የጥምቀት በዓል አከባበር በጀርመን
ሰኞ፣ ጥር 11 2012
ለ 28 ዓመታት ተከፋፍሎ የቆየው ቅዱስ ሲኖዶሱ ከለውጡ በኋላ ዳግም መዋሃዱን ተከትሎም በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኙት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ደብረ ፀሃይ ቅስተ ማርያም እና ደብረ ሃይል ቅዱስ ዑራኤል ወቅዱስ ያሬድ አድባራት በቅርቡ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ከ 1.7 ሚልዮን ዩሮ በሚልቅ ወጭ በገዛው ሰፊ ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጠ በሚገኘው ግዙፍ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ የከተራና የጥምቀት በዓልን በሕብረት እና በልዩ ድምቀት አክብረዋል::በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የውጭ አገር ቱሪስቶችን ቀልብ ጭምር በእጅጉ የሚስበውን የጥምቀት ክብረ በዓለም በማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት ለመመዝገብ ውሳኔ ማሳለፉም ለኢትዮጵያውያኑ ከበዓሉ ሌላ ተጨማሪ ደስታ መፍጠሩን አስተውለናል:: አብዛኛዎቹ የበዓሉ ታዳሚዎች ምንም እንኳን በውጭው ዓለም በዓሉን በሰላም እና በነጻነት ማክበራቸው ቢያስደስታቸውም በአገር ቤት ግን ሥርዓት አልበኝነት መንገሱ እና በተለይም በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በካህናት እና በምዕመናኑ ላይ እየደረሰ ነው ያሉት ተደጋጋሚ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄዱ ደስታቸው ላይ የሃዘን ድባብ አጥልቷል::
በሺዎች የሚቆጠሩ የዕምነቱ ተከታዮች በታደሙበት በፍራንክፈርቱ የጥምቀት በዓል በአገር ቤት በተለይም በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በካህናት እና በምዕመናኑ ላይ እየደረሰ ነው ያሉት ተደጋጋሚ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄዱ አንዳንድ አድባራትም ለዘመናት ሲጠቀሙበት የኖሩትን የታቦታት ማደሪያ ስፍራ ተነጥቀው በየትኛውም ሥርዓት ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ የጥምቀትን በዓል ለማክበር አለመቻላቸውን መሰማታቸው ሕዝበ ክርስቲያናትን በእጅጉ ያሳዘነ ጉዳይ መሆኑ ነው የተገለፀው:: ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት በዶክተር ዓብይ የሚመራውን የለውጥ ኃይል ወደ ስልጣን መምጣት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአውሮጳ ጉዞ በመደገፍ በፍራንክፈርት ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተካፍለው ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ፍሬዘር ያ ስሜታቸው አሁን ላይ መቀየሩን አልሸሸጉንም::የጥቃቱ ዝምታስ እስከመቼ ይሆን ሲሉም ይጠይቃሉ::
በጀርመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት በሕብረትም ሆነ በተናጥልም ያከበሩት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የውጭ አገራት ዜጎችንም ትኩረት የሳበ ነበር:: በዓሉ በተለይም በፍራንክፈርቲ የመስካየ ኅዝናን መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን በደማቅ ኃይማኖታዊ ሥርዓት የተከበረ ሲሆን ምዕመኑን ጸበል የመርጨት ሃይማኖታዊ ስርዓት ከተከናወነ በኋላም ልክ እንደ አገርቤቱ ባህል በሃገር ባህል አልባሳት የተዋቡ ምዕመናን፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናት፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ታቦታቱን በዝማሬ በምስጋና እና በዕልልታ ወደ ክብር ማደሪያ መቅደሳቸው ሸኝተዋል::
እንዳልካቸው ፈቃደ
ነጋሽ መሐመድ