1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ክልል የዕዳ ቀዉስ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 8 2011

ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ ባሉት ጊዜያት የደቡብ ክልል መንግስት የካፒታልና መደበኛ ወጪዎችን ለመሽፈን የጥሬ ገንዘብ አጥረት አጋጥሞታል። በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ከመቀዛቀዛቸውም በላይ ከሰው ሀይል ስልጠናና ከጉዞ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የበጀት ዕቅዶችም እንዲታጠፉ ተደርጓል።

https://p.dw.com/p/3Nto0
Äthiopien Finanzkrise
ምስል DW/S. Wegayehu

የደቡብ ኢትዮጵያ የዕዳ ቀዉስና ዉዝግብ

      
የደቡብ ክልል ከ2006 ዓም ጀምሮ እስከአሁን ለእርሻ ማዳበሪያ የወሰደው የብድር ዕዳ ዛሬ ላይ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዬን ብር መድረሱ እየተነገረ ይገኛል። በየአንዳንዱ ቀን 1.8 ሚሊዮን ብር እየወለደ የሚገኘው  የብደር ዕዳ በክልሉ የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን በማስተጓጎል ብቻ የተወሰነ አልሆነም። የክልሉ ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የስራ ሃላፊዎች እንደሚሉት እዳው እየተቆለለ መምጣት ክልሉ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ ጨምሮ መደበኛ ወጪዎችን ለመሸፈን ዳገት እየሆነበት ነዉ። 

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ ባሉት ጊዜያት የደቡብ ክልል መንግስት የካፒታልና መደበኛ ወጪዎችን ለመሽፈን የጥሬ ገንዘብ አጥረት አጋጥሞታል። በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ከመቀዛቀዛቸውም በላይ ከሰው ሀይል ስልጠናና ከጉዞ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የበጀት ዕቅዶችም እንዲታጠፉ ተደርጓል። 
የክልሉ መንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ክፍያ ከወትሮው የክፍያ ጊዜ እስከ አስር  ቀናት መዘግየቱ የበጀት ጉድለቱ አካል መሆኑ ነው የሚነገረው። የደቡብ ክልል ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊና የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ አባተ በበጀት ጉድለቱ ምክንያት በክልሉ ከ2006 ዓም ጀምሮ በየምርት ዘመኑ በብደር ሲሰራጭ የነበረው የእርሻ ማዳበሪያ ዕዳ ክምችት አራት ነጥብ አምስት ቢሊዬን ብር በመድረሱ ነዉ ይላሉ። 

የክልሉ መንግስት ብድሩን ሲያሰራጭ የነበረው መደበኛ በጀቱን ዋስት በማድረግ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል የቢሮ ሃላፊው አቶ ተፈሪ ይሁንእንጂ ክልሉ ብድሩን በገባው ውል መሰረት ስብስቦ ባለመመለሱ ከፌደራሉ መንግስት ከሚያገኘው ጥቅል በጀት ላይ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ተቆርጦ ለንግድ ባንክ ገቢ መደረጉን ይናገራሉ ። የደቡብ ክልል ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊና የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተሩ አቶ ተፈሪ አባተ የዕዳው ክፍያ በክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅኖ ማሳደሩን ያረጋግጣሉ ። 

የእርሻ ማዳበሪያ ስርጭቱ በ2006 ሲጀመር የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮና የክልሉ የህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት እንዲያቀርብ ከደቡብ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የገንዘብ አቅርቦቱን እንዲያመቻች፣ የኦሞ ማይከሮ ፋይናንስ ተቋም ደግሞ የብድር ስርጭትና አስባሰቡን እንዲቆጣጠር በማቀድ መሆኑን በደቡብ ክልል ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የተዘገጀው የውል ሰነድ ይጠቁማል። 
ይሁንእንጂ በተለይ በኦሞ ማይከሮ ፋይናንስ ተቋም በኩል ያለው የብድር አስባስብ ላይ የጎላ ድክመት እንደሚታይ የሚናገሩት አቶ ተፈሪ ተመላሽ ብድሮችን የማባከንና እንደራሱ የቁጠባ ገንዘብ መልሶ የማበደር ሁኔታዎች ይስተዋላሉ ብለዋል። 

Äthiopien Finanzkrise
ምስል DW/S. Wegayehu

አቶ ደስታ ዳንጊሶ በደቡብ ክልል የህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ የግብዓትና ምርት ግብይት ዘርፍ ዳይሬክተር ናቸው ። አቶ ደስታ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በክልሉ ተመዝግቦ የሚገኘው የብድር ዕዳ በአብዛኛው በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኝ ነው። ዕዳው በየዓመቱ በመከማቸት አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ሊደርስ የቻለውም የማዳበሪያ ግበአቱን ለመውሰድ ለተመለመሉ አርሶ አደሮች ቀደምሲል የወሰዱትን ሳይመልሱ በየዓመቱ ተጨማሪ ብድር በመሰጠቱ ነው ይላሉ። 
በተወሰነ ደረጃ የተሰበሰበው ተመላሽ ዕዳም ቢሆን የብድር ሂደቱን የማስተዳደሩን ስራ የወሰደው የኦሞ ማይከሮ ፋይናንስ ተቋም የተሰበሰበውን ተመላሽ ገንዘብ ለሌላ ጉዳይ የመጠቀም ችግሮች እንደሚስተዋሉም አቶ ደስታ ይናገራሉ። 

በኦሞ ማይከሮ ፋይናንስ ተቋም የብድር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተገኝወርቅ ሰራዊት ለአርሶ አደሩ ይሰጡ የነበሩ ብድሮች ተደራራቢ መሆን ለዕዳው መከማቸት ምክንያት ሆኗል በሚለው ሀሳብ እንደሚስማሙ ይናገራሉ ። 
በብድር ላይ ተጨማሪ ብድር መስጠት አግባብ ካለመሆኑም በላይ የተቋሙ አሰራር እንደማይፈቅድ የሚናገሩት አቶ ተገኘወርቅ ይሁንእንጂ ተቋሙ ተደራራቢ ብድሮችን እንዲያስተናግድ የተለያዩ ጫናዎች ይደረጉበት ነበር ብለዋል። 

Äthiopien Finanzkrise
ምስል DW/S. Wegayehu

በኦሞ ማይከሮ ፋይናንስ ተቋም የብድር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተገኝወርቅ ሰራዊት በአሁኑወቅት በክልሉ ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የተጠቀሰው የአራት ነጥብ አምስት ቢሊዬን ብር ዕዳ የልተሸጠ ፣ በመጋዝን ተከማችቶ የሚገኝውንና ለብልሽት የተዳረገውን የእርሻ ማዳበሪያ መጠን ጭምር ያካተተ ነው ይላሉ። 
የኦሞ ማይከሮ ፋይናንስ ተቋም በቢሮው ከተጠቀሰው የዕዳ መጠን ውስጥ የመሰብሰብ ሃላፊነት ያለበት በሽያጭ ላይ የዋለውን የአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ዕዳን ብቻ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ይህንንም በህጋዊ የፋይናንስ አሰራር መሰረት ለመሰብሰብ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ ። 
ተቋሙ በብድር አመላለስ ረገድ የራሱ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ተመላሽ የማዳበሪያ ዕዳ ገንዘብን ወደ ራሱ በጀት አዙሮ እየተጠቀመበት ይገኛል የሚባለውን ግን አንደማይቀበሉት ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት ። 

በደቡብ ክልል እንደተራራ ተቆልሎ የሚገኘው የብድር ዕዳ በተቋማቱ መካከል ከፈጠረው እሰጥ አገባ ባሻገር በክልሉ መንግስት መደበኛ ወጪ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የበጀት ጉድለት እንዲያጋጥም አድርጓል። 
የክልሉ ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ምክትል ቢሮ ሃላፊና የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ አባተ አሁን ክልሉን ቀፍድዶ የያዘውን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ለማስታገስ ከቀጣዩ የ2012 የበጀት ዓመት በብድር የሚታሰብ ገንዘብ ከፌደራሉ መንግስት ተጠይቆ ምላሽ መገኘቱን ገልጸዋል። 
ከፌደራሉ መንግስት በብድር ተገኘ የተባለው የገንዘብ መጠን አሁንም የጉድለቱን ስልሳ በመቶ ያህል ብቻ የሚሸፍን ነው የሚሉት አቶ ተፈሪ በዚህም የሰራተኞች ደሞዝ ፣ የመድሃኒት ገዢና የውሃ አቅርቦትን ለመሳሰሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች ብቻ ምላሽ ለመስጠት ማስቻሉን አብራርተዋል ። 
<< >> 
ከደቡብ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው አሁን በክልሉ መንግስት ላይ የሚታየው የብድር ዕዳ መጠን እያስከተለ ከሚገኘው የበጀት ጉድለት በተጨማሪ በየቀኑ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ብር እየወለደ ይገኛል ። 
ምክትል የቢሮው ሃላፊና የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተሩ አቶ ተፈሪ አባተ በየዓመቱ እየተንከባለለ ለሚገኘው ዕዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ መደረሱን ይናገራሉ ። 
በዚህ መነሻም በአሁኑወቅት የክልሉ መንግስት ባሰቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁሉንም ባለድርሻ ተቋማት ያካተተ ቡድን ተዋቅሮ ተግባራዊ እንቀስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ምክትል የቢሮው ሃላፊ አስረድተዋል ። 
በተለይም በግለሰቦችና በተቋም ደረጃ የሚገኘውን ተሰብሳቢ የብድር ዕዳ መጠን እስከነወለዱ የመለየት ስራ መከናወኑን የጠቆሙት አቶ ተፈሪ በቅርቡም የህግ አስገዳጅነትን ጭምር በመጠቀም የዕዳ ማስመለስ ሰራዎችን ለመጀመር አስፈላጊው መሰናዶ ተጠናቋል ብለዋል ። አድማጮቻችን በደቡብ ክልል የማዳበሪያ ዕዳ ያስከተለውን የበጀት ጉድለት የተመለከትንበት የዛሬው ከኢኮኖሚው ዓለም ዝግጅታችን በዚሁ አብቅቷል በሰላም ቆዩን።
 

Äthiopien Finanzkrise
ምስል DW/S. Wegayehu

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ