1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 2 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 2016

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት አሁን አሰልጣኝ ሜኬል አርቴታ፤ ዬርገን ክሎፕ እና ፔፕ ጓርዲዮላ ተፋጠዋል ። በመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች ውድድር የአስተናጋጇ ሀገር ጋና ጥቋቁር ልዕልታት ሊሲዎችን አሸንፈዋል ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ደጊቱ አዝመራው በዙርኪክ ማራቶን ድል ተቀዳጅታለች ። የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ እና ረቡዕ ይኖራል ።

https://p.dw.com/p/4dOoE
Manchester City v Liverpool
ምስል Martin Rickett/empics/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት አሁን አሰልጣኝ ሜኬል አርቴታ፤ ዬርገን ክሎፕ እና ፔፕ ጓርዲዮላ ተፋጠዋል ። በሳምንቱ መጨረሺያ ግጥሚያዎች፦ ድል የቀናው አርሰናል የደረጃ ሰንጠረዡ መሪነትን ተረክቧል ። በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ ሊቨርፑል 2ኛ እንዲሁም በአንድ ነጥብ ብቻ ልዩነት ማንቸስተር ሲቲ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  በአፍሪቃ ጨዋታዎች ውድድር የአስተናጋጇ ሀገር ጋና ጥቋቁር ልዕልታት የኢትዮጵያ አቻቸውን አሸንፈዋል ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ደጊቱ አዝመራው በማራቶን ድል ተቀዳጅታለች ። 

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ደጊቱ አዝመራው ስፔን ባርሴሎና ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው 45ኛው የዙሪክ ባርሴሎና ማራቶን አንደኛ በመውጣት ድል ተቀዳጅታለች ። 2:19:52 በመሮጥ ያሸነፈችው ደጊቱ ለጥቂት ስምንት ሰከንድ ብቻ በመዘግየቷ ክብረ ወሰን ሳትሰብር ቀርታለች ። የቦታው ክብረወሰን በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ዘይነብ ይመር ወርቁ የተያዘ ነው ። አትሌት ደጊቱን በመከተል የሀገሯ ልጆች ኢትዮጵያውያቱ ሹቆ ገነሞ (2:21:35) እና መሠረት ድንቄ (2:22:58) የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።

በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሰ አብርሃም 1ኛ በመውጣት ለድል በቅቷል ። ታደሰ ውድድሩን ያጠናቀቀው 2:05:01 በመሮጥ ነው ። ኬንያውያኑ ኮሊን ኪፕኪሩ (2:06:44) እና ኤድሞንድ ኪፕንጌቲች (2:07:21) ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኔ ተስፋዬ (2:10:19) አምስተኛ ደረጃ አግኝቷል ።

የአፍሪቃ ጨዋታዎች በጋና

የዘንድሮ የአፍሪቃ ጨዋታዎች አዘጋጅ ጋና ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴት እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን ኬፕ ኮስት ስታዲየም ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ማሸነፍ ችሏል ። በ13ኛው የአፍሪቃ ጨዋታዎች መክፈቻ ውድድር፦ የጋና ቡድን በተከላካይ እና ግብ ጠባቂ ያለመግባባት በተፈጠረ ስህተት የኢትዮጵያ ቡድንን 1 ለ0 አሸንፏል ። ምንም እንኳን 78ኛው ደቂቃ ላይ አቢባ ኢሳህ የተባለችው ተጨዋቹ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ብትሰናበትበትም የጋና ቡድን 84ኛ ደቂቃ ላይም የግብ ዕድል አምልጦታል ።  የካቲት 26 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ባለፈው ሳምንት ዐርብ የጀመረው እና የተለያዩ የስፖርት ዘርፎችን የሚያካትተው የአፍሪቃ ጨዋታዎች ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ሳምንት ይጠናቀቃል ። በሁለት ሳምንት ፉክክሮቹ ከእግር ኳስም ባሻገር፤ የእጅ ኳስ፤ ነጻ ትግል፤ ባድሜንተን፤ የውኃ ዋና፤ ጁዶ፤ ቴኳንዶ፤ ብስክሌት፤ የሜዳ ቴኒስ በመሳሰሉ በ23 የስፖርት ዘርፎች ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።

አትሌት ኂሩት መሸሻ በቡዳፔስት የ1500 ሜትር ርቀት ፉክክር አሸናፊ በሆነችበት ወቅት ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደር
ኢትዮጵያ ብዙውን ጊዜ ስኬታማ የሆነችበት የአትሌቲክስ ፉክክር ከፊታችን ሰኞ እስከ ዐርብ ድረስ ይኖራል ። አትሌት ኂሩት መሸሻ በቡዳፔስት የ1500 ሜትር ርቀት ፉክክር አሸናፊ በሆነችበት ወቅት ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Chai v.d. Laage/IMAGO

እስካሁን 36 የወርቅን ጨምሮ 66 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ግብጽ በመሪነቱ ሰፍራለች ። ደቡብ አፍሪቃ በ9 ወርቅ በጥቅሉ 29 ሜዳሊያ ሁለተኛ እንዲሁም አልጄሪያ በ8 ወርቅ በድምሩ 40 ሜዳሊያ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ትናንት በነበሩ የብስክሌት ፉክክር ግጥሚያዎች በገብረ መድኅን መራዊ እና ከ23 ዓመት በታች በናሆም ዘርዓይ ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች ያገኘችው ኤርትራ እንደ ኬንያ እና ቦትስዋና 20ኛ ደረጃ ላይ ሰፍራለች ።

 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ  ቡድን 62 ወንዶች እና 75 ሴቶች በድምሩ 137 አትሌቶችን አካቷል ።  ኢትዮጵያ ብዙውን ጊዜ ስኬታማ የሆነችበት የአትሌቲክስ ፉክክር ከፊታችን ሰኞ እስከ ዐርብ ድረስ ይኖራል ። 89 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፉበታል ። በነዚያ ውድድሮች ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያዎችን ትጠብቃለች ። በብስክሌት 12 አትሌቶች፤ በውኃ ዋና 8፤ በጠረጴዛ ቴኒስ 10 አትሌቶች ኢትዮጵያን ይወክላሉ ።  በሴቶች የእግር ኳስ ቡድን 18 ተሳታፊዎችን ኢትዮጵያ አስመዝግባለች ።

ኢትዮጵያ የፊፋ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ወቅትን በመጠቀም ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ከሌሶቶ ቡድን ጋ ለማድረግ መስማማቷ ተዘግቧል ።  በዚህም መሰረት ከሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ጋ መጋቢት 12 እና መጋቢት 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ጨዋታዎች እንደሚኖሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል ።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ በበርካቶች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ሲጠበቅ የነበረው የሊቨርፑል እና የማንቸስተር ሲቲ ግጥሚያ ባለመሸናነፍ ተጠናቋል ። አንድ እኩል የተለያዩት  ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ በመጋራታቸውም ቅዳሜ ዕለት ብሬንትፎርድን 2 ለ1 ያሸነፈው አርሰናል ዳግም የመሪነቱን ቦታ ከሊቨርፑል ተረክቧል ።

የሊቨርፑሉ ኮሎምቢያዊ አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ
የሊቨርፑሉ ኮሎምቢያዊ አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ ብቃቱን በተደጋጋሚ ዐሳይቶ የማንቸስተር ሲቲ ተከላካዮችን ቢያስጨንቅም፤ ሊቨርፑል ግን እንደ ሳላኅ ያለ ጨራሽ አጥቂ ሳያስፈልገው አልቀረም ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Rui Vieira/AP/dpa/picture alliance

ዐሥር ጨዋታዎች እየቀሩ መሪው አርሰናል በደረጃ ሰንጠረዡ ከሊቨርፑል የበላይ የሆነው በግብ ልዩነት ብቻ ነው ። ያለፈው ባለድል ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ከሁለቱ የሚለየው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው ።  63 ነጥብ አለው ።  የካቲት 18 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በትናንቱ እልህ አስጨራሽ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ቀዳሚውን ግብ በ23ኛው ደቂቃ ላይ በጆን ስቶን ቢያስገባም በተለይ ከሁለተኛው አጋማሽ በኋላ ሊቨርፑል እጅግ አይሎ ነበር ። በተገኘው የፍጹም ቅጣት ምትም አሌክሲስ ማክ አሊስተር ሊቨርፑልን አቻ አድርጎ መላ አንፊልድን አስቦርቋል ። የማንቸስተር ሲቲው ደብረወይና ተቀይሮ በመውጣቱ እጅግ ሲበሳጭ አሰልጣኙም ሲያባብሉት ታይቷል ። የሊቨርፑሉ ኮሎምቢያዊ አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ ብቃቱን በተደጋጋሚ ዐሳይቶ የማንቸስተር ሲቲ ተከላካዮችን ቢያስጨንቅም፤ ሊቨርፑል ግን እንደ ሳላኅ ያለ ጨራሽ አጥቂ ሳያስፈልገው አልቀረም ። ተቀይሮ የገባው ሞሐመድ ሳላኅም ቢሆን ውጤቱን መቀየር ተስኖታል ። ጨዋታው ሲጠናቀቅ ያልተቀየረው ጨዋታው ሲጀመር ዕንደታየው ሁሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ እና አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ከልብ በመነጨ መንፈስ ሲተቃቀፉ መታየታቸው ነው ። ምናልባትም አሁን በሚመሩት ቡድኖቻቸው አሰልጣኝነት የትናንቱ የመጨረሺያ ግንኙነታቸው ሳይሆን አይቀርም ።

ዛሬ ማታ ቸልሲ ከኒውካስል ተስተካካይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ። ትናንት ብራይተን ኖቲንግሀም ፎረስትን 1 ለ0 አሸንፏል ። ዌስትሀም ከበርንሌይ ሁለት እኩል ተለያይቷል።  ቶንሀም በቀይ ካርድ አንድ ተጨዋቹ በገዛ ሜዳው የተሰናበት አስቶን ቪላን 4 ለ0 ድል አድርጓል ።

ሔሪ ኬን አሊaneትስ አሬና ስታዲየም ውስጥ ማይንትስ ላይ ሲያስቆጥር ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደር
የቡንደስሊጋ ግጥሚያ በከፊል ። የባዬርን ሙይንሽን አጥቂ ሔሪ ኬን አሊaneትስ አሬና ስታዲየም ውስጥ ማይንትስ ላይ ሲያስቆጥር ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Straubmeier/nordphoto GmbH/picture alliance

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሌቨርኩሰን ትናንት ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 አሸንፏል ። ቮልፍስቡርግ 28ኛው ደቂቃ ላይ ሞሪትስ ዬንትስ በቀይ ካርድ ተሰናብቶበታል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሆፈንሀይምን 3 ለ1 አሸንፏል ። ቦሁም በፍራይቡርግ የ2 ለ1 ሽንፈትን አስተናግዷል ። ከምንም በላይ ግን ሔሪ ኬን ሦስት ኳሶችን ከመረብ አሳርፎ ሔትትሪክ በሠራበት የቅዳሜው ግጥሚያ ባዬርን ሙይንሽን በግብ ተንበሽብሿል ። ተጋጣሚው ማይንትስ ላይ እየተመላለሰም 8 ለ1 ረምርሞታል ። ከትናንቱ ድል ያገኘውን ጨምሮ ባዬርን ሙይንሽን እስካሁን 57 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛነት ላይ ይገኛል ። ከመሪው ባዬርን ሌቨርኩሰን ግን በ10 ነጥብ ርቋል ። የካቲት 11 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሻምፒዮንስ ሊግ

ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የሚደረጉ የሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ ። በነገው ዕለት የእንግሊዙ አርሰናል የፖርቹጋሉ ፖርቱን ያስተናግዳል ። በመጀመሪያው ግጥሚያ ፖርቱ በሜዳው አርሰናልን 1 ለ0 አሸንፏል ። በመጀመሪያ ግጥሚያቸው አንድ እኩል የተለያዩት የስፔኑ ባርሴሎና እና የጣሊያኑ ናፖሊም የሚጋጠሙት ነገ ማታ ነው ።

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጋጣሚ ቡድኖችን ለመለየት ጣ ሲወጣ
የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጋጣሚ ቡድኖችን ለመለየት ጣ ሲወጣ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Martial Trezzini/KEYSTONE/dpa/picture alliance

ረቡዕ ዕለት የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከከሆላንዱ ፒኤስቪ አይንድሆቨን ጋ ይጋጠማል ። በመጀመሪያው ግጥሚያ አንድ እኩል ነው የተለያዩት ። በተመሳሳይ ሰአት ነገ ማታ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ለመልስ ግጥሚያው የጣሊያኑ ኢንተር ሚላንን ያስተናግዳል ። በመጀመሪያው ግጥሚያ ኢንተር ሚላን 1 ለ0 አሸንፏል ። በጣሊያን ሴሪኣ የደረጃ ሰንጠረዡንም ከተከታዩ ኤሲ ሚላን በ16 ነጥብ ርቆ በአጠቃላይ 75 ነጥቡ እየመራ ይገኛል ። በአንጻሩ አትሌቲኮ ማድሪድ በስፔን ላሊጋ 55 ነጥብ ሰብስቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ከመሪው ሪያል ማድሪድ በ16 ነጥብ ይበለጣል ። ቀደም ሲል የመልስ ግጥሚያቸውን ያደረጉት ሪያል ማድሪድ፤ ባዬርን ሙይንሽን፤ ፓሪ ሳን ጃርሞ እና ማንቸስተር ሲቲ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር