1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ስድስት የስልጣን ዓመታት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2016

በመላው ኦሮሚያ ትላልቅ ከተሞች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ስልጣን የመጡበት እና በስድስት ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው አሳኩ የተባሉ ስራዎችን የሚያበረታታ የድጋፍ ሰልፍ ተደርጓል፡፡

https://p.dw.com/p/4eLwK
Äthiopien Shaggar City | Kundgebung
ምስል Seyoum Getu/DW

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ስድስት ዓመታት በስልጣን ላይ

የጥቀላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ በኦሮሚያ

ዛሬ በመላው ኦሮሚያ ትላልቅ ከተሞች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ስልጣን የመጡበት እና በስድስት ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው አሳኩ የተባሉ ስራዎችን የሚያበረታታ የድጋፍ ሰልፍ ተደርጓል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስኬት ስራዎች በተሞካሹበት በድጋፍ ሰልፉም በህዝቦች ትብብር ሰላምን ማጽናት የሚሉ መፈክሮች ጎልተው ተስተጋብቷል፡፡

በተቃራኒውም አስተያየታቸውን የሚሰጡ የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት በባለፉት ስድስት ዓመታት ከታዩት ስኬቶች አገሪቱ ያጣቻቸው በረከቶች ብዙ ናቸው በሚል ቅሬታ የሚያሰሙ አሉ፡፡

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስድስት ኣመታት አመራር ስኬት”

የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስድስተኛ ዓመት የስልጣን ዘመንን የዘከረው የድጋፍ ሰልፍ በኦሮሚያ ክልል ከሸገር ከተማ እስከ የተለያዩ በርካታ የዞን ከተሞች ተካሂዶ ውሏል፡፡ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመጡ የተባሉ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተስፋዎች ተሞካሽተዋል፡፡ ሰልፉ ላይ የታደሙ አስተያየት ሰጪዎችም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስድስት ዓመታት በፊት ልትበተን ከቋፍ የደረሰችውን አገር አንድነቷን አጽንተዋል” ይላሉ፡፡ በግብርናውም መስክ በወሰዱት የበጋ እና መኸር የስንዴ ምርት ኢኒሼቲቭ አመርቂ ያሉት ስራ መስራታቸውን ያነሳሉ፡፡

ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ ከወጡ የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ
የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስድስተኛ ዓመት የስልጣን ዘመንን የዘከረው የድጋፍ ሰልፍ በኦሮሚያ ክልል ከሸገር ከተማ እስከ የተለያዩ በርካታ የዞን ከተሞች ተካሂዶ ውሏል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

በተለይም አገር መረጋጋት በተሳናት ጊዜ “በአንድ እጃቸው ልማቱን በሌላኛው እጃቸው ሰላምን ለማጽናት ይታገላሉ” ያሉት የድጋፍ ሰልፉ ታዳሚዎች ከህዝብ ዘንድ ሰላምን የማጽናት እገዛ ብያገኙ የበለጠ ልማቱን እንደሚሳኩም በማሰብ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡የድጋፍ ሰልፍ በኦሮሚያ

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ እንደ ነቀፌታ የተነሱ ሃሳቦች

በኦሮሚያ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለውን ተቃዋሚውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ የሚመሩት ፕሮፌ ሰር መረራ ጉዲና ግን በዚህ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ አይመስሉም፡፡ “በርግጥ የሚታይ ልማት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ስር ተሰርተዋል” በማለት ሃሳባቸውን የጀመሩት መረራ፤ ግን ደግሞ ይላሉ “ኦሮሚያም ጭምር በሰላም እጦቱ ሰው በድሮን ጭምር እየተጎዳ ነው” ብለዋል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ውጤቶቹ ይበዛሉ የሚል ምልከታ እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ሰፊ የማህበረሰብ ድጋፍ መቸራቸውን ያስታወሱት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህሩ ሲሳይ አሳምሬም የጠበቁትን ለውጥ ግን አለመመልከታቸውን ያነሳሉ፡፡ “በኢኮኖሚው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት ፈታኝ ጋረጣን ደቅኗል፡፡ በፖለቲካም እንደ ቀድሞው ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኞች እና ምሁራን ይታሰራሉ፡፡ በርካቶች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋልና የድፍ ሰልፉ ከምን የመነጨ እንደሆነ አይገባኝም” በማለት ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
በኦሮሚያ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለውን ተቃዋሚውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ የሚመሩት ፕሮፌ ሰር መረራ ጉዲና ግን በዚህ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ አይመስሉም፡፡ምስል Eshete Bekele Tekele/DW

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት መብራቱ ገርጅሶም አሁን ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝባዊ ድጋፍ እንደቀድሞው መሆኑን ይጠራጠራሉ፡፡ “ህዝቡ የመጀመሪያውን ሁለት ዓመታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ አደባባይ የሚወጣው በራሱ ተነሳሽነት ነበር፡፡ አሁን ግን እነደዛ አይመስለኝም፡፡ በርግጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራርነት የተሰሩ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከዚያ ወዲያ ግን በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ህዝቡን ሊያስደስት የሚችል ነገር አይታየኝም” በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡የኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድና የተቃዋሚ የፖለቲካ ቅሬታ  

ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ ከወጡ የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስኬት ስራዎች በተሞካሹበት በድጋፍ ሰልፉም በህዝቦች ትብብር ሰላምን ማጽናት የሚሉ መፈክሮች ጎልተው ተስተጋብቷል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

ባለፉት ስድስት ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትርነት በትረ ስልጣን ጨብጠው ኢትዮጵያን የመሩዋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንደ ድጋፍ ሁሉ ሰፋፊ ተቃውሞም ገጥሞአቸው ያውቃል፡፡ በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በስፋት እርስበርስ ግጭቶች ተቀስቅሰው መቶ ሺዎች እንዳለቁ፣ ሚሊዮን ዜጎች እንደተፈናቀሉ እና በቢሊየን ዶላሮች የሚተመን ንብረት የወደመም በሳቸው አመራር ዘመን ነው፡፡ በርግጥ ለሁሉም ጥፋቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠያቂ ሊሆኑ አይገባም የሚሉ ድምጾች እንደሚሰሙ ሁሉ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከስድስት ኣመታት በፊት ለውጥ እንዲመጣ አብሯቸው ታግለዋል የተባሉትም ጭምር የኋላ ኋላ የተቃውሞ ጎራ መቀላቀላቸው ቅሬታን ካሰፉ አበይት ጉዳዮች ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡ በርካቶች አገሪቱ ከገባችበት የግጭት አዘቅጥ ትወጣ ዘንድ መመካከርን እና መደማመጥን አብዝተው እያሹ ነው፡፡

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ