1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ዶናልድ ትራምፕ ላይ ዳግመኛ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ

ሰኞ፣ መስከረም 6 2017

"ተጠርጣሪው፣ከትራምፕ በግምት ከ300-500 ሜትሮች ርቀት ላይ በጎርፍ ኮርሱ ውስጥ በነበረበት ሁኔታ፣አንድ የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረባ ተኩስ ከፍቶበታል።ተጠርጣሪው፣በጎልፍ ኮርሱ የሰንሰለት አጥር ዳርቻ ጠመንጃውን አነጣጥሮ ተመልክተውታል።"

https://p.dw.com/p/4kgYx
 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ
 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕምስል Alex Brandon/AP Photo/picture alliance

ድጋሚ የግድያ ሙከራ በትራምፕ

 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ዳግመኛ የግድያ ሙከራ እንደተፈጸመባቸው ተገለጸ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት፣በዶናልድ ትራምፕ ላይ ትናንት የግድያ ሙከራው የተፈጸመባቸው፣ፍሎሪዳ በሚገኘው የጎልፍ ክለባቸው ሲሆን፣ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ውሏል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ሆነው ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለመመለስ፣የዛሬ ሁለት ወር ግድም በፔንሲልቫኒያ ግዛት ባካሄዱት የምርጫ ዘመቻ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው፣ጆሯቸው በጥይት መጨረፉ ይታወቃል።

ትናንት ለሁለተኛ ጊዜ የግድያ ሙከራ የተፈጸመባቸው ደግሞ፣ንብረታቸው በሆነውና ፍሎሪዳ በሚገኘው የጎልፍ መጫወቻ ላይ ሳሉ ሲሆን፣ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ውሏል።

ተጠርጣሪው ማነው?

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ተጠርጣሪው ሪያን ዌስሊ የተባለ የ58 ዓመት የሀዋይ ግዛት ነዋሪ ነው።

በዚሁ ግለሰብ የማኀበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ በተካሄደ ምርመራ እንደተመለከተው፣ተጠርጣሪው የውጭ ዜጎች ወደ ዩክሬን በመሄድ ከሩሲያ ጋር እንዲዋጉ በመጠየቅ የተለያዩ ጽሑፎችን አስፍሯል።

ሪያን፣በኖርዝ ካሮላይና ግዛት የተለያዩ ወንጀሎች ይፈጽም እንደነበር ተነግሯልም።

በቅርብ ጊዜ የወጡ የማኀበራዊ ሚዲያ ጽሑፎች ለፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደንና ለዴሞክራቲክ ፓርቲው ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ካማላ ሃሪስ ድጋፉን የገለጸባቸው ናቸው።

ባለፈው በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተደረገውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ፣ባይደንና ሃሪስ በወቅቱ የምርጫ ቅስቀሳ ዝግጅቱ ላይ እንደነበረ በተገደለው የቀድሞ የእሳት አደጋ ሠራተኛ የቀብር ሥነስርዓት ላይ እንዲገኙ አሳስቦ እንደነበርም ታውቋል።

በቅርቡ በዴሞክራቲክ ፓርቲ የመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ወቅት በአካል በመገኘት ድምጽ ሰጥቷል።

የፖሊስ ኃላፊው መግለጫ

ይኸው ተጠርጣሪ የትናንትናውን ግድያ እንዴት እንፈጸመ ባለሥልጣናት ሲገልጹ፣ተጠርጣሪው በትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ በፈጸመበት ወቅት ከእርሳቸው ከ300-500 ሜትሮች ርቀት ላይ ነበር።

ሪክ ብሬድሻው፣በፍሎሪዳ ፓልም ቢች አውራጃ የፖሊስ ኃላፊ ናቸው።

"ተጠርጣሪው፣ከትራምፕ በግምት ከ300-500 ሜትሮች ርቀት ላይ በጎርፍ ኮርሱ ውስጥ በነበረበት ሁኔታ፣አንድ የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረባ ተኩስ ከፍቶበታል።ተጠርጣሪው፣በጎልፍ ኮርሱ የሰንሰለት አጥር ዳርቻ ጠመንጃውን አነጣጥሮ ተመልክተውታል።"

የፈዴራሉ የምርመራ ቢሮ በምህፃረ ቃሉ ኤፍቢአይ በበኩሉ፣ትራምፕ ተጠረጣሪው ከነበረበት ቦታ ከ275 እስከ 455 ሜትር ርቀት ላይ እንደነበሩ አስታውቋል።

ተጠርጣሪው ጥቃቱን ለመፈጸም ይዟቸው ስለነበሩ መሣሪያዎችየፖሊስ ኃላፊውየሚከተለውን ተናግረዋል።

"ተጠርጣሪው በተገኘበት አካባቢ AK-47 ዓይነት የጦር መሣሪያ፣ማነጣጠሪያ፣ሁለት ቦርሳዎች እና ጎ ፕሮ ካሜራ ተገኝተዋል።"

ይኸው ተጠርጣሪ፣በአሜሪካ የደኅንነት ጥበቃ ተቋም/ሴክሬት ሰርቪስ/ባልደረቦች ተኩስ ሲከፈትበት፣ከተደበቀበት ጫካ ወጥቶ ወደ አንድ ኒሳን መኪና በመሄድ ዘልሎ መግባቱን አንደ የዐይን እማኝ ተናግሯል።

የዐይን እማኙ፣የተጠርጣሪውን መኪና እና የሰሌዳ ቁጥር ፎቶ ያነሳ ሲሆን መኪናዋ ከቆይታ በኃላ በጎልፍ መጫወቻው ሰሜናዊ ክፍል መገኘቷን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ተጠርጣሪውም፣መኪናው ውስጥ እንዳለ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ
 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕምስል Rick Bowmer/AP/picture alliance

የምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ መልዕክት

በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ የሆኑት ካማላ ሃሪስ፣በX ማኀበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ትራምፕ ላይ ስለተሞከረው ግድያ ገለጻ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።

ትራምፕ ደኅና በመሆናቸው ደስተኛ ነኝ ያሉት ካማላ ሃሪስ፣አሜሪካ ውስጥ ሁከት ቦታ የለውም ብለዋል በዚሁ መልዕክታቸው።

ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደንና ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ በግድያ ሙከራው ምርመራ ዙሪያ ወቅታዊ መረጃዎችን በመከታተል ላይ ሲሆኑ፣ ዶናልድ ትራምፕ ላይ ጉዳት ባለመድረሱ እፎይታ እንደተሰማቸው ከነጩ ቤተመንግስት የወጣው መረጃ አስታውቋል።

ትራምፕ ምን አሉ?

ዶናልድ ትራምፕ ከግድያ ሙከራው በኇላ ለደጋፊዎቻቸው በላኩት የኤሜል መልዕክት፣በአካባቢያቸው ተኩስ እንደነበረ፣እርሳቸውን ግን ደኅና መሆናቸውን ገልጸዋል።
ታሪኩ ሃይሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ