቱን የቱሪስት መዳረሻነት እድል ይበልጥ ያሰፋል የሚል እምነት አሳድሯል። የማይዳሰስ ቅርስ በመባል በዓለም አቀፉ ተቋም የተመዘገበው ይኸው በዓል ዕውቅና ባገኘ ማግስት የመጀመርያ በሆነው ፌስቲቫል በሀረር ትናንት ተከብሯል። ። ሀረሪዎች ዘመን ለተሻገረ ባህላዊ ሀብታቸው ላገኘው ዕውቅና ደስታቸውን ሲገልጡ የክልሉ መስተዳድር ከተማይቱን ምቹ የመኖሪያ እና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ኅብረተሰቡ እና ሌሎች የግል ተቋናት ጥሩ ስራ እየሰሩ ስለመሆናቸው ገልጿል ። 

በዘንድሮው ዓመት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ ፣ የትምህርት እና የባህል ድርጅት በእንግሊዝኛ ምዕፃሩ/ UNESCO በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውየሸዋልኢድ በዓል በሀረር  በሚከበርበት ወቅት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ይህን እድል መሰረት በማድረግ ከተማይቱን ምቹ የመኖሪያ እና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በህብረተሰቡ እና በግል ተቋማት ጥሩ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሸዋልኢድ በዓለም አቀፉ ተቋም እውቅና እንዲያገኝ ከክልሉ ጋር በመሆን ስራውን ሲሰራ የቆየው የፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር የቅርሱ መመዝገብ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ያስገኛል ያሏቸውን ጥቅሞች አብራርተዋል።

የሸዋልኢድ በዩኔስኮ የተመዘገበው  "በኃይማኖታዊ ይዘቱ ሳይሆን በባህላዊ ይዘቱ "መሆኑን በአፅንኦት የገለፁት የባህልና ስፖርት ሚንስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ባህሉን ጠብቀው ላቆዩ አካላት እውቅና በማግኘቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የሽዋልኢድ ዓመታዊ በዓል በከፊል
የሽዋልኢድ ዓመታዊ በዓል በከፊልምስል Mesay Teklu/DW

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚንስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የቱሪዝም ፀጋን ታድላለች ባሏት ጥንታዊቷ ሀረር ከቱሪዝም ሀብቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ሚንስቴሩ ከክልሉ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ሸዋልኢድ በተቀዳጀው አለም አቀፍ እውቅና ማግስት ዛሬ እየተከበረ ባለው የመጀመርያው በዓል ታዳሚዎች ደስታቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል።

ከትናንት ጀምሮ በከተማዋ እየተከበረ በሚገኘው በዓል የፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ሸዋል እድ በዩኔስኮ የተመዘገበበትን እውቅና  የሚገልጽ ሰርተፍኬት ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስረክቧል።

የሽዋልኢድ ዓመታዊ በዓል በከፊል በሐረር ከተማ ሲከበር
የሽዋልኢድ ዓመታዊ በዓል በከፊል በሐረር ከተማ ሲከበርምስል Mesay Teklu/DW

የሸዋልኢድን አስመልክቶ በጀጎል ግንብ የሚከናወነው ፌስቲቫል በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ታዳሚዎች በተገኙበት ትናንት ከአመሻሽ ጀምሮ ሲከበር ሌሎች የበዓሉ ኩነቶች በመካሄድ ላይ ናቸው።

በበዓሉ የፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተጎራባች ክልል እና ከተማ አስተዳደር የባህል ቡድን ተወካዮች እና ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት እየተከናወነ ይገኛል።

 ከኢድአልፈጥር በዓል መከበር በኃላ ባለው አንድ ሳምንት እለት  በሀረሪዎች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የሽዋልኢድ ከወራት ቀደም ሲል በዩኔስኮ ስለመመዝገቡ መዘገባችን ይታወሳል።