1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በበልግ ወራት የጎርፍ አደጋ የሚያሰጋቸው የአፋር፣የአማራ፣የኦሮሚያ፣የሶማሊና ደቡብ ክልሎች

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2016

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፤ በሶማሌ ክልል ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ ሊጠቁ እንደሚችሉ፣በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች 145,000፣ በኦሮሚያ 421,000 ፣ በአፋር ወደ 83,000 የሚጠጉ ሰዎች ፣ በአማራ 45,000 እንዲሁም በትግራይ 4,000 የሚጠጉ ሰዎች የጎርፍ ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ መተንበዩን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4fIiv
Äthiopien | Überflutung in Konso-Zone
ጎርፍ በኮንሶ ዞን ከአንድ ዓመት በፊት ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የጎርፍ አደጋ የሚያሰጋቸው የአፋር፣የአማራ፣የኦሮሚያ፣የሶማሊና ደቡብ ክልሎች

የበልግ ዝናብ በሚዘንብባቸው ወራት ውስጥ የአፋር ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሊ እና ደቡብ ክልሎች በከፍተኛ ደረጃ ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ  መለየቱን በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) አስታወቀ። በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሚመራና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አጋሮችን ያካተተ የጎርፍ ቅድመ መከላከል እቅድ መዘጋጀቱን የገለፀው ድርጅቱ በሶማሊ ክልል ብቻ ከ 1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ ሊጠቁ እንደሚችሉ አስታውቋል። ባለፉት የበልግ ወራት ቅጽበታዊ የጎርፍ ተጋላጭነትን ያስከተሉ የጎርፍ አደጋዎች ተከስተው እንደነበር የገለፀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ ኢንስቲትዩት "በቀሪው የበልግ ወራትም ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ስርጭት ይኖራቸዋል" ብሏል። የሰሞኑ ከባድ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ዜጎችን ሕይወት እየነጠቀ፥ መሠረተ ልማቶችንም እያወደመ ነው።
ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዝርዝር ዘገባ አዘጋጅቷል። የጎርፍ አደጋና ስጋት በኢትዮጵያ

የትኞቹ አካባቢዎች በምን መጠን የጎርፍ ተጋላጭ ናቸው?

በኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሚመራው የሰብአዊ እርዳታ አጋሮችን ያካተተ የበልግ ዝናብ ወቅት የጎርፍ ተጋላጭነት ቅድመ ዝግጅት እቅድ መውጣቱን የገለፀው በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፤ በአምስት ክልሎች ከፍተኛ የጎርፍ ተጋላጭነት የሚያስከትል ሁኔታ እንደሚፈጠር አስታውቋል።
በሶማሌ ክልል ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ ሊጠቁ እንደሚችሉ፣ 773,000 ደግሞ እንደሚፈናቀሉ ይጠበቃል ያለው ይሄው ድርጅት፣ በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች 145,000 ፣ በኦሮሚያ 421,000 ፣ በአፋር ወደ  83,000 የሚጠጉ ሰዎች ፣ በአማራ 45,000 እንዲሁም በትግራይ 4,000 የሚጠጉ ሰዎች የጎርፍ ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ መተንበዩን ገልጿል።
በአዲስ አበባ ፣ በድሬዳዋ በባቲ እና ሌሎችም ከተሞች ቅጽበታዊ ጎርፍ ያስከተለ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ዘንቦ እንደነበር ያስታወቁት በኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጅ ኢንስቲትዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ እስካሁን በነበሩት የበልግ ወራት ከመደበኛ መጠን በላይ የዝናብ ስርጭት እንደነበር ገልፀዋል።
"በየካቲት ፣ በመጋቢት እና እስከዛሬ ድረስ በሚያዝያ ወር በብዙ የሀገራችን አካባቡዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ሥርጭት ነበራቸው"።ያም ሆኖ ግን ይሄው የበልግ ወቅት ዝናብ ለግብርና ሥራ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።

በዳሰነች ከሁለት ዓመት በፊት የደረሰ የጎርፍ ማጥለቅለቅ
በዳሰነች ከሁለት ዓመት በፊት የደረሰ የጎርፍ ማጥለቅለቅምስል Shewangizaw Wegayehu

በጎርፍ ምክንያት እየደረሰ ያለው ጉዳት

ትናንት ሚያዝያ 20 ለዛሬ እጥቢያ እስከ ረፋዱ 3:30 ድረስ በአዲስ አበባ ከባድ ዝናብ የዘነበ ሲሆን ያንን ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ እስከ ቀኑ አሥር ሰዓት ድረስ አራት ሰዎች ሞተው መገኘታቸውን የሀገር ውስጥ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። በኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጅ ኢንስቲትዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ በቀጣይ የበልግ ወራት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ጎርፍ የሚያስከትል ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል ትንበያ ማመልከቱን ገልፀዋል።የጎርፍ ስጋት የደቀነው የዘንድሮ ክረምት በኢትዮጵያ
"በቀሩው የበልግ ወራትም በተለይም ከእለት ወደ እለት ለበልግ ዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎቻችን ይጠቁማሉ"።

የተበበሩት መንግሥታት ማስጠንቀቂያ 

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀጠለው የፀጥታ ችግር ባለፈ የድርቅ ሁኔታዎች እንዲሁም ኤል ኒኖ በሚያስከትለው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የሚከሰት ጎርፍ የሚያስከትለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የዜጎች ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን አስታውቃል።
ሰሞነኛው የጎርፍ አደጋ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን በኬንያ እስካሁን 76 ሰዎች፣ በታንዛኒያ ደግሞ 155 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል። የተባበሩት መንግስታት ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወቅት በዚሁ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ ባሉ ሀገራት ጎርፍ 300 ሰዎችን መግደሉን አስታውሷል።

ሰሎሞን ሙጬ


ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ