1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድርቅ አደጋና የኢሰመኮ ማሳሰቢያ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 19 2014

ኢሰመኮ የፌዴራል ፣ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች መንግሥታት በአፋጣኝ ሊተገብሯቸው ይገባል ካላቸው መካከል አንዱ በመረጃና በምዝገባ ሥርዓት የታገዘ፣ አሳታፊ የሆነ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት የተዘረጋለት እንዲሁም ከፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ምላሽ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና ክትትል ማድረግ የሚለው ነው።

https://p.dw.com/p/4EgHz
Äthiopien Konsso | Wassermangel
ምስል Konso Development Association

«በድርቅ ለተጎዱት የሚሰጠዉ ርዳታና ድጋፍ መቀጠል አለበት» ኢሰመኮ

 

በድርቅ ምክንያት ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ የሚሰጠዉ ርዳታና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።የሶማሊያ፣የኦሮሚያና የደቡብ ኢትዮጵያን ክልሎችን የመታዉ ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንስሳት ገድሏል።የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሚሉት ድርቁ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለረሐብ አጋልጧል።የኢትዮጵያ መንግስት የሚቆጣጠረዉ ኢሰመኮ  በበኩሉ በተለይ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ የፌደራሉና የሁለቱ ክልሎች መንግስታት በአፋጣኝ በመረጃና በምዝገባ ሥርዓት የታገዘ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት የተዘረጋለት ፣ ከፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ድጋፍ ማድረግ አለባቸዉ።በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች ለድርቁ የሚሰጡ ምላሾች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ልዩ ፍላጎቶች ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርባቸዋልም ብሏል።

" ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ዝናብ ዘነበ ማለት ችግሮች ሁሉ በአንድ ጊዜ ተወገዱ ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል" ሲሉ አንድ የተቃሙ የሥራ ኃላፊ ተናግረዋል።የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)  በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ እና ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ከየካቲት 14 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብለው በተለያዩ አካላት በይፋ እውቅና የተሰጣቸው አካባቢዎች በመዘዋወር የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል በማድረግ ባለ 50 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። 

"በድርቁ ጉዳት ሳቢያ በተለይ በቂ ውኃና ምግብ ባለመኖሩ ሰዎች ለተለያዩ የጤና እክሎች ተዳርገዋል" የያለው የኢሰመኮ ዘገባ "የጤና ግልጋሎት መስጫ ተቋማት በአካልም በኢኮኖሚም ተደራሽ አለመሆናቸውንም ተምልክቻለሁ ፣ በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በተፈናቃይ ካምፖች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተግባራት አለመከናወኑ እና የተፈናቃዮችን ጤና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል እንደ ወረርሽኝ የመሰለ የበሽታ ተጋላጭነት እንደነበር ፣ ይህም የድርቅ ተጎጂዎችን የጤና መብት ማስጠበቅ ላይ ጉዳት አስከትሏል" ሲል ሪፖርቱ ዘርዝራል።
የደረሰው ጉዳት ቀላል የሚባል ካለመሆኑ መነሻ ምላሹም በዚያው መጠን መሆን እንደሚገባውም ተገልጿል። 

Äthiopien Somali Region | Dürre, Trockenheit | tote Tiere
ምስል Maria Gerth/DW

በኢሰመኮ የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሚዛኔ አባተ (ዶክተር) "ክትትል የተደረገባቸው ቦታዎች በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች ቢሆንም ይሄኛው የተራዘመና ከባድ ጉዳት ያስከተለ" መሆኑን ገልፀዋል።
በኢሰመኮ የጅማ ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ ከኦሮሚያ ክልል 22 ዞኖች አንዱ የሆነው ቦረና በድርቅ ከ 1983 ዓ. ም ጀምሮ እስካሁን ለ 12 ጊዜ መመታቱን ተናግረዋል። ይሁንና በወቅቱ ምላሽ ባለመሰጠቱ እና ቅድመ ጥንቃቄው የላላ መሆኑ ችግሩ ተደጋግሞ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል። 

የክትትል ሪፖርቱ በሁለቱም ክልሎች የድርቁን አደጋ ቅነሳ፣ ቅድመ-ማስጠንቀቂያና ዝግጅት እንዲሁም የማሳወቅ ሥራዎች በይፋ አለመሠራታቸው ለድርቁ አደጋ ምላሽ የዘገየ እንዲሆን ምክንያት መሆኑን ከክትትል ሪፖርቱ መረዳት ተችሏል፡፡ 

Dürre und Trockenheit am Horn von Afrika
ምስል Claire Nevill/AP Photo/picture alliance

ኢሰመኮ የፌዴራል ፣ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች መንግሥታት በአፋጣኝ ሊተገብሯቸው ይገባል ካላቸው መካከል አንዱ በመረጃና በምዝገባ ሥርዓት የታገዘ፣ አሳታፊ የሆነ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት የተዘረጋለት እንዲሁም ከፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ምላሽ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና ክትትል ማድረግ የሚለው ነው። 
ዝናብ ዘነበ ማለት ችግሩ ሁሉ ተፈታ ማለት አይደለም ሲሉ አቶ በዳሳ ለሜሴ ድጋፍ የመቀንዝ አዝማሚያ መታየቱን ጠቅሰው እርምት እንዲደረግበት ጠይቀዋል። 

ኢሰመኮ መንግሥት የድርቁን አደጋ በይፋ የማሳወቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ተጎጂዎች አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ብቻ ምሆናቸው በድርቁ ለተጎዱና አዋሳኝ አካባቢዎች የሚሰጠው ትኩረት ሊቀንስ እንደማይገባ ጥሪ አድርጓል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ