1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የፓርቲዎች ውይይት

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2016

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያዩ። በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ጥሪው ቀርቦላቸው በውይይቱ ከመሳተፍ የተቆጠበ የአንድ ፓርቲ መሪ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎች አምስት፣ ከክልል ፓርቲዎች ሦስት ሦስት ተወካይ መጋበዛቸውን ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4eJoh
Äthiopien Premierminister Abiy Ahimed Diskussion
ምስል Office of Prime minister of Ethiopia

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያዩ። በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ጥሪው ቀርቦላቸው በውይይቱ ከመሳተፍ የተቆጠበ የአንድ ፓርቲ መሪ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎች አምስት፣ ከክልል ፓርቲዎች ሦስት ሦስት ተወካይ መጋበዛቸውን ገልፀዋል። በሌላ በኩል 13 ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ካሰባሰበው ኮከስ አባል ፓርቲዎች መካከል አብዛኞቹ በስብሰባው አለመሳተፋቸውን የአንድ ፓርቲ መሪ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። በውይይቱ የሀገሪቱ ሰላምና ደኅንነት፣ ግጭቶች የሚፈቱበት ሁኔታ፣ የቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ እና መሰል ሀገራዊ ጉዳዮች መነሳታቸው ታውቃል።ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀዉስ እንድትወጣ ሁሉን አቀፍ ዉይይት መጠየቁ

ተሳታፊዎች ምን አሉ?

በዛሬው ውይይት ከተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ጸሐፊ የሆኑትን ዶክተር ራሔል ባፌን ጠይቀናቸዋል። «ጥሩ ነበር። ያው ለረጅም ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አንዳንድ ጉዳዮች ላይ እንደ የጋራ ምክር ቤት ለመገናኘት ጠይቀን አልተሳካም ነበር። አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ክፍሎችን እያነጋገሩ ስለነበረ እኛም እንደ አንድ ባለድርሻ እድሉ ተሰጥቶን ነበር» በማለት በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልፀዋል።የፊት ለፊቱ ንግግር አንድምታ እና የኢትዮጵያ መሻት

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተደረገው ውይይት ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ከእያንዳንዳቸው ስድስት፣ ከክልላዊ ፓርቲዎች ሦስት ሦስት ተወካዮች መሳተፋቸውን የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ በቀለ ነግረውናል። ፓርቲያቸው ግን በውይይቱ ከመሳተፍ ተቆጥቧል። «እኛም የጋራ ምክር ቤት አባል እንደመሆናችን ጥሪውና ግብዣው ደርሶናል። እኛ ግን ለገጽታ ግንባታ እና ፓርቲው የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በሕዝብ አድናቆትን ተቸራቸው የሚለውን ለማሳየት ስለሆነ ዋጋ የለውም ብለን ነው የተውነው።»

ኮከስ የተባለው ስብስብ አባላቱ አልተሳተፉም

13 የፖለቲካ ፓርቲዎችን አባል ያደረገው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ኮከስ የውይይቱን ጥሪ እንዳልተቀበለው እና እንዳልተሳተፈ አንደኛው አባል ፓርቲ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናግረዋል።ሰላም እና የሲቪክ ድርጅቶች አስተዋጽዖ

ውይይቱ ቀጣይ ነው ተብሏል

በውይይቱ መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ያሉት ዶክተር ራሔል ባፌ ውይይቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል ብለዋል። የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር በአዲስ አበባ እንዲሁም የክልል ፓርቲዎች ከክልል የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ