1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዜጠኞች የማኅበራዊ አንቂዎችና የሌሎች ተጠርጣሪዎች እስር ፤ መልዕክት ለአፍሪቃ መሪዎች

ዓርብ፣ ግንቦት 19 2014

ኢሰመጉ ግለሰቦች ከየቦታው ተጠልፎው ለተውሰኑ ቀናት የት እንደደረሱ አለመታወቁ እና ኃለፊነቱን የሚወስድ አካል አለመኖሩ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ሕገ-መንግሥታዊ መብትን መቃወም ነው ፤ እሥራቶቹም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣የንግግር ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት መብቶችን የሚገድብና አደጋ ላይ የሚጥልም ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/4BuNI
Daniel Bekele | Leiter der äthiopischen Menschenrechtskommission
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

የአርብ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ቅኝት


የአማራ ክልል ከ4ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን ማስታወቁ፣ ካለፈው ሰሞን አንስቶ በዚህ ሳምንትም የቀጠለው የጋዜጠኞችና የማኅበራዊ አንቂዎች እስር በኢትዮጵያ እንዲሁም የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ለአፍሪቃ መሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዝግጅት ትኩረት ናቸው።
የአማራ ክልል ከ4ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በዚህ ሳምንት ሰኞ ነበር ይፋ ያደረገው።የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች  በሰጡት መግለጫ  «ሕግን ለማስከበር ተካሄደ ባሉት በሰሞኑ እንቅስቃሴ  ከ4552 ያላነሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል» ብለዋል።  በማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘግቡ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል። 
ሰሎሞን ጌታቸው   «የማይመስል ነገር ተቃውሞን በማፈን ማስቆም አይቻልም፡፡ ሲሉ በአጭሩ አስተያየታቸውን በፌስቡክ አስፍረዋል።
ሳምሶን ክብረት በሚል የፌስቡክ ስም የተጻፈ አስተያየት
« ምንም አይነት ቀውስ ባልተሰማበት ሁኔታ በሰሞኑ ዘመቻ ብቻ ይሄን ያህል ሰው ማሰር ምን ይባላል? » በማለት እስሩን ተቃውመዋል።
ኤርሚያስ ኢትዮ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ግን ሳምሶን ካሉት ይለያል
«በዚህ እርምጃ ለምሳሌ አደገኛ ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ወንጀልን መቀነስ እንዲሁም በተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ደግሞ ህዝቡ በፖሊስ ላይ እምነት እንዲኖረው ያደርጋል ሱሉ እርምጃውን ደግፈዋል። 
አቶ ገሞራው ደግሞ ግልጽ እንዲሆንላቸው ስለሚፈልጉት ጉዳይ ጥያቄ አቅርበው መሆን አለበት ያሉትንም ጠቁመዋል።
«ከ4ሺህ በላይ የተባሉት ወንጀለኞች ቢሆኑ እሰየው ነበር። ነገር ግን በዚህ ሽፋን " ፋኖን ለማጥፋት ነዉ " ስለሚባለዉ እዉነታዉን ህዝብ እንዴት ይወቀዉ? ሲሉ ከጠየቁ በኋላ « ቢያንስ ሕጉ በሚያዘዉ መንገድ የፍርድ ቤት መጥሪያ ይዞ ፖሊስም ማንነቱን ሳይደብቅ በይፋ ተይዘዉ የተወሰዱበትም ጣቢያ ለቤተሰብ ግልፅ ተደርጎ በ 48 ሠዓት ፍ/ቤት መቅረብ ይኖርባቸዋል»ሲሉ አሳስበዋል። ያረጋል ሉሌ በበኩላቸው ከሚያስተዳድሩት ህዝብ ጋር እልህ በመጋባት የአማራን ህዝብ የግጭት አውድማ ማድረግ ትክክል አይደለም ። ሰከን በሉ እባካችሁ ሲሉ አሳሪዎችን መክረዋል።
ሰሞኑን በጋዜጠኞች በማኅበራዊ አንቂዎችና ና በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ የሚካሄደው እስር  እንዳሳሰባቸው የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመጉ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ በማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው ባወጧቸው መግለጫዎች አስታውቀዋል። ኢሰመጉ በዚህ ሳምንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ግለሰቦች ከየቦታው  ተጠልፎው ለተውሰኑ ቀናት የት እንደደረሱ አለመታወቁ እና ኃለፊነቱን የሚወስድ አካል አለመኖሩ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ሕገ-መንግሥታዊ መብትን  መቃወም ነው ብሏል።  እነዚህ ተደጋጋሚ እሥራቶች በኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ ያለውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣የንግግር ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት መብቶችን አለአግባብ የሚገድብና አደጋ ላይ የሚጥልም ነው ሲል አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች “በተቀናጀ መንገድ የሕግ በላይነትን ማስከበር” በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት መውሰድ በጀመሩት እርምጃ፣ በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት ያለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን መመልከቱን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።  በተለይም በአማራ ክልል በርካታ ታሳሪዎች ከመደበኛ መኖሪያ አካባቢያቸውና ከመደበኛ እስር ቦታዎች ውጭ ጭምር በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንኳን ለማወቅ መቸገራቸውን መረዳቱን ገልጿል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ“የዚህ አይነት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን” ገልጸዋል። 
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢያ አህመድ በጻፈው ደብዳቤ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ከቤታቸውና ከሥራ ገበታቸው በጸጥታ ኃይሎች መታፈናቸው እንዳሳሰበው ገልጾ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ሰምተው እንዳልሰሙ መሆናቸው እንዳሳዘነዉ ጠቅሶአል። መንግሥት ጋዜጠኞችን በሕግ አግባብ ብቻ እንዲጠይቅ እና ጋዜጠኞችን ያፈኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።ዓለም አቀፎቹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ሲፒጄና ኤር ኤስ ኤፍ እስሩን አውግዘው ጋዜጠኞ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።  
ሚክያስ በፌስቡክ «ዘንድሮማ መንግስት እስር ቤት ውስጥ የሆነ የስርጭት ጣቢያ ካላቋቋመ ምን አተረፈ።»ሲሉ  ተሳልቋል። ሰላም ኢትዮጵያ እስሩን ተቃውመው መሪዎች ሊያስተካክሉ የሚገባቸው ያሉትን በፌስቡክ  ጠቁመዋል። 
«ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ፣ በሀሳብ የሚሞግቷቸውን ወደ እስር ቤት መወርወር ማሸነፊያቸው ብቸኛው መንገድ መሆኑ ነው ያሉት ሰላም  ትክክለኛ መሪ የህዝብን ልብ መግዛት የሚቻለው የሚተቹትንና በሀሳብ የሚበልጡትን በማሠር ሳይሆን የሚተቹበትን ሰርቶ በማሳየት እና የተሻለ ሀሳብ አምጥቶ ህዝብን በጉልበት ሳይሆን በተግባር በመሳብ ማሸነፍ ሲችል ብቻ ነው ብለዋል። 
ዳውድ ሀሰን «ጋዜጠኝነት ከወንጀል መደበቂያ ዋሻ አይደለም ።ማንኛውም ሰው ወንጀል ከሰራ ይጠየቃል ነብይ እንኳ ቢሆን ።»ሲሉ መሳይ አምባው ደግሞ «እኔ ያልገባኝ በተደጋጋሚ በአስቸኳይ እንድፈቱ ከማለት ውጭ በአፋኙ ላይ የሚወሰድ እርምጃ ምንድነው፡፡ ሲሉ ጠይቀዋል። ገና ይታያል በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ለአጠቃላዩ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል የሚል ሀሳብ ይዟል። «የሀገራችን መሪዎች ህዝብን ማሰር ሳይሆን ማፈን በምትባል ነገር ተጠምደዋል ማሰር መፍትፍሄ ሳይሆን ህዝባዊ አመፅን ይወልዳል::ታላቁ መፍትሄ ማሰር ሳይሆን ቀርቦ መወያየት ነዉ ብየ አምናለሁ የማይቀርብ ካለ በየሁሉም የእምነት አባቾች በኩል መላክና እንዲወያዩ ማድረግ በዉይይቱም እኔን ብቻ ስሙኝ አለማለት የሌሎችን ሀሳብ በሚገባ ማዳመጥ ከተቻለም አጥጋቢ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል ብየ አስባለሁ ሲሉ ሀሳባቸውን  ደምድመዋል። :: 
«በፍጥነት የክስ ሂደቱን ማካሄድ እና ንጹሁና አጥፊውን ቶሎ ለይቶ መልቀቅ ኑሩ ይስሀቅ መፍትሄ ያሉት ነው።
ሚኒበል ደረሰም የበኩላቸውን መፍትሄ ጠቁመዋል። 
«ህዝቡን ማዋከቡን ማስሩን ይተውት እና ራሳቸውን ያፅዱ በትክክል ህዝቡን ያድምጡ ህዝብ ሁሌም አይሳሳትም ስለዚህ ወታደራዊ አፈናን አሁኑኑ ያቁሙ የታፈኑትንም ይለቀቁ ህዝቡ አምሮል የኑሮ ዉድነቱ ሞቱ ጀምላ እስሩ በቃ በማለት።
በቀድሞ መጠሪያው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በአሁኑ  መጠሪያው የአፍሪቃ ኅብረት በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 25 ቀን 1963 ዓም  ነው የተመሰረተው።ድርጅቱ ከዛሬ 20 ዓመት አንስቶ ስያሜውን ወደ አፍሪቃ ኅብረት ቀይሯል። የምስረታው እለት የአፍሪቃ ቀን በመባል በየዓመቱ ይታሰባል። ዘንድሮም የአፍሪቃ ቀን በአፍሪቃ ኅብረት አባል ሀገራት ከትናንት በስተያ ታስቦ ውሏል። በዚህ ሳምንት መጨረሻ የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች በአህጉሪቱ አሉታዊ ተፅዕኖ በሚያሳድሩት በሽብርተኝነት እና በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ላይ ለመወያየት በኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ ማላቦ ነገና ተነገ ወዲያ ልዩ ጉባኤ ያካሂዳሉ። የአፍሪቃ ቀን በታሰበበት ረቡዕ  ዶቼቬለ ለፊስ ቡክ ተከታዮቹ ለአፍሪቃዉያኑ መሪዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎ ሲል ላቀረበው ጥያቄ በርካታ ተከታዮቻችን ሃሳባቸውን አካፍለውናል። ከመካከላቸው አንዱ የላመስግነው ተካ ነው። «ጥሩ መሪ ሆኑ»ይላል።ሞሐመድ ኑርሁሴን መሀመድ ጦርነት ይብቃን ሲል ጉዲሳ አም « ህዝባችሁን አትግደሉ፣ አታፍኑ ፣አታስደፍሩ፣ አትዝረፉ ፣በቂም አትሰሩ፣አትሰውሩ፣ ..ሰራዊታችሁንም በአግባቡ ያዙ፣ ተጠቅማችሁበት አትጣሉ ህዝብ ዘላላማዊ ፣ስልጣን ጊዜያዊ ነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።  
«በመንግሥት የሚመራ ሙስናን እንቀንስ ዘላቂ ልማት እናስፍን ያሉት ደግሞ ተሰማ ነጋሽ መሰለ ናቸው። 
ወርቁ ወርቁ ደግሞ «እንኳን አደረሳችሁ ባለአደራ ናችሁና አደራችሁን በታማኝነትና በፍቅር ተወጡ የሰጣችሁ እርሱ ይጠይቃችኋልና በተረፈ ለበረከት ሁኑ።
ስዩም ደግሞ «ለአፍሪቃ አምባገነኖች በሙሉ! ጥላቻው ያልፋል፣አምባገነኖች ይሞታሉ፣ከህዝቡ የነጠቁት ስልጣን ለህዝቡ ይመለሳል።» በሏቸው መስሚያ ጆሮ ካላቸው ብለዋል።
አብርሽ ከወልዲያ መሪዎቹ ከአደራ ጋር የሚከተሉትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
እንደ አለቃ ሳይሆን እንደ መሪ ይሁኑ። ስልጣናቸውን ህዝብን ለማገልገል እንጅ ህዝብን ለማግለል ና ለማጋደል አይጠቀሙበት።
 የነጭ ተላላኪነት ና ተገዥነታቸውን ያቁሙ።  ልክ እንደ NATO አይነት ጠንካራ ለአህጉሪቷ ጥቅም የቆመ የጦር ግምባር ይፍጠሩ።አህጉር አቀፍ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የእርስበርስ የንግድ ትስስር ይፍጠሩ። በምንም በምንም ብለው ሰላም የሰፈነባት ከነጮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነች የበለፀገች አፍሪካን ገንብተው ለመጪው ትውልድ እንዲያስረክቡ አደራ እላለሁ።»

Äthiopien | AU Gipfel in Addis Abeba
ምስል Shadi Hatem/APA Images/ZUMAPRESS/picture alliance
Äthiopien Addis Abeba |  Tefera Mamo
ምስል Solomon Muchie/DW

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ