የጠ/ሚኒስትሩ የመፍትሔ እንክብሎች ይቀጥላሉ ወይስ አልቀዋል? | ኢትዮጵያ | DW | 31.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የጠ/ሚኒስትሩ የመፍትሔ እንክብሎች ይቀጥላሉ ወይስ አልቀዋል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አገሪቱ በፈተና ምጥ ተይዛ ባለችበት ወቅት ነበር ወደ ሥልጣን የመጡት። መንበረ ሥልጣኑን በተቆጣጠሩ የመጀመሪያ ቀናቶች ውስጥ ከችግሮቿ የሚገላግላት ሁነኛ መድኃኒት ማቅረብ ባይችሉም የሕመም ማስታገሻ እንክብሎችን እያዋጧት ነበር ማለት ይቻላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማንኛውም ዜጋ ሳይቀር በማይከብድ ቋንቋ ፍቅር፣ ይቅርታ እና ሠላምን ሰብከዋል። ይህም ጊዜያዊ እፎይታ አስከትሎ ነበር። ነገር ግን እያደር የሕመም ማስታገሻው እየደከመ፤ ሕመሙ እየበረታ መምጣቱ አይቀጥርም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ተዘጋጅተዋል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከሚያደርጓቸው ንግግሮች ጀምሮ እስከሚወስዷቸው እርምጃዎች ድረስ አስደናቂ ነበሩ። ፍጥነታቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ያልተለመደ ከመሆኑም በላይ ለመተንተንና ቀጣዩ ይህ ይሆናል የሚለውን ለመተንበይ ይቸግር ነበር። አሁን ግን ፍጥነቱ ጋብ ያለ ይመስላል። ጠንካራ ትችቶችም እየተሰነዘሩ ነው። ፍጥነቱ በምን ምክንያት ተቀዛቀዘ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገራሚ የመፍትሔ እንክብሎቻቸውን ጨርሰው ይሆን?
ከቅርብ ግዜ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የድንገቴ እርምጃዎች ሕዝቡም መደነቅ እየቀነሰ፣ በጣም ተቀባይነት ያገኙ ሐሳቦቻቸው ሳይቀር ለትችት እየቀረቡ ይመስላል። ሌላው ቀርቶ "መደመር" የሚለውና የከተሜው አንደበት ውስጥ ዘሎ የገባው  መርሓቸው ሳይቀር ተጠያቂ ሆኗል። "ከእነእከሌ ጋር አልደመርም" ከሚሉት ቅሬታዎች ጀምረው "መደመር ማለት ምንድነው? የራስን አመለካከት ይዞ ግዜያዊ ችግርን ለመፍታት መተባበር ወይስ ማንነትን ጥሎ በዘላቂነት መዋሐድ?" እስከሚለው ጥያቄ እየተነሳ በተቺዎች ተብጠልጥሏል።
በዚህ ሳምንት ደግሞ ሪኔ ሌፎርት እና አሌክስ ደዋል የተባሉ ሁለት የኢትዮጵያ ጉዳይ ታዋቂ ተንታኞች ስለኢትዮጵያ መፃኢ ግዜ የሚታያቸውን ጽፈዋል። ሁለቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሔድ አደጋ ያዘለ እንደሆነ አልሸሸጉም። ትልልቆቹን የፖለቲካ ተቃርኖዎች እየፈቱ ነው ተብሎ በሚታሰብበት ወቅት የፖለቲካ ተንታኞች አደጋው ብቻ የሚታያቸው በምን ምክንያት ነው?
ሰዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃዎች መደነቅ የቀነሱት በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው፣ ዋና የሚባሉት ፖለቲካዊ የለውጥ እርምጃዎች በሙሉ ተበስረው አልቀዋል። ከፖለቲካ እስረኞች ፍቺ የተሰደዱትን እስከ መመለስ፣ ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ሠላም ከማውረድ ጀምሮ የመንግሥት ንግድ ተቋማትን ለከፊል የግል ይዞታ ማዘዋወር ጉዳይ፣ ከአፋኝ ዐዋጆች መሻሻል እስከ ተቋማዊ መልሶ ማዋቀር - ሁሉም ተነግረው አልቀዋል። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዚህ የበለጡ አስደናቂ ቃል ኪዳኖችን መግባት ከዚህ በኋላ ይቸግራቸዋል። 
ሌላኛው ምክንያት የዜጎች እምነት መቀየሩ የወለደው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጡ ሰሞን የነበረው ግንዛቤ እርሳቸው የወሰዷቸውን እርምጃዎች ያደርጉታል ብሎ ለመገመት የማያስችል ነበር። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚነስትሩ ከኢሕአዴግ የወጡ እንደመሆናቸው "የኢሕአዴግን ጥቅም" ብቻ (ማለትም "ሰጥ ለጥ አድርጎ መግዛት") ያስጠብቃሉ ብሎ ይገመት የነበረ መሆኑ ነው። አሁን ግን ባለፉት አራት ወራት በተወሰዱት እርምጃዎች ስርዓቱ መለወጡን፣ አሮጌው ኢሕአዴግ ሞቶ አዲሱ መወለዱን ብዙ ሰው አምኗል። ሕዝቡ ፍላጎቱ እና ስርዓቱን የሚመለከትበት ዓይን ስለተቀየረ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አዳዲስ ቃል ኪዳኖች እንደ መጀመሪያው ሰሞን አይደነቅም።


ቀጥሎ ምን እንጠብቅ?
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክሮች፣ ንግግሮች እና አዳዲስ የማሻሻያ ሐሳቦች ዜጎችን ማስደነቅ ማቆማቸው ወይም መቀነሳቸው የማስታገሻ እንክብሎቹ መሥራት ማቆማቸውን ያሳያል። ቀጥሎ ፍቱን መድኃኒት የሚጠየቅበት ወቅት መምጣቱ አይቀሬ ነው። 
አምና ፖለቲካችን ጤነኛ አልነበረም። ፖለቲከኞች በየእስር ቤቱ፣ በስደት እና በጦር ሜዳዎች ተበትነው ነበር። ሲቪል ማኅበራት ተመናምነው ሞት አፋፍ ላይ ነበሩ፤ ብዙኃን መገናኛዎችም እንደዛው። ዘንድሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕመም ማስታገሻ እንክብሎች አማካይነት የተበተኑት ተቃዋሚዎች ተሰባስበው ዳግም እየተደራጁ ነው። ዐዋጆች እየተከለሱ እንደመሆኑ ሲቪል ማኅበራት እና ብዙኃን መገናኛዎችም ቀስ በቀስ ማበባቸው አይቀርም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማስታገሻ ሕክምና የፖለቲካ ምኅዳሩን ሊያሰፋው ይችላል፤ ለዘርፈ ብዙ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ግን መድኃኒት ሊሆኑ አይችሉም። የተቃዋሚዎች መልሶ መደራጀት አዳዲስ ጥያቄዎች እና አዳዲስ አማራጮችን ለሕዝብ ያስተዋውቃል። የሲቪል ማኅበራት እና ብዙኃን መገናኛዎች ማንሰራራትም ዜጎች መብቶቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን የሚያቀርቡባቸው አማራጮችን ያበረክታል። ያኔ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ፈተና በይፋ ይጀምራል። 
መፍትሔው ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ብዝኃነትን እንድትቀበል መፍቀድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከቀዳሚዎቻቸው በርግጥም የተለዩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ኢሕአዴግ በምርጫ ሊሸነፍ እንደሚችል ቢሰጉም እንኳ የፖለቲካ ምኅዳሩን ክፍት አድርጎ መጫወት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ የቻሉ እንደሆን ከማስታገሻ እንክብሎች ወደ ፍቱን መድኃኒት መስጠቱ ይሸጋገራሉ። አለበለዚያ ግን ወደ ቀደመው የቀውስ አዙሪት ተመልሶ ለመግባት ረዥም ግዜ አይወስድም። 

በፈቃዱ ኃይሉ
በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የዶይቸ ቬለን አቋም አያንጸባርቅም።
 

ተዛማጅ ዘገባዎች