1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደረቅ ጭነት ማጓጓዣ አሽከርካሪዎችን ያማረረው ተደራራቢ «የኮቴ» ክፍያ

ዓርብ፣ ግንቦት 30 2016

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች እና በየመንገዱ በሚጠየቀው “የኮቴ” በተባለው “የተጋነነ ክፍያ” መማረራቸውን አሽከርካሪዎች እና የአሽከርካሪ ባለንብረቶች አስታወቁ፡፡ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶቻቸው በጉዳዩ ላይ አቤት ብንልም እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንበትም ብለዋልም፡፡

https://p.dw.com/p/4gmZ9
Äthiopien Straße Ababa-Djibouti
ምስል DW/Y. Gebregziabher

የደረቅ ጭነት ማጓጓዣ አሽከርካሪዎች የተደራራቢ ግብር ክፍያ ምሬት መነሻው ምን ይሆን ?

አሽከርካሪዎችን ያማረረው የገቢ አሰባሰብ

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች እና በየመንገዱ በሚጠየቀው “የኮቴ” በተባለው “የተጋነነ ክፍያ” መማረራቸውን አሽከርካሪዎች እና የአሽከርካሪ ባለንብረቶች አስታወቁ፡፡

ይህን ክፍያ የፌዴራል መንግስት በሚያስተዳድረው ዋና ዋና መንገዶች በተጋነነ መልኩ እንድንከፍል እየተገደድን ነው ያሉት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶቻቸው በጉዳዩ ላይ አቤት ብንልም እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንበትም ብለዋልም፡፡

በክልሉ የሚሰበሰበውን የትኛውም ገቢ አሰራር የሚዘረጉት የኦሮሚያ ከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ እንዲሁም የገቢዎች ቢሮ ግን እንዲህ ያለ ክፍያ ምንነት አናውቅም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአሽከርካሪዎች ምሬት

ሰጡ ብርሃን አሽከርካሪና ጣና አሽከርካሪዎች ማህበር የተሰኘ የአሽከርካሪዎች ማህበር አባል ነው፡፡ ከጅቡቲ የሚመላለሰውን ከባድ ተሽከርካሪ ጨምሮ በአገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተንቀሳቀሱ በዚሁ ስራ ብቻ የሚተዳደሩም ናቸው፡፡ አሽከርካሪዉ ለዶቼ ቬሌ በሰጡት አስተያየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አቅጣጫዎች ስንቀሳቀሱ የሚጠየቁት “የኮቴ” የተባ በየውስን ኪሌሜትሮች የሚጠየቅ ክፍያ እጅጉን እንዳማረራቸው አስረድተዋል፡፡

“ለምሳሌ ከሞጆ ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ባለው ሶስት ጊዜ ትጠየቃለህ፡፡ አንድ አሽከርካሪ ጭነት ስጭን የሚጠየቀው ሮያሊቲ ታክስ አለ፡፡ የንን ግዴታ ነው ትከፍላለህ የትም፡፡ የንን ደግሞ አንድ ቦታ ከፈልክ ማለት ትጋሜ ለመክፈል አትገደድም፡፡ አሁን ግን የኮቴ የሚል ነገር ነው ያመጡት፡፡ የትኛው መስሪያ ቤት ነው በፌዴራል መንገድ ላይ ገመድ እየወጠረ የኮቴ የሚሰበስበው የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ አማረው አንስተዋል፡፡

ለእገታ የሚዳረጉት አገር አቋራጭ ሾፌሮች አቤቱታ

ክፍያውን የሚጠየቁት በየውስን ኪሌሜትር ርቀት መሆኑን የሚስረዱት አሽከርካሪው በየቦታው እስከ ሁለት ሺህ ብር እንደምጠየቁም ገልጸዋል፡፡ “ሞጆ ላይ ለምሳሌ 2000 ብር ትጠየቃለህ፡፡ ከዚያም በየቦታው አንድ ሺህም ከዚያ በላይም ትጠየቃለህ፡፡ ያንን መከራከር አሊያም ማስረዳት ብትሞክር ወደ ዱላ ሊሄድ ስለምችል የተጠየቅከውን መክፈል ነው ያለብህ፡፡ መሰል ክፍያ ከአገር ውጪ ጅቡቲ እንጠየቀለን አንድ ጊዜ፡፡ በአገር ውስጥ ግን መሰል የኮቴ የሚል ክፍያ ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ነው የምንጠየቀው” ብለዋልም፡፡

አሽከርካሪው እንደሚሉት ከዚህ በፊት በዚህ መማረራቸውን ማመልከታቸውን ተከትሎ የኦሮሚያ ከተማ እና ቤቶች ልማት ቢሮ አንድ ጊዜ የከፈለ ሰው ድጋሜ መጠየቅ እንደማይገባው ለሁሉም ለክልሉ ከተማ አስተዳደሮች የካቲት 07 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ብያረጋግጥም አሁንም መሬት ላይ ባለመተግበሩ የሚስመርር ያሉት ተደጋጋሚ ክፍያው አሁንም መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

የጭነት ማጓጓዣ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ
መሰል ክፍያ ከአገር ውጪ ጅቡቲ እንጠየቀለን አንድ ጊዜ፡፡ በአገር ውስጥ ግን መሰል የኮቴ የሚል ክፍያ ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ነው የምንጠየቀው” ብለዋልም፡፡ምስል Dawro zone government communications affairs

የአሽከርካሪዎች ማህበር አስተያየት

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስከያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱም በዚሁ ላይ ተጠይቀው ማህበሩ ከፍተኛ ክፍያ የምጠየቅበት እንደሞጆ ያሉ ከተሞችን ወርዶ ብጠይቅም ክፍያው ይቀጥላል መባላቸውን ተከትሎ ጥያቄያቸውን ወደ ክልሉ መንግስት እና የፌዴራል ትራንስፖርት ለማምጣት ማቀዳቸውን አስረድተዋል፡፡  ከሞጆ ከተማ አስተዳደር የከባድ አሽከርካሪዎች ከተማዋን ማጨናነቅ ብዙ ተጽእኖ እንዳለው በማስረዳት ክፍያው እንደምቀጥል ማስረዳቱን ተከትሎም “ሁለት ሺህ ብር መክፈል አያዋጠንም ብለናቸው ሌሎች ከተሞችም ብንሄድ ተመሳሳይ መልስ እንደምሰጠን ተረድተን ጥያቄያችንን ወደ ክልሉ ከፍተኛ መዋቅር እና የፌዴራል ትራንስፖርት እና ሎጂስትክ ሚኒስቴር ለመውሰድ አቅደናል” ሲሉም አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡

የአገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች የስጋት ድምጽ

በቅሬታው ላይ የመንግስት ምላሽ

በኦሮሚያ እንደማንኛውም ክልሎች አሰራር ሁለት አይነት የገቢ አሰባሰብ መኖሩ ይነገራል፡፡ እነዚህም በከተማ ልማት ቢሮ በኩል የሚዘረጋው የመዘጋጃ ቤት ገቢ እና በገቢዎች ቢሮ በኩል የሚዘረጋው መደበኛ ገቢ ናቸው፡፡

በዚሁ መሰረት ከአሽከርካሪዎች ተደጋግሞ በየከተሞቹ መግቢያ በአንድ ጊዜ ጭነት ይሰበሰባል ስለተባለው “የኮቴ” ክፍያን ያውቀው እንደሆን ለክልሉ ከተማ እና ቤቶች ልማት ቢሮ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አየለ ከፋለ “ከኛ ጋ ልወጣ የምችለው የማዘጋጀ ቤት ገቢ ልሰበሰብበት የሚችልበት መነሻ ደንብ ነው፡፡ ከዚያን በየከተሞች ደረጃ የሚከፈል የኮቴ ሳይሆን የአገልግሎት የሚባል ክፍያ አለ፡፡ ከዚያ ውጪ በኛ በኩል እደዚህ በየቦታው ከባድ አሽከርካሪዎችን እያቆሙ ገቢ የሚሰበሰብበት መንገድ የለም፤ አናውቅምም” ብለዋል፡፡

"ምን አለ ልጆቻችንን ብናሳድግበት…?" የሾፌሮች ተማጽኖ

በኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ በኩል ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ለሜሳ አየለ፤ “አረ በፍጹም የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ታክስ ላይ ሌላ ታክስ አያስከፍልም፡፡ አንደኛው ወደ ጅቡቲ የሚሄድ ከባድ ተሸከርካሪ ላይ ምንም አይነት ክፍያ አንጠይቅም፡፡ የኬቴ ክፍያ የሚባለው ደግሞ ምርት ከምጫንብት ስፍራ እንጂ በመንገዱ ስላለፈ ብቻ አይጠየቅም፡፡ አንዴ ብቻ ነው የሚጠየቀው፡፡ ደረሰኙን ይዞ ይሄዳል በመላ ኦሮሚም ሆነ ኢትዮጵያ ዳግም የሚጠየቅበት አሰራር የለም” ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ማዕድን በሚወጡ ወጣቶች ቀርቦላቸው እንዲህ ያለ አሰራር አለመኖሩን ደብዳቤ እንደጻፉላቸው የሚገልጹት ምክትል የቢሮ ኃላፊው አሁንም ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸው ወገኖች ካሉ ወደ ቢሮያቸው ብመጡ ችግሩ እንድቀረፍላቸው እንሰራለን ብለዋል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ