የገንደውሐው ግድያ እና የእነ ጫልቱ እስር | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 11.01.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የገንደውሐው ግድያ እና የእነ ጫልቱ እስር

በሳምንቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዋንኛ መነጋገሪያ ርዕሰ-ጉዳይ ሆኗል። ከሁለት ቀናት በፊት በምዕራብ ጎንደር ዞን የጦሩ አባላት በተኮሱት ጥይት በርከት ያሉ ሰዎች መገደላቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘንድ ቁጣ እና ሐዘን አጭሯል። ለሶስተኛ ጊዜ ከቤተሰቦቿ መኖሪያ ቤት ተወስዳ የታሰረችው የጫልቱ ታከለ ጉዳይም መነጋገሪያ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:11

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በምዕራብ ጎንደር ዞን በገንደውሐ ከተማ እና ኮኪት በተባለ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ተኩስ ከፍተው በርከት ያሉ ሰዎች መገደላቸው እና መቁሰላቸው ከተሰማ በኋላ በበርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የቁጣ እና የሐዘን ስሜት ያዘሉ መልዕክቶች በስፋት ታይተዋል። አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለDW እንደተናገሩት ባለፈው ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ዘጠኝ ሰዎች የተገደሉበትን እና 15 ሰዎች የቆሰሉበትን ተኩስ በመቃወም በገንደውሐ ከተማ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተኩስ የከፈቱት ሱር የተባለው የግንባታ ኩባንያ ንብረት ናቸው የተባሉ ተሽከርካሪዎች ከአካባቢው መንቀሳቀሳቸውን በተቃወሙ ነዋሪዎች ላይ መሆኑን የአይን ዕማኞች ተናግረዋል። በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የሟቾች ቁጥር 15 ደርሷል የሚሉ መረጃዎችም ሲዘዋወሩ ታይተዋል። ነገር ግን የቁጥሩን ትክክለኛነት ከዐይን እማኞች፣ ከሆስፒታል የመረጃ ምንጮች አሊያም ከክልሉ ባለሥልጣናት ያረጋገጠ አልተገኘም።

መታፈሪያ አስራት በየነ "የዛ ጦር አዛዦችና በሰላማዊ ተቃውሞ ላይ ተኩስ የከፈቱት ወታደሮች ለህግ ይቅረቡ። በሐገራችን ውስጥ አንዱ የእንጀራ ልጅ ሌላው ልጅ ሊሆን አይችልም። መከላከያ የተንሸዋረረ አይኑ ይመርመር" ሲሉ ድርጊቱ እንዳስቆጣቸው ገልጸዋል። ጃሕ ጆብ ጆቪች በበኩላቸው "የዶክተር አብይ ትልቁ ጠላት መከላከያው ነው ።ከዚህ በኋላ ዜጎቻችንን አንገልም ብሎ በተናገረ ሳምንት ሳይሞላ ከ15 ሰው በላይ በአማራ ክልል በመከላከያ ተገድሏል። ገዳይ መከላከያ ሰራዊቶች ተይዘው ለማስተማሪያ ተገቢውን ፍርድ ማግኘት አለባቸው። ፍትህ ለሞቱት" የሚል አስተያየት አስፍረዋል።

እንዲህ በርካቶችን ያስቆጣ እንዲሁም ያሳዘነ ድርጊት ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሌላ አወዛጋቢ ጉዳይ ገጥሞት ነበር። በትግራይ ክልል ከሚገኙ የጦር ሰፈሮች ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ለማንቀሳቀስ የሞከረው ሰራዊቱ ዕቅዱ በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ሳይሳካለት ቀርቷል። በወቅቱ የገጠመውን ተቃውሞ በትዕግስት ያለፈው ጦሩ በአማራ ክልል ወስዶታል የተባለው እርምጃ ግን ትዝብት ላይ ጥሎታል። ትዛዙ መለስ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "የመከላከያ መሳሪያ አማራ ላይ ይሰራል። ነገር ግን ሽሬ ላይ ይታገታል፤ወለጋ ላይ ደጋግሞ ይታገሳል፤ በጣም ያሳፍራል ፡፡ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ኢሕአዴግ መቼ ነው የሚለወጠው? ደግሞ ይህን ስል ትግራይ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ሰው ይገደል ማለቴ አይደለም። ሁሉንም መታገስ ሁሉንም በእኩልነት ማስተዳደር ማለቴ ነው" የሚል ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ብሩክ ሚካኤል በበኩላቸው "አብዛኛው 'ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ' በሱር ኮንስትራክሽን ግጭት ለተገደሉት ሰዎች ተቃውሞውን እያቀረበ ያለው መከላከያው ሽሬ ላይ እንዴት ሳይተኩስ ቀሩ የሚል ጥያቄ አንስቶ ነው። እኔ እንደ አንድ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ መከላከያው ሽሬ ላይ ባለመተኮሱ አመሰግነዋለው ። ተጨማሪ ህይወት ከመቅጠፍ እራሱን ስላቀበ ። መከላከያውን መጠየቅ ካለበት እዛው ስህተት በሰራበት ቦታ ብቻ እንጂ ወደ ኃላ ሄዶ ጥሩ የሰራበትን ቦታ እየጠቀሱ እዚህ ከተኮሰ እዛ መተኮስ ነበረበት የሚል የደከመ አመክንዮ የሚከተል ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ በተገኘበት ቢኮረኮም ደስ ይለኛል'' ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን የኮምዩንኬሽን ፅህፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለዜጎች ደህንነት ዋስትና መሆን ሲገባው ለዜጎች ስጋት መሆን የለበትም፡፡ ሌላ ተልእኮ ካልኖረ በስተቀር ህዝብ ተወያይቶ መፍትሄ እስኪሰጥ ድረስ እንዴት መታገስ ያቅታል?" የሚል አስተያየት አስፍሯል። ጽህፈት ቤቱ  "ድርጊቱ በጣም ስህተትና አጸያፊ ስለሆነ አዴፓ የሚመራው የክልሉና የፌድራሉ መንግስት በጋራ በመሆን አጥፊዎችን በአስቸኳይ አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እናሳስባለን" ሲል ቆንጠጥ ያለ አስተያየት አስፍሯል።

ሚሊዮን ሐይለሚካኤል "በምንም መመዘኛ እና መስፈርት መከላከያ ምዕራብ ጎንደር ላይ የፈጸመው ድርጊት ተቀባይነት የለውም፡፡ በጣም ያማልም ያሳዝናልም፡፡ ነገር ግን ነገሩን በጣም አሳዛኝ የሚያደርገው አንዳንድ ወዳጆች የንጹሃኑን ሞት ለራሳቸው የፖለቲካ ፍጆታ ሲያውሉ መመልከቱ ነው፡፡ የአንድ ምስኪን ልጅ ሞትን የፖለቲካን ትርፍ አስልቶ መነገጃ ማድረግ አሳፋሪ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰብዓዊነት ይቅደም ሌላው ሁሉ ከዛ በኋላ የሚመጣ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ሐሰን መሐመድ "መከላከያው የገደለው አማራ ስለሆኑ ነው ፣ አማራው በትክክለኛ ልጆቹ መመራት ካልጀመረ እናም በአማራነቱ ካልተደራጀ ፣የዚህ አይነት ዜና ነገም እንደምንሰማ እርግጠኛ ነኝ ። መንግስት ተብየው ለአማራ ቦታ የለውም" ብለዋል።

"አዴፓ የአማራን ሕዝብ ኅልውና አስጠብቅ። ጥያቄውንም መልስ። ወይንም ቦታውን ለአብን ልቀቅ" የሚል መፈክር በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲዘዋወር ታይቷል።

ጉዳዩ ከመክረሩ የተነሳ አድማ እንዲደረግ የተላለፉ ጥሪዎች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ታይተዋል። መሳፍንት ባዘዘው እምቢተኛው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "በመጪው ሰኞ በትምህርት ማቆም አድማ ይጀመራል" የሚል መልዕክት አጋርተዋል። መሳፍንት "ቀጥለን ወደ ተቀናጀ አመፅ እንገባለን" ሲሉም አክለዋል። የተለያዩ የማኅበራዊ ገፅ ተጠቃሚዎች ከአድማው ሐሳብ ጋር አያይዘው ከሚያሰራጯቸው ጥያቄዎች "መካከል መከላከያ ሰራዊት በአስቸኳይ ከአማራ ምድር ለቆ ይውጣ" የሚለው ይገኝበታል።

የአድማ ሐሳቡ ግን በፌስቡክ መንደር ነቀፋ አላጣውም። የሰው ወንድም ማሙዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "አሁንም አክቲቪስቶች ተረጋግቶ ማሰቡ ይቀላል! ሕዝብን ከድጡ ወደ ማጡ ለመውሰድ የሚተጋ ማንኛውም አካል ከድርጊቱ  መቆጠብ ይኖርበታል" የሚል መልክዕታቸውን በግል ገፃቸው አካፍለዋል።  የሰው ወንድም "እሳት በነደድ ቁጥር አብረን የምናነድ ከሆነ ለህዝባችን መፍትሄ ሳይሆን የባሰ ቀውስ ያመጣል!። አድማ መጥራቱ ማንን እየጎዳ እንደሆን የተረዳን አይመስለኝም። ከስሜታዊነት ወጥተን በተቻለን መጠን እየተደጋገፍን የምንሰራበት መስመር ቢኖርና ዘለቄታዊ በሆኑ መፍትሄዎች ላይ ትኩረት ቢሰጡ የተሻለ ይሆናል" ብለዋል።  ከድር እንድሪስ የተባሉ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው "በሞቱት ወገኖቻችን ደም ቁማር ይቁም። ምንም አይነት አድማ የሚባል የለም። ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት እና ጥያቄ እንጂ ለፖለቲካ ቁማርተኞች ተብሎ የሚደርግ አድማ የለም" ሲሉ ጠጠር ያለ መልክዕት አስተላልፈዋል።

የእነ ጫልቱ እስር

ጫልቱ ታከለ እንደገና ታስራለች። ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለሁለት ጊዜ ታስራ የተፈታችው ጫልቱ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሻምቡ ከተማ ከሚገኘው የቤተሰቦቿ መኖሪያ ቤት በጸጥታ ኃይሎች መወሰዷን የቅርብ ሰዎች ለDW ተናግረዋል። በምዕራብ አሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለመከላከል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እንዳስታወቀው በሰዎች ሞት እና መፈናቀል የተጠረጠሩ 171 ግለሰቦች የሆሮ ጉድሩ ዞንን ጨምሮ በምዕራብ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር አውሏል።

የኦሮሚያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተለው ገረሱ ቱፋ "ለረጅም ጊዜ በእስር ሲሰቃዩ የነበሩ እንደነ ጫልቱ ታከለ ዓይነት ሰዎችን ምክንያቱ ባልተበራራ ሁኔታ ማሰሩ ያለው የለውጥ ተስፋ ላይ መጥፎ ጥላ ያጠላል። ስለዚህ መንግስት በፍጥነት የእርምት አርምጃ መወሰድ ይጠበቅበታል"ብሏል።

አፈንዲ ሙተቂ "ይህቺ ልጅ በሐሰት ክስ ለታሰረችባችው ዓመታት ካሳ ሊከፈላት ይገባ ነበር። እርሷን ማሰር የግፍ ግፍ ነው" ሲል ተቃውሞውን በፌስቡክ ገጹ አጋርቷል። አፈንዲ ለጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መሥተዳር አቶ ለማ መገርሳ ያስተላለፈው መልዕክትም አለ።  አፈንዲ ሁለቱን መሪዎች በስም ጠቅሶ "ከዚህ በኋላ አንድም የኦሮሞ ልጅ በኦነግ ስም አይታሰርም" ብላችሁ ቃል ገብታችሁ አልነበረምን? ይኸውና በርካታ የኦሮሞ ልጆች "የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች ናችሁ" ተብለው እየታሰሩ ነው። የሚገርመው ነገር ጫልቱ በሶሻል ሚዲያ ተሳትፎዋ በጣም ቁጥብ፣ ሰላም ፈላጊ እና moderate ከሚባሉ ሰዎች አንዷ መሆኗ ነው» ብሏል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic