የዶክተር ነጋሶ አስከሬን ሽኝት | ኢትዮጵያ | DW | 03.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የዶክተር ነጋሶ አስከሬን ሽኝት

የመንፈስ ጽናት በኩራት በአደባባይ መስክረዋል። ወይዘሮ ሬጂና ኢትዮጵያ ውስጥም በሙያቸው በህመም እና በምጥ የሚሰቃዩ በርካታ ችግረኛ ወገኖችን በመርዳት ታላቅ አገልግሎት ማበርከታቸውን በቅርበት የሚያውቋቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸው ያስረዳሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:54

የዶክተር ነጋሶ ሽኝት

                               
ባለፈው ቅዳሜ ፍራንክፈርት ዛክዘን ሃውሰን ሆስፒታል ዉስጥ በሕክምና ላይ እያሉ ያረፉት የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት የነጋሶ ጊዳዳ አስክሬን ዛሬ ወደ አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ ተሸኘ።አስከሬኑ ከመሸኘቱ በፊት ፍራንክፈርት በሚገኘዉ የካቶሊክ የሱስ ክርሽየ ቤተ ክርስቲያን ፀሎትና ሟቹ ጀርመን በነበሩበት ዘመን ያከናወኗቸዉን ምግባራት የሚዘክሩ ንግሮች ተደርገዋል።በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባለቤት ሬጊና አልበል፣ ልጆቻቸዉ ኢብሳና ጃለኔ ነጋሶ፣ ሌሎች የቤተሰቦቻቸዉ አባላት፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለስልጣናት፣ የካቶሊክ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶና የመካነየሱስ አብያተ ክርስቲያናት ተጠሪዎችና መንፈሳዊ አባቶች  ተገኝተዋል።የፍራንክፈርቱ ወኪላችን እንዳልካቸዉ ፈቃደ የሽኝትና የፀሎት ሥርዓቱን ተከታትሎታል።
 በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን  " ዶክተር ነጋሶ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ በእግራቸው እና በታክሲ ሲሄዱ አስታውሳለሁ:: ዕውነትን መከተል ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል አስተምረውን ያለፉ ታላቅ ሰው ናቸው " ብለዋል::
ስልጣን ለህዝብ አገልግሎት መዋል አለበት የሚል ዕምነትን  ጨምሮ ለፍትህና ለመርህ መገዛትን ጽኑ ዓላማቸው ያደረጉት ዶክተር ነጋሶ እንደ ጎሮሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ 2001 ዓ.ም የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ አያሌ የሕይወት ፈተና እንደገጠማቸው በሕይወት በነበሩበት ወቅት ተናግረዋል ::ከሽግግር መንግሥቱ  ወቅት ጀምሮ አገሪቱን በተለያየ የመንግሥት ኃላፊነትና በርዕሰ ብሄርነት ለበርካታ ዓመታት ማገልገላቸው ቢታወቅም ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በፖለቲካ የአስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት በተፈጠረው ውዝግብና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማምጣት ከተቃውሞ የፖለቲካ ጎራ ጎን  በመሰለፋቸው ምክንያት ማግኘት የሚገባቸው ጥቅማጠቅም እንዲቋረጥ ብሎም ከሚኖሩበት የመንግሥት ቤት ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ የኃይል ሙከራ እንደተደረገባቸውም ራሳቸው የደረሰባቸውን በደል በተለያዩ መድረኮች በአንደበታቸው ሲገልጹ ቆይተዋል::

ለረጅም ዘመን የሚሰቃዩበትን የልብ ህመም ጨምሮ የገጠማቸውን የጤና ዕክል በውጭ አገራት ወተው ለመታከም ከባድ ፈተና ገጥሟቸው እንደነበረም ዶክተሩም ሆኑ ወዳጆቻቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ የቆዩት ጉዳይ ነው:: በዚህ ሁሉ ፈተና ግን ከ 30 ዓመታት በላይ በትዳር አብረዋቸው የቆዩት ጀረመናዊቷ አዋላጅ ነርስ የህክምና ባለሙያ ባለቤታቸው " ኢትዮጵያ ውስጥ ካንተው ጋር እሞታለሁ እንጂ ጥዬህ የትም አልሄድም " ማለታቸውን በማስታወስ የባለቤታቸውን የመንፈስ ጽናት በኩራት በአደባባይ መስክረዋል:: ወይዘሮ ሬጂና ኢትዮጵያ ውስጥም በሙያቸው በህመም እና በምጥ የሚሰቃዩ በርካታ ችግረኛ ወገኖችን በመርዳት ታላቅ አገልግሎት ማበርከታቸውን በቅርበት የሚያውቋቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸው ያስረዳሉ:: በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመጀመሪያዋ የውጭ ዜጋ የቀድሞዋ ቀዳማይት ዕመቤት ጀርመናዊቷ ወይዘሮ ሬጂና  አልበል  በበኩላቸው ነጋሶ አገሩን የሚወድ ሙያውን የሚያከብር እና በዛ ሁሉ ፈተና መሃል እንኳ የሚገጥመውን ውጣ ወረድ ተቋቁሞ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በአቅሙ ለመርዳት እስትንፋሱ እስካለፈችበት ቀን ድረስ ሳይሰለች የደከመ መንፈሰ ብርቱ ሰው ነበር ሲሉ የዶክተሩን ጠንካራ ሰብዕና በተለያዩ ቃለ መጠይቆች ተናግረዋል::
እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር በ 1984 ዓ.ም  በአፍሪቃዊቷ ሩዋንዳ  በጀርመን የረድኤት አገልግሎት ድርጅት ውስጥየሚያከናውኑትን ተግባር አጠናቀው ወደ ፍራንክፈርት ከተማ ሲመለሱ ከትዳር አጋራቸው ዶክተር ነጋሶ ጋር ትውውቅ የፈጠሩት "ድጋፍ ለሶስተኛው ዓለም አገርት ህዝቦች" ወይም "Das Dritte Welt" በተሰኘው ማዕከል ውስጥ እንደነበር ወይዘሮ ሬጂና ነግረውናል ::ወቅቱ ጎልማሳው ፖለቲከኛ ዶክተር ነጋሶ ጀርመናውያን ግራ ዘመም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች ፍራንክፈርት ከተማ የመሰረቱት የዚሁ የሶስተኛ ዓለም አገራት መርጃ ነጻ ማህበር ዳይሬክተር ሆነው የተመረጡበት ሲሆን ሬጂናና ሴት ጓደኛቸውም  ይህንኑ ለአፍሪቃ ላቲን አሜሪካና ለሌሎችም የሶስተኛው ዓለም ሕዝቦች መብት መከበር የሚታገል የዴሞክራቶች ገለልተኛ ማህበር ለማገልገል በመጡበት ወቅት ዶክተሩ የስራ ቱታቸውን ሰብስበው የማዕከሉን ህንጻ ቀለም እየቀቡ ሲያድሱ በማየታቸው ተደምመው ከዛች ቅጽበት ጀምሮ በሁለቱ መካከል የተጸነሰ ፍቅር ለትዳር መብቃቱን ዛሬ በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል:: " ለመላው ኢትዮጵያውያን የሃሳብ እና የዲሞክራሲ መብት መከበር በጽናት የታገለ ታላቅ ሰው ነበር " ሲሉም ፕሬዝዳንት ነጋሶ በአገሪቱ ያበረከቱትን በጎ ተግባር ጠቅሰዋል:: ዶክተር ነጋሶ በተለይም በፕሬዝዳንትነት የስልጣን ዘመናቸው አያሌ ውጣ ውረዶችን እና ፈተናዎችን ቢያሳልፉም በህይወት እስኪለዩ ድረስ በጽናት አብረዋቸው በትዳር ዘልቀዋል:: በትዳር በነበራቸው ቆይታም የአንዲት ሴት ልጅ ወላጆች ለመሆን ችለዋል :: ወይዘሮ አልበል በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ አዲሱ ገበያ በሚባለው አካባቢ በመሰረቱት እና " ሬይጂና የቤተሰብ የጤና እና ማሕበራዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል " በተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነትም ወላጅ አልባ ለሆኑ እንዲሁም ለችግረኛ ሕጻናት እና ሴቶች የጤና እና የምክር ግብረሰናይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ:: የመጀመሪያ ልጃቸው ኢብሳ ነጋሶም " ከአባቴ ጋር ብዙ ማከናወን የምንፈልጋቸው ጉዳዮችና ዕቅዶች ነበሩ :: አለመታደል ሆኖ ውጥናችንን ከግብ ሳናደርስ በህይወት ተለየን:: ዛሬ በሞቱ ብናዝንም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤተሰባችን አድርጎ ጥሎልን ስላለፈ እንጽናናለን ብሏል ::
 
ዶክተር ነጋሶ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በተማሩበት ሙያ እና በፖለቲካ ተሳትፎ የተለያዩ ግልጋሎቶችን ያበረከቱ ሲሆን  ከከፍተኛ የትምህርት ትቋም በተመረቁበት ትምህርትም የኦሮሞን ባህል፣ ታሪክ እና እሴት የሚያንፀባርቁ እና የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ጥናቶችን አካሂደዋል። በጀርመን የፍራንክፈርቱ ዮሃን ጎቴ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ እና ማህበራዊ ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ካገኙ

በኋላም በዛው በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮምኛን ቋንቋ ሰዋሰው እና ሥነልሳን ማወቅ ለሚፈልጉ ተማሪዎች ያስተማሩ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለሱም በአንትሮፓሎጂ የትምህርት ተቋምም ላይብረሪ ውስጥ ማገልገላቸውን ግለ ታሪካቸው ያስረዳል:: ባደረባቸው ህመም ከሁለት ሳምንታት በፊት በፍራንክፈርት ከተማ በህክምና የቆዩት ዶክተር ነጋሶ ባለፈው ቅዳሜ በ 76 ዓመታቸው ዛክዘን ሃውሰን በተባለ ሆስፒታል ውስጥ በልብ ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ከአስክሬን ምርመራው ውጤት ለማረጋገጥ ተችሏል:: በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ዘመናቸው ለአገሪቱ አያሌ ተግባራትን ያከናወኑ ታላቅ ሰው መሆናቸውን አውስተዋል:: በዛሬው ዕለት የጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፍራንክፈርት ቆንጽላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት እና ቤተሰቦቻቸው በፍራንክፈርት የካቶሊክ የሱስ ክርሽየ ቤተክርስቲያን ያዘጋጁት ሥነ ሥርአት እንዳበቃም አስክሬናቸው ወደ ፍራንክፈርት አውሮፕላን ማረፊያ ተሸኝቷል:: አስክሬናቸውን የያዘው አውሮፕላን ነገ ማለዳ ከንጋቱ 12 ሰዓት ኢትዮጵያ እንደሚደርስ የሽኝት መርሃግብሩ አስተባባሪዎች ገልጸዋል:: ዶክተር ነጋሶ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ:

እንዳልካቸዉ ፈቃደ

ነጋሽ መሐመድ

እሸተ በቀሌ

 

Audios and videos on the topic