1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ሆንዋል ተባለ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 2 2014

በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ትናንት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ቁጥራቸው በውል ባልታወቁ ሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ትናንት በልዩ ወረዳው ሀጠያ እና ሥለሌ በተባለ ቀበሌያት ከቀትር እስከ ምሽት በዘለቀው የተኩስ ልውውጥ ሰዎች ሞተዋል፣ የተደናገጡ ነዋሪዎችም ወደ ጫካ ሸሽተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4B6Gc
Infografik Karte Äthiopien EN

በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ትናንት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ቁጥራቸው በውል ባልታወቁ ሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ትናንት በልዩ ወረዳው ሀጠያ እና ሥለሌ በተባለ ቀበሌያት ከቀትር  እስከ ምሽት በዘለቀው የተኩስ ልውውጥ ሰዎች ሞተዋል፣ የተደናገጡ ነዋሪዎችም ወደ ጫካ ሸሽተዋል፡፡ 
የአሁኑ የተኩስ ልውውጥ የተካሄደው  ልዩ ወረዳውን በጊዜያዊት ተረክቦ እያስተዳደረ የሚገኘው ጥምር የጸጥታ ግብረ  ኃይል መንግሥት «ጽንፈኛ» ሲል የሚጠራው የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሦስት ቀናት ውስጥ ከዘረፏቸው የጦር መሣሪያዎች ጋር አጅ እንዲሰጡ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ትናንት ሰኞ ማብቃቱን ተከትሎ ነው፡፡ በልዩ ወረዳው የገጠር ቀበሌያት አሁንም የፀጥታ ሥጋት እንዳጠላበት ቢገኝም በአስተዳደር ከተማ ጊዶሌ አንጻራዊ ሰላም እንደሚታይ ለዶቼ ቬለ (DW) የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግን አሁንም እንደተዘጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ 
በደራሼ ልዩ ወረዳ ከባለፈው የሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ በተከሰተው አለመረጋጋት የተነሳ አካባቢው አሁን ድረስ ሥጋት ድባብ እንዳጠላበት ይገኛል፡፡ ልዩ ወረዳው በዞን እንዲዋቀር እንፈልጋለን  የሚሉ  ሀይሎች  የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችንና የመንግሥት የፀጥታ አባላትን ገድለው የጦር መሣሪያዎች ከዘረፉ ወዲህ የልዩ ወረዳው መዋቅር እንደፈረሰ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመከላከያ ሠራዊት የሚመራ ጥምር ሀይል አካባቢውን በጊዜያዊነት እያስተዳደረ ይገኛል፡፡ ይህ ጥምር ሀይል ታዲያ መንግሥት ድንፈኛ  ሲል የሚጠራው  የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሶስት ቀናት ውስጥ ከዘረፏቸው የጦር መሣሪያዎች ጋር እጅ እንዲሰጡ ያስቀመጠው ቀን ገደብ ትናንት ሰኞ አብቅቷል፡፡

የጥምር ኃይሉ ሰብሳቢ ሌተናል ኮሌኔል ፈጠነ ሲሳይ ከልዩ ወረዳው የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይትና በክልሉ መንግሥት ቴሌቪዥን በቀረበው  ማሳሰቢያቸው በጥቃቱ በቀጥታ ከተሳተፉት በተጭማሪ በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ድርጊቱን ሲያስተባብሩ የነበሩትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ 
ጥምር ሀይሉ ለታጣቂ ቡድኑ አባላት እጃችሁን ስጡ ሲል ያቀረበው ቀነገደብ  ትናንት ሰኞ ማብቃቱን   ተከትሎ በልዩ ወረዳው ሁለት ቀበሌያት የተኩስ ልውውጥ መሰማቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡ነዋሪዎቹ እንዳሉት የተኩስ  ልውውጡ የተሰማው ከልዩ ወረዳው ጊዶሌ ከተባለው የልዩ  ወረዳው አስተዳዳራዊ ከተማ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙት  ሀጠያ እና ሥለሌ  በሚባሉ ቀበሌያት ውስጥ ነው ፡፡ 
ትናንት ቀትር ላይ የተጀመረው የተኩስ ልውውጥ እስከ ምሽት መዝለቁን የሚናገሩትና የሀጠያ ቀበሌ ነዋሪ ነኝ ያሉ አንድ የአይን እማኝ ‹‹ ድንገት በተከፈተው ተኩስ አብዛኛው የቀበሌው ነዋሪ በመደናገጥ ወደ ጫካ በመሸሽ አሁን ድረስ እዚያው ተሸሽገን ነው ያለነው ፡፡ በጥይት የሞቱን የቆሰሉ ሰዎች ቢኖሩም ተጠግተን ለማጣራት አልቻልንም ›› ብለዋል፡፡ 
በልዩ ወረዳው የገጠር ቀበሌያት አሁንም የፀጥታ ሥጋት እንዳጠላባቸው ቢገኝም በአስተዳደራዊ ከተማ ጊዶሌ ግን አንጻራዊ ሰላም እንደሚታይ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ 
ያም ሆነ የልዩ ወረዳው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በመዘረፋቸው እስከአሁን አገልግሎት እንዳልጀመሩ  ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ትናንት ሰኞ የልዩ ወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ጥምር ሀይሉ ባደረገው ጥሪ መሠረት ወደ ሥራ መሄዳቸውን የሚናገሩት አንድ የከተማው ነዋሪ የመሥሪያ ቤቶቹ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ በመዘረፋቸው ሥራ መጀመር እንዳልቻሉ ገልጸዋል ፡፡

ዶቼ ቬሌ DW በጉዳዩ ላይ የጥምር ሀይሉንም ሆነ የክልሉን የሥራ ሃላፊዎች ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ሃላፊዎቹ በቅርቡ አጠቃላይ መግለጫ ስለሚሰጥ ጠብቁ ከማለት በስተቀር አሁን ባለው ሁኔታ ዝርዝር  መረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም፡፡ 
የሰገን ሕዝቦች ዞን በሚል ይጠራ የነበረውን የኮንሶ ፣ የአማሮ ፣ የቡርጂ ፣ የደራሼና የአሌ ወረዳዎችን  ያቀፈው ዞን ከሶስት ዓመት በፊት በአዋጅ ከፈረሰ ወዲህ በአስተዳደር መዋቅርና በወሰን ይገባኛል ጥያቄ አካባቢው አሁን ድረስ ሰላም እንደራቀው ይገኛል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ


አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ