የጀርመን ውህደት እና ውጤቱ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ውህደት እና ውጤቱ

የጀርመን ውህደት የጀርመን ኤኮኖሚ ከአውሮጳ የመሪነቱን ቦታ እንዲይዝ አስተዋጽኦ በማድረግ ይወደሳል በአንጻሩ ከ27 ዓመት በኋላም ዛሬም በቀድሞዋ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘታቸው ማነጋገሩ ቀጥሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:22
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:22 ደቂቃ

የጀርመን ውህደት

ጀርመን ዳግም የተዋሀደችበት 27ተኛ ዓመት ዛሬ ተከብሯል። ጀርመንን ለሁለት ከፍሎ የቆየው ግንብ በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 1961 ነበር የተገነባው። ምሥራቅ ጀርመን የጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ምዕራብ ጀርመን ደግሞ የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ሆነው ተነጣጥለው የቆዩት ለ28 ዓመትት ነው።

በጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 3፣ 1990 ደግሞ ውህደቱ እውን ሆነ። ላልተጠበቀው ውህደት መፋጠን በጎርጎሮሳዊው ህዳር 9 1989 ሁለቱን አገሮች ለያይቶ የቆየው ግንብ መፍረሱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ጀርመንን ለሁለት የከፈለው ግንብ ከመፍረሱ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር የነጻ ትምሕርት እድል አግኝተው ምሥራቅ ጀርመን የመጡት። የጀርመንኛ ቋንቋ እና ከትምህርታቸው የተወሰነውን ስቪካው በተባለችው የምስራቅ ጀርመን ከተማ ከተከታተሉ በኋላ ለቀጣይ ትምሕርት ምዕራብ ጀርመን በርሊን ሄደው እዚያው በርሊን የተማሩ እና ና የሚሠሩ የምጣኔ ሐብት ምሁር ናቸው። የግንቡን መፍረስ ቅጽበታዊ ይሉታል።  በወቅቱ የምሥራቅ እና ምዕራብ ጀርመን የኑሮ ደረጃ ልዩነት የሰፋ እንደነበረ የሚናገሩት ዶክተር ፀጋዮ ያኔ ኢትዮጵያ የነበሩ ሸቀጦች እንኳን ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ ብርቅ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። 

የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል ጀርመን ሲኖር 47 ዓመት ሊጠጋው ነው። ጀርመንን ለሁለት የገመሰው ግንብ እያለ 20 ዓመታት ፣ከተዋሀዱም በኋላ ላለፉት 27 ዓመታት መጀመሪያ በመጣበት በምዕራብ በርሊን ነው የኖረው እና አሁንም የሚኖረው። በወጣትነቱ ለትምሕርት ምዕራብ በርሊን መጥቶ ኑሮውን እዚሁ ያደረገው ይልማ በሁለቱ ሀገራት አስተዳደር ውስጥ የነበረው ልዩነት እጅግ ሰፊ ነበር ይላል።

አቶ ስዩም ሙሉጌታ ጀርመን መኖር ከጀመሩ 37 ዓመታት ተቆጥረዋል። ግንቡ ሳይፈርስ ምዕራብ በርሊን የነበሩት አቶ ስዩም ምሥራቅ በርሊን ይሄዱም ነበር። ያኔ የውጭ ዜጎች ጥላቻ እምባዛም ነበር ይላሉ ። ውህደቱ የጀርመን ኤኮኖሚ ከአውሮጳ የአንደኝነቱን ደረጃ እንዲይዝ አስተዋጽኦ አድርጓል። በአንጻሩ ከ27 ዓመት በኋላም ዛሬም በቀድሞዋ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ አላገኙም።

በምሥራቅ ጀርመን የሚፈለገውን እድገት በተጠበቀው መጠን እና ጊዜ ማምጣት ባለመቻሉ ሥራ አጥነት ዐብይ ችግር ነው። ይህ እና ሌሎችም የማህበራዊ ፍትህ ጉድለቶች ብዙዎች ከምሥራቁ ክፍል ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዲፈልሱ አድረጓል።በዚህ ሰበብ አንዳንድ ከተሞች ወጣት አልባ እስከመሆን መድረሳቸውን ዶክተር ፀጋዮ ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ በጡረታ ላይ የሚገኙት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ስዩም ቀድሞ ያን ያህል የነበረው የውጭ ዜጎች ጥላቻ ከውህደቱ በኋላ ተባብሷል ይላሉ። 

ዶክተር ፀጋዮም ዘረኝነት ከውህደቱ በኋላ በምሥራቁ ክፍል የተባባሰው እነርሱን መጠቀሚያ ባደረጉ ምዕራብ ጀርመን ኃይሎች አማካኝነት መሆኑን ያስረዳሉ። ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ የጀርመን ምክር ቤት ለመግባት የሚያስችል ድምጽ ማግኘቱ ብዙዎችን አሳስቧል። ይህ ከሚያሳስባቸው አንዱ ዶክተር ፀጋዮ ናቸው። እንደ አቶ ስዩም ግን አሁን በጀርመን ዘረኝነት እንደገና ቢያቋጠቁጥም እንደ ጠዋት ዜዛ መጥፋቱ አይቀርም ይላሉ።

 ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic