1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደመራና የመስቀል በዓላት የፀጥታ ችግር ባለበት የአማራ ክልል እንዴት ተከበረ?

ዓለምነው መኮንን
ዓርብ፣ መስከረም 17 2017

የፀጥታ ችግር ባለበት በአማራ ክልል የዘንድሮው የደመራና መስቀል በዓላት በአንዳንድ አካባቢዎች በተለመደው መንገድ በአደባባዮች ማከበራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በየሰፈሩና መንደሩ በህብረት የሚደረገው ዝግጅት ግን መቀዛቀዙን ነዋሪዎቹ ገልጠዋል፡በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ «ተከበረ ማላት አይቻልም» ብለዋል ነዋሪዎቹ።

https://p.dw.com/p/4l9kb
Äthiopien Religion l Feierlichkeiten zum Meskel-Fest
ምስል Amanuel Sileshi/AFP via Getty Images

የመስቀል በአል አከባበር በአማራ ክልል

የተለያዩ የአማራ ክልል ነሪዎች ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት ግጭቶች በተለያዩ ቦታዎች በሚስተዋሉበት የአማራ ክልል የዘንድሮው  የደመራና  የመስቀል በዓላት በተለያዩ ስሜቶች ተከብረዋል፡፡በዓላቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በድምቀት ሲከበሩ በሌሎች ደግሞ ከወትሮው በተለየ ቀዝቀዝ ባለ ስሜት መከበራቸውን ነው ያነጋገርናቸው የደሴ፣ የጎንደር፣ የአጣዬ፣ የፈረስ ቤት፣ የደብረወርቅ፣ የደብረማርቆስና የባሕር ዳር ከተሞች ነዋሪዎች የገለፁት፡፡

በዓሉ በአደባባዮች በድምቀት ተከብሯል

አስተያየታቸውን ከሰጡን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችመካከል ሙለጌታ ዓለማየሁ የደመራ በዓል በጎንደር ከተማ ትናንት በድምቀት ተከብሮ ዛሬ ደግሞ በመንደሩ ሰዎች በተለመደው መልኩ ተሰባስበው እያከበሩት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“ እንደተለመደው ጥሩ ነው፣ በጋራ ነው እከበርን ያለነው፣ አሁን ቡና ተፈልቶ እየጠጣን ነው፣ ዳቦው፣ ፈንድሻው፣ ቦቆሎው ቀርቧል አካባቢው “ጨረቃ” መስሏል”፡ ብለዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የአጣዬ ከተማ ነዋሪ አቶ እሸቱ አሳዬ በዓሉ በድምቀት መከበሩን ነግረውናል፡፡
እንደ አቶ እሸቱ በዓሉ በአጣዬ ዜሮ 1 በተባለ አካባቢ ደመራ ተዘጋጅቷል፣ በዓሉ በተለዬ ሁኔታ እተከበረ እንደሆነ አብራርተዋለል፡
በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ከተማ አስተዳደር አስተያየት ሰጪ እንደነገሩን የደመራ በዓል ሆጤ በተባለ አካባቢ በድምቀት ቢከበርም በየመንደሩ የነበረው ሁኔታ ግን እንደበፊቱ በጋራ ሳይሆን የተቀዛቀዘና ግላዊነት የተላበሰ ነበር፡፡

የአማራ ክልል የመስቀል በዓል አከባበር
በአማራ ክልል የመስቀል በዓል በአደባባይ ቢከበርም በየሰፈሩ የነበረው አከባበር ግን  በዓሉ ከህብረት ይልቅ በተጠናጠል ተከብሯልምስል Alemnew Mekonnen/DW

ደመራው በሆጤ አደባባይ በደመቀ ሁኔታ መከበሩን ገልፀው፣ በየመንደሩ ያለውን ግን ቀደም ሲል ይከነበሩ ከነበሩትየበዓል አከባበር ጋር ማወዳደር እንኳ እንደማይቻል ነው የገለፁት፡፡ “በሁሉም መልኩ ተቀዛቀዘ ነው” ሲሉ ነው ድባቡን ለማሳየት የሞከሩት፡፡ ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ ድለቃዎች፣ ሙዚቃዎች፣ የህፃናቱ ጫጫታ እንደማይታይ ተናግረዋል፡፡ “በየቀያችን ችቦ ለኩሰናል” ነው ያሉት፡፡

 በዓሉ ከህብረት ይልቅ በተጠናጠል ተከብሯል


አብዛኛው ሰው በዓሉን ያከበረው በየግቢው እንደሆነና በቤተክርስቲያንም ቢሆን እንደተጠበቀው እንዳልነበረ ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ ከተማ ነዋሪ መምህር አስማማው አታላይ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛው ሰው በየግቢው እያከበረ ነው፣ አከባበሩም የፈዘዘ እንደሆነ አመልክተዋል፣ ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያን የሚደረገው የበዓል አከባበር ሰፊ ህዝብ ይወጣበት እንደነበር አስታውሰው የዘንድረው ሁኔታ ግን ያነን እንደማያሳይ ነው አስተያየት ሰጪው ያስረዱት፡፡ ከዚህ ቀደም በየመንደሩ በዓሉን ለማክበር 40 ክል ሰዎች በአንድ ሰበሰቡ እንደነበርም አስታውሰዋል፣ ዘንድሮ ግን 3 እና 4  እሆነ ሰው በየበሩ ነው እከበረ ያለው ሲሉ አክለዋል፡፡

 የአማራ ክልል የመስቀል በዓል አከባበር
ግጭት ባጠላበት የአማራ ክልል የመስቀል በዓል አከባበርምስል Alemnew Mekonnen/DW

«በዓሉ አልተከበረም ማለት ይሻላል»

በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪው ፀሐዩ አበራ በዓሉ አልተከበረም ማለት እንደሚሻል ገልጠዋል፤ ምክንያቱ ደግሞ የፀጥታ ሁኔታው አስተማማኝ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት በአካባቢው ያለው የፀትታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑና ባለው ስጋት በዓሉ ተከብሯል ለማለት ያስቸግራል ነው ያሉት፡፡ ነዋሪው ትናንትና በቤተክርስቲያን ካደረገው ዝግጅት ውጪ በየመንደሩ የሚደረግ ምንም ዝግጅት የለም ብለዋል፡፡ የህፃናት ችፈራና የበዓል ድምቀት ምንም የለም  ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የደብረማርቆስ ከተማ አስተያየት ሰጪ ቀደም ባሉት ዓመታት በዓሉን ሰብሰብ ብለው ያከብሩ እንደነበር ጠቅሰው ዘንድረ ግን  ሁሉ እንደሌለ ገልጠዋል፡፡
አንድ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ህብረተሰቡ የገንዘብ እጥረትም እያጋጠመውና የኑሮውድነቱ ተቆጣጣሪ ያጣ እስኪመስል በማሻቀቡ ሰው ገንዘብ አዋጥቶ በዓልን በጋራ ከመዋል ልቅ በየራሱ በአቅሙ በየግቢው ነው በዓሉን እያከበረ ያለው ብለዋል፡፡
የደመራ በዓል ትናንት በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከበረ ሲሆን በባሕር ዳር ከተማም የከተማዋ ምዕመናንና ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡

ዓለምነው መኮነን
ታምራት ዲንሳ
ፀሐይ ጫኔ