1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

„የጠቢባን ማእድ“ የስደተኛዉ ማስታወሻ

ሐሙስ፣ ግንቦት 1 2016

„ጠላትህ እንዳይሰማ የምትፈልገዉን ሚስጢር ለጓደኛህ አትናገር። -የንግግር ሰዎች ተግባር ይርቃቸዋል። -ፍቅርን በጥሩ ዋጋ ሊገዛዉ የሚችል ነገር ቢኖር ፍቅር ብቻ ነዉ። -በቁጣ ከሚደሰት ይልቅ መሳቅ የሚወድ ሰዉ የበለጠ ጠንካራ ነዉ። -ዓይን ራሱን ሲያምን ጆሮ ግን የሰማዉን ያምናል“ ከ„የጠቢባን ማእድ የተወሰደ።

https://p.dw.com/p/4fexL
Deutschland Wondesen Yehualashet
ምስል private

„የጠቢባን ማእድ“ የስደተኛዉ ማስታወሻ

„የጠቢባን ማእድ“ የስደተኛዉ ማስታወሻ

«በዚህ መጽሐፍ ዉስጥ ከብዙ ነገር በጥቂት በጥቂቱ እናገኛለን። እንደ «ብፌ» ማለት ነዉ። የስፖርቱንም፤ ቀልዱንም፤ አባባሉንም፤ የሃገራት ትልልቅ የተባሉ ሃያስያን ንግግር ፤ ዉልደታቸዉ እድገታቸዉ ብሎም ከነፎቶግራፋቸዉ በመጽሐፉ ዉስጥ ይገኛል። አንባቢዉ በቀላሉ እንዲረዳዉ ነዉ ይህን ያደረኩት። 

በቅርቡ „የጠቢባን ማእድ“ በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሐፍ ለአንባብያን ያቀረቡት ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት ናቸዉ። በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ አቅራብያ ሲኖሩ 24 ዓመት እንደሆናቸዉ የሚናገሩት ደራሲ ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት ማንበብ «ሆቢዬ» ነዉ የምወደዉ መዝናኛዬ ነዉ ሲሉ ይናገራሉ። አሁን ለመጀመርያ ጊዜ ለአንባብያን ያሳተሙት መጽሐፍ ከዛሬ 38 ዓመት ጀምሮ ከተለያዩ ጋዜጣዎች መጽሔቶች፤ መጽሐፎች፤ የቴሌቭዥንና የሬድዮ ፕሮግራሞችን እና ታማኝ  ካልዋቸዉ  ድረ-ገጾች ያሰባሰቧቸዉ ናቸዉ። ጽሑፎቹን ከሬድዮም ሆነ ከቴሌቭዝን ሰሙት፤ በእጃቸዉ እየጻፉ ምንጭ እያስቀመጡ ለ38 ዓመታት ሲሰበስቡ ዘልቀዋል። በእጅ እየጻፉ ካሰባሰቧቸዉ ጽሁፎች መካከል ጥቅሶች፤ ወርቃማ አባባሎች፤  ምክሮች፤  ቀልዶች፤  ቅንጭብጭብ ታሪክን እና ድንቃ ድንቅ የሚባሉ ጽሑፎች ይገኙበታል።   

«መጽሐፉ የፈጀዉ 38 ዓመት ነዉ። መጽሐፉ የመጀመርያ ገጽ ላይ እንደሚናገረዉ፤ ከ 1976 ዓ.ም ጀምሮ ማለትም ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ብዙ መጽሐፍትን አነብ ነበር። በዝያን ዘመን እንደ አሁኑ የተለያዩ የሚዲያ ማሰራጫ ባልተስፋፋበት ዘመን በተለይ 1970 ዎቹ ቤት ዉስጥ 1980 ቤት ዉስጥ  ካነበብኳቸዉ በእጄ እየጻፍኩ ያጠራከምኳቸዉ ጽሑፎች ናቸዉ አሁን መጽሐፍ መልክ ተሰብስበዉ ለአንባብያን የቀረቡት»

ደራሲ ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት
ደራሲ ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸትምስል private

„የጠቢባን ማእድ“ የተሰኘዉ እና በዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት ለአንባብያን በቀረበዉ መጽሐፍ ላይ የቻይናዉያን የስፔናዉያን የጃፓናዉያንን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች አባባሎች በረድፍ በረድፍ ተጽፈዉ ይገኛሉ።  የጀርመናዉያን አባባሎች በሚለዉ ስር ከተቀመጡት መካከል በጥቂቱ ፤„ጠላትህ እንዳይሰማ የምትፈልገዉን ሚስጢር ለጓደኛህ አትናገር። -የንግግር ሰዎች ተግባር ይርቃቸዋል። -ፍቅርን በጥሩ ዋጋ ሊገዛዉ የሚችል ነገር ቢኖር ፍቅር ብቻ ነዉ። -በቁጣ ከሚደሰት ይልቅ መሳቅ የሚወድ ሰዉ የበለጠ ጠንካራ ነዉ። -ዓይን ራሱን ሲያምን ጆሮ ግን የሰማዉን ያምናል“  ይላል። ከአስር የማያንሱ የዓለም ሃገራት አባባሎች፤ የታዋቂ ሰዎች ታሪኮች፤ በራድዮ አልያም በጋዜጣ የተጻፉትን ሁሉ ለ 38 ዓመታት ያሰባሰቡ የነበሩት  ዲ/ን ወንድወሰን ፤ በእጃቸዉ ነበር የሚጽፉት። መጽሐፉን ለማሳተም ወደ ኢትዮጵያ ሄደዉ በኮንፒዉተር ተጽፎ አራት መቶ ገጽ እንደወጣዉ ተናግረዋል።

ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት ሁለተኛ መጽሐፍም ለማሳተም እቅድ ይዘዋል። የምረቃ ሥነ-ስርዓቱ በሚኖሩበት በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ኢትዮጵያዉያንን በተጋበዙበት በቅርቡ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ዲ/ን ወንድወሰን ይህን ሁሉ ዓመት በእጃቸዉ እየጻፉ ያጠራቀሟቸዉን የተለያዩ መጣጥፎች በመጽሑፍ መልክ ሲያስቀምጡ አንድም ቀን መጽሐፍ አሳትመዋለዉ ብለዉ እንዳላሰቡ ተናግረዋል። ይሁንና እዚሁ በጀርመን ሃምቡርግ ከተማ የሚገኝ ጋዜጠኛ እና ዲያቆን ባልንጀራቸዉ መክሯቸዉ መጽሐፍ ማሳተም ወደሚለዉ ሃሳብ መግባታቸዉን አልሸሸጉም።  

በጀርመን ፍራንክፈርት በሚገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንየሚያገለግሉት ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት እዚያዉ በሚኖሩበት ፍራንክፈርት ከተማ አቅራብያ በሚገኝ የሊፍት ወይም የአሳንስር አምራች ድርጅት ዉስጥ፤ በኤሌትሪክ ስራ ተሰማርተዉ እንደሚገኙም ነግረዉናል። 

ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት፤ በቅርቡ ካሳተሙት „የጠቢባን ማእድ“ ከተሰኘዉ መጽሐፋቸዉ ዉስጥ የሕይወት መመርያ ሊሆኑ የሚገቡ ጠቃሚ ምክሮች በሚልር ርዕስ ስር ከተቀመጠዉ ምክር አዘል መጣጠፍ መካከል ይህን ልናካፍል ወደድን።

ከአብርሆት ቤተ-መጸሕፍት የተሰጠ ምስክር ወረቀት
ከአብርሆት ቤተ-መጸሕፍት የተሰጠ ምስክር ወረቀትምስል private

-ጽናት ድልድይ ነዉ። ተስፋ መቁረጥ ግድግዳ ነዉ። ሁለቱም በቃላት ይገነባሉ። አልችልም። አይሆንም አይሳካም፤ ከንቱ ነዉ፤ የትም አልደርስም፤እድሜዬ ሄድዋል፤ የሚለዉን ግንብ አፍርስ። ይቻላል። ይሳካል። የማይሆን ነገር የለም። እኔ አሸናፊ ነኝ ብለህ ለዉስጥህ ንገረዉና ወደ ስኬትህ በድል ተሻገር። ስለዚህ እኔ ድልድይ እንጂ ግድግዳ አልሰራም። አሸናፊ ነኝ ። ያሰብኩት ሁሉ ይሳካል። እኔ ሰዉ ነኝ፤ ሰዉ ዓለምን ይቀይራል። እኔም ከቀያሪዎቹ አንዱ ነኝ በል። ይላል።

ደራሲ ዲ/ን ወንድወሰን የኋላእሸት ለሰጡን ቃለ-ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን፤ ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀዱን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረእግዚአብሔር