1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጅማ ሆስፒታል መድኃኒት አቅርቦት ፈተናና የሐኪሞች ክፍያ ጥያቄ

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2016

በጅማ ሆስፒታል በተከሰተው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር የህክምና ሂደቱን ባግባቡ ለመከወን ፈተና እያሆነ ነው ሲሉ ተገልጋዮችና ሐኪሞች ተናገሩ ። በተለይም ሐኪም ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገኘው መድኃኒት ቤት ከተወሰኑት ውጪ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ተገልጋዮች ዋጋው እጅግ ከፍተኛ በሆነ ከውጪ መድኃኒት ለመግዛት ይገደዳሉ ተብሏል ።

https://p.dw.com/p/4dzDE
Äthiopien  Jimma Hospital
ምስል Seyoum Getu/DW

የመድኃኒት እጥረት እና የሚያሳድረው ተፅእኖ

በጅማ ሆስፒታል በተከሰተው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር የህክምና ሂደቱን ባግባቡ ለመከወን ፈተና እያሆነ ነው ሲሉ ተገልጋዮችና ሐኪሞች ተናገሩ ። በተለይም ሐኪም ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገኘው መድኃኒት ቤት ከተወሰኑት ውጪ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ተገልጋዮች ዋጋው እጅግ ከፍተኛ በሆነ ከውጪ መድኃኒት ለመግዛት ይገደዳሉ ተብሏል ። የኃኪሞች የጥቅማጥቅም ክፍያ መዘግየትም ሌላው ፈተና መሆኑን ሠራተኞቹ አስረድተዋል ።

ከባድ የመኪና አደጋ የደረሰበትን ወንድማቸውን በጅማ ሪፌራል ሆስፒታል አሳክመው እየወጡ ያሉት አስተያየት ሰጪ የሆስፒታሉ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከሚገኘው መድኃኒት ቤት የታዘዘላቸውን መድሃኒት በማጣታቸው ወደ ውጪ ወጥተው ለመግዛት መገደዳቸውን ያስረዳሉ፡፡ "ከባድ አደጋ ነበር የደረሰበት፡፡ ጥሩ ህክምና አግኝተን ተስፋ ይዘን እየወጣን ነው አሁን፡፡ ከዋጋ አንጻር በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገኘው የሆስፒታሉ መድኃኒት ቤት በእጅጉ የተሻለ ቢሆንም የለም ስለምንባል ከውጪ ነው ታዞ የምንገዛው” ሲሉም ሃሳባቸውን ዘርዝረዋል፡፡

ሌላኛዋ የሆስፒታሉ ተገልጋይ ልጃቸውን አሳክመው እየወጡ መሆኑን በማስረዳት አሁንም መድሃኒቱን ግን ከውጪ ለመግዛት መገደዳቸውን ገልጸውልናል፡፡ "ልጄ ትምህርት ቤት ከልጆች ጋር ተጣልቶ መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ አሳክመው እየወጣሁ ነው፡፡ ግን መድሃኒት ከውጪ ለመግዛት ለገድጃለሁ” ብለዋል፡፡

የመድኃኒት እጥረት እና የሚያሳድረው ተፅእኖ

በሆስፒታሉ የሚያገለግሉና ማንነታቸው ግን እንዳገለጽ የጠየቁን አንዲት የሆስፒታሊ ሓኪም እንደሚሉት በሆስፒታሉ መድሃኒት ቤት ውስጥ የተከሰተው  የመድሃኒት እጥረት በህክምና አሰጣጡም ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ በርካታ ለመድሃኒት ግዢ አቅሙ የሌላቸውም ታካሚዎች እጅግ ልዩነት ባለው ውድ ዋጋ መድሃኒት ከውጪ ለመግዛት እንደሚገደዱም በማንሳት ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ "ጊቢው ውስጥ የመድሃኒት እጥረት ማጋጠሙ ሃኪሞች የሚሰጡትን አገልግሎት ያስተጓጉላል፡፡ ብዙ መድሃኒት ከጊቢው መድሃኒት ቤት ለምን ጠፋ ለምለው ብዙም እውቀት ባይኖረኝም አብዛኛው ለህክምና መገልገያ የሚውሉ መድሃኒቶች ግን ከውጪ እንደሚገዙ ነው የማውቀው፡፡ ጊቢ ውስጥ ብዙም የመድሃኒት አቅርቦቱ የሉም፡፡ ፋርማሲዎች ብኖሩም ባዶያቸውን ነው የቆሙት” በማለት አማረው ነው አስተያየታቸውን ያጋሩን፡፡

የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ተገልጋዮች ዋጋው እጅግ ከፍተኛ በሆነ ከውጪ መድኃኒት ለመግዛት ይገደዳሉ ተብሏል
ጅማ ሆስፒታል የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ተገልጋዮች ዋጋው እጅግ ከፍተኛ በሆነ ከውጪ መድኃኒት ለመግዛት ይገደዳሉ ተብሏል ምስል Seyoum Getu/DW

የጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ፈተና

እንደ አስተያየት ሰጪዋ የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍል በዚህ ለከፍተኛ ችግር ስለሚዳረጉ የህክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ይፈተናሉ፡፡ "ሆስፒታሉ የሪፌራል ሆስፒታል እንደመሆኑ አብዛኛው ተገልጋዮቹ የሚመጡት ከወረዳዎች ነው፡፡ እነዚህ ተገልጋዮች በብዛት ሙሉ የጤና መድህን ተጠቃሚ ናቸው፡፡ መድሃኒት ሆስፒታል ውስጥ የሚሸጠው በዚያው መሰረት ቢሆንም ከውጪ መድሃት ለመግዛት የሚገደዱት ደግሞ እጅግ ጭማሪ ባለውና ከአቅማቸው በላይ በሆነ ወጪ ነው፡፡ ምክኒያቱም አሁን የመድሃኒት ዋጋ በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ይህ ላላሰቡትና ከአቅማቸው በላይ ለሆነ የህክምና ወጪ ነው የሚዳርጋቸው” ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡ የሆስፒታሉ ነርስ  የመድኃኒት እጥረቱ የህክምና አሰጣጡን ሥራ እንደሚጎዳ ገልጸዋል፡፡ "አብዛኛው ተገልጋይ የጤና መድህን ተጠቃሚ ቢሆንም ምንም አይነት መድሃኒት በሆስፒታሉ አያገኙም፡፡ ይህ ደግሞ ከ20 በመቶ የበለጠ አገልግሎት እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆናል” ነው ያሉት፡፡

የሐኪሞች ጥቅማጥቅም ክፍያ መዘግየት መዘዙ

ጅማ ሆስፒታል የመድኃኒት እጥረቱ የህክምና አሰጣጡን ሥራ እንደሚጎዳ ባለሞያዎች ገልጸዋል
ጅማ ሆስፒታል የመድኃኒት እጥረቱ የህክምና አሰጣጡን ሥራ እንደሚጎዳ ባለሞያዎች ገልጸዋል ምስል Seyoum Getu/DW

አስተያየታቸውን የሰጡን የህክምና ባለሙያዎቹ ከመድሃኒት አቅርቦት እጥረቱ በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎቹ የደሞዝ ጥቅማጥቅም በወቅቱ አለመከፈልና እጅግ መዘግየት አገልግሎቱን ከሚያዉኩ ሌላው ክስተት ነው ይላሉ፡፡ "ለህክምና ባለሙያዎቹ ለአዳር የሚከፈል ክፍያ አለ፡፡ ይህ ክፍያ በአግባቡ እየተከፈለ አይደለም፡፡ እስከ ስድስት ወር ይዘገያል፡፡ ይህ ሰራተኞች ላይ ጥሩ ስሜት ባለመፍጠሩ ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራሉ” ነው ያሉት፡፡ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ነርስ ሃሳባቸውን ቀጠሉ "አሁንበቀደም ነው የሁለት ወር የተከፈለን፡፡ ሆኖም አሁንም የአራት ወር ክፍያ አልተከፈለንም፡፡ በዚህ ደስተኛ ያልሆነ ሃኪም ታካሚውንም ከልቡ ለማገልገል አስቸጋሪ ነው የሚሆንበት” በማለት የችግሩን ስፋት አስረድተዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ በሆስፒታሉ አጋጥሟል ስለተባለው  የመድሃኒት እጥረት  እና የሃኪሞች ቅሬታን ይዞ ወደ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ብደውልም ከዚህ በፊት ለሌሎች ሚዲያ ከሰጠሁት ሃሳብ ሌላ የሚለው የለም ብለው ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ ከሰሞኑ ሃላፊውን ጠቅሶ እንደዘገበው የዩኒቨርሲቲው በጀት በ50 በመቶ መቀነስ ችግሮቹ እንዲከሰቱ ምክኒያት ናቸው፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ