የያዮ የድንጋይ ከሰል እና የጥቅም ግጭት | ኤኮኖሚ | DW | 13.06.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የያዮ የድንጋይ ከሰል እና የጥቅም ግጭት

በኦሮሚያ ክልል የኢሉባቦር ዞን ከዚህ ቀደም በመከላከያ ሚንስቴር ሥር የሚገኘዉ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እጅ የነበረውን የያዮ የከሰል ድንጋይ ማምረቻ ለተደራጁ ወጣቶች ሰጠሁ ቢልም ውሳኔው እስከ ዛሬ ገቢራዊ አልሆነም። በአካባቢው የሚገኘው የተፈጥሮ ሐብት መፍትሔ ያልተበጀለት የጥቅም ግጭት ፈጥሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:27
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:27 ደቂቃ

የያዮ ነዋሪዎች በሜቴክ ላይ የሚያቀርቧቸው በርካታ ቅሬታዎች አሏቸው

በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሥር የሚገኘው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ይቆጣጠረው የነበረውን የያዮ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ በማኅበር ለተደራጁ 171 ወጣቶች መስጠቱን በኦሮሚያ ክልል መስተዳድር የኢሉባቦር ዞን አስታውቋል። የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ እንደሚሉት ወጣቶቹ በያዮ ወረዳ ጭቦ ቀበሌ የሚገኘውን የድንጋይ ከሰል አምርተው አይካ አዲስ ለተባለው ኩባንያ ይሸጣሉ። "ከዚህ በኋላ በቀጥታ የከሰል ድንጋዩን ለአይካ አዲስ የሚያቀርቡት እነዚህ በማኅበር የተደራጁት ወጣቶች ይሆናሉ። ወጣቱ ይኸንን የተፈጥሮ ሐብት ተጠቅሞ የተወሰነ ሐብት አከማችቶ ወደ ሌላ ሥራ እሚተላለፍበት ሁኔታ እና ከዚህ የተፈጥሮ ሐብት ላይ ደግሞ ቀጣዩ እየመጣ ያለው ወጣት ደግሞ በተራው ተደራጅቶ ሐብት የሚፈጥርበት ሁኔታ ይጠበቃል" ይላሉ አቶ ነመራ።

ሜቴክ ተብሎ የሚታወቀው  የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የድንጋይ ከሰሉን ላለፉት አምስት አመታት እያመረተ አይካ አዲስ ለተባለው ኩባንያ  ይሸጥ እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ይናገራሉ። በኢሉባቦር ዞን ዕቅድ መሠረት 171 ወጣቶች በሁለት ማኅበራት የተደራጁ ሲሆን ከፊሎቹ ከዚህ ቀደም በዚያው የማዕድን ማውጫ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። ወጣቶቹን የማደራጀት ኃላፊነት የተሰጣቸው  አቶ ጌታቸው አብዲሳ "ከአይካ አዲስ ጋር እንደተነጋገርነው በቀን ከ60 እስከ 80 ቶን የማውጣት አቅም አላቸው። አንዱን ቶን የተዋዋሉት በ1,300 ብር ለማቅረብ ነው። የሚያወጡበትን መሳሪያ የሚረዳቸው አይካ አዲስ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ነመራ ቡሊ እና አቶ ጌታቸው አብዲሳ ሥምምነት መፈጸሙን ይናገሩ እንጂ ሜቴክ የድንጋይ ከሰል ማምረቻውን እንዳላስረከባቸው ወጣቶቹ ይናገራሉ።

የ27 አመቷ ዘኪያ አሊዪ ጅብሪል "ከብዙ ጥያቄ በኋላ ተደራጅተን ሕጋዊ ሰውነታችንን ሙሉ በሙሉ አሟልተን ወደ ሥራ ልንገባ ነበር" ስትል ትናገራለች። የከሰል ድንጋይ የሚመረትበት ሥፍራ ተወልዳ ያደገችበት ቀዬ፤ የያዮ የማዳበሪያ ፋብሪካ የሚገነባበትም የቀድሞው የአባቷ ማሳ ነው። የድንጋይ ከሰል ማምረቻው ሊሰጣቸው ቃል ከተገባላቸው፤ ከአይካ አዲስ ጋርም የግብይት ውል ከፈረሙ ወጣቶች አንዷ ዘኪያ ናት።

"ብር ከፍለን ደረሰኝ ካወጣውን ወደ አምስት ወር ቆየ። ሁሉንም ነገር ከጨረስን በኋላ አንሰጥም እኛ አንለቅም እኛው ነን የምንሸጠው ብለው እምቢ አሉን። ከዚያ በኋላ ቅርብ ጊዜ በስንት ጥያቄ በስንት ሰላማዊ ሰልፍ በቀደም ደግሞ ጸደቀ ተብሎ ከኦሮሚያም ሰው ተገኝቶበት ትልቅ ዝግጅት አዘጋጅተን ለቀናል ካሉ በኋላ የሆነ የቀረ ፊርማ አለ። አልፈረሙም ወረቀት ላይ። ከዛ በኋላ አንሰጥም፤ እኛ ፊርማ አልፈረምንም የዛን ቀን ራሱ በቃል ነው እንጂ ያልንው እኛ ፊርማ ስላልፈረምን አሁንም አንለቅም ብለው እንግዲህ ወደ ሥራ አልገባንም። እዛ ቦታ ብንደርስ ራሱ ይገሉናል"

የእርሻ ማሳቸው ለማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ከመወሰዱ በፊት ቡና ጭምር የሚያመርቱ ገበሬ የነበሩት አቶ መኪዮ አሊዬ "ከ2005 ኅዳር ወር ጀምሮ እስከ 2010 ኅዳር ወር ከዚያ ቦታ ላይ እስከ 2800 ቢያጆ ከሰልን ያመረተ ሜቴክ ነው። የኅብረተሰቡን ሐብት አውጥተው ይሸጣሉ፤ አንዲት መጠጥ ውሐ ሁለት ሶስት ኪሎ ሜትር መንገድ ስሩልን ብለን ጠይቀን አቃተን። መዝረፍ እንጂ መሥራትን የማያውቁ ናቸው። ለሕዝቡ እስካሁን ምንም አይነት ጥቅም አልሰጠም" ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታ የሰነበተ መሆኑን ያስረዳሉ።

እንዲህ ግዙፉ የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ከአካባቢው ነዋሪ ጋር የተፋጠጠባት የኢሉባቦሯ የያዮ ወረዳ በተፈጥሮ ሐብት የበለጸገች ነች። በዓለም ምርጡ ተብሎ የሚወደሰው የአረቢካ ቡና ይመረትባታል፤ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የባሕል እና የሳይንስ ድርጅት (UNESCO) የተመዘገበው ያዮ ጥብቅ የተፈጥሮ ደንም በዚያው ይገኛል። አካባቢው ባለው ምድረ ህይወት (Biosphere)፤ ሥነ-ምሕዳር እና የአዕዋፍ ዝርያዎች የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች አጥብቀው ይቆረቆሩለታል። የአካባቢውን የተፈጥሮ ሐብት ባለቤትነት፣ ቁጥጥር እና አጠቃቀም በጥልቀት ያጠኑት ዶ/ር ካሳሁን ከሊፋ  እንደሚሉት በነዋሪው፤ የተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች እና የመንግሥት ተቋማት መካከል ውድድር ከፍ ሲልም የጥቅም ግጭት ፈጥሯል። የጥናት ባለሙያው "በእጃቸው ገንዘብ፤ በእጃቸው ሐብት ያላቸው ሰዎች አሸናፊ ሆነው ይወጣሉ። በተለይ በተለይ ዋናውን ሚና የሚጫወተው ከልሒቃን ጋር የሚኖር ግንኙነት ነው። ከፖለቲካው ወይንም ከገዢዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች አሸናፊ ሆነው ይወጣሉ። በአብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጎጂ ነው። ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ትስስር እና እውቀት የላቸውም። ከዚያም ባሻገር ደግሞ ሕጋዊ አካሔዶችን እንኳን ለመከተል አቅም የላቸውም" ሲሉ የሁኔታውን ፈታኝነት ያስረዳሉ።

 "እኔ እንዳየሁት በያዮ የመጀመሪያው ተሸንፏል ብዬ የማስበው የአካባቢው ኅብረተሰብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአንድ ወቅት ምንም እንኳን ተሰሚ ቢሆኑም የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች በተለይ እዛ አካባቢ ላይ ሲሰሩ የነበሩ የተፈጥሮ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ተሸናፊ ሆነዋል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የከሰል ድንጋይ ከማውጣት ሥራው ጋር የተገናኙ አካላት ወታደሮች ነበሩ። ለምሳሌ ሜቴክ ነበር ዋናው። ሜቴክ ደግሞ በመንግሥት የሚመራ የመከላከያ አንድ ክንፍ ነው። ምን አይነት ኃይል ሊኖራቸው ይችላል የሚለውን መገመት ይቻላል። ሌላውን የማይሰሙበት ደረጃ ላይ ነበር የደረሱት። ስለዚህ እስካለፈው ዓመት ድረስ አሸንፎ የወጣው ሜቴክ ነበረ"

የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን በ2004 ዓ.ም. ወደ ያዮ ወረዳ ያቀናው በሁለት አመታት ውስጥ የማዳበሪያ ፋብሪካ ገንብቶ ለማስረከብ ነበር። የግንባታው ሒደት በተባለው ጊዜ መጠናቀቅ ተስኖት የግንባታ ወጪውም  ከ11 ቢሊዮን ወደ 20 ቢሊዮን አብር አሻቅቦ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጭምር አስቆጥቷል።አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል "በቢሊዮን የሚቆጠር ብር እየባከነ በማን ጊዜ እና በማን ብር ላይ ማ እንደሚማር አልገባኝም" ሲሉ በወቅቱ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

በዓመት 300 ሺ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ሊያመርት ውጥን የተያዘለትን ፋብሪካ የሚያስገነባው የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ደሜ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የተናገሩትም ቢሆን ተስፋ የሚሰጥ አልነበረም። አቶ ፈቃዱ "በወር 90 ሚሊዮን ብር ወለድ እየከፈልን ነው። በቀን ወደ 3 ሚሊዮን ብር አካባቢ ማለት ነው። ይኸ ደግሞ ተደራርቦ ነው የሚቀጥለው። ስለዚህ ለዕቅዱ የተያዘው በጀት ራሱ በወለድ የሚያልቅ ነው" ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

በግንባታው መጓተት ሳቢያ እስካለፈው 2009 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 1.8 ቢሊዮን ብር ወለድ ተከፍሎበታል የተባለው እና ዛሬም ድረስ ፈቅ ያላለው ግንባታ ኪሳራ ግን ይኸ ብቻ አይደለም። አቶ ካሳሁን በጥናት እንዳረጋገጡት ነዋሪዎቹም እንደሚናገሩት ከእርሻ መሬታቸው የተፈናቀሉ የተከፈላቸው ካሳ በቂ አልነበረም። "ካሳው በጣም የወረደ ነው። ከፈለክ ትወስዳለህ ካልፈለክ ደግሞ ትታሰራለህ" ስትል ዘኪያ ታስረዳለች።

አቶ ካሳሁን እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ተቋማት የተሰሩ ጥናቶች በያዮ የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት አዋጭ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር። ፋብሪካዉ በዓለም ባንክ የከፋ አካባቢያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጫና ያሳድራል የሚል ደረጃ ቢሰጠውም የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መንግሥት ግን ተግባራዊ ለማድረግ አላፈገፈገም። አቶ ካሳሁን "በእኔ ጥናት መሰረት 4,000 ሺህ ሰው ቢፈናቀልም ለ2,200 ሰው ብቻ ነው የካሳ ክፍያው የተሰራው። 65 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ ተይዞ ነበረ። ከ2,200 ሰዎች ግን የካሳ ክፍያ ያገኙት እኔ ጥናት እስከሰራሁበት ጊዜ ድረስ 320 ሰዎች ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ተረስተው ነበረ ማለት ነው" ሲሉ የጥናታቸውን ግኝት ያስረዳሉ። የካሳ ክፍያ ያገኙ ሰዎችም ቢሆኑ የንግድ ሥራ ሥልጠና እንዳልተሰጣቸው፤ ለተፈናቀሉ ሰዎች ይፈጠራል የተባለው የሥራ ዕድል ውጤታማ እንዳልሆነም አቶ ካሳሁን ያስረዳሉ።

የድንጋይ ከሰል ማምረቻውን ለተደራጁ ወጣቶች የመሥጠቱ ውሳኔ ቅሬታን በጊዜያዊነት በመፍታት ረገድ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ቢሆንም ዘላቂነቱ ግን አጠያያቂ ነው። የክኅሎት እና የገበያ ትሥሥር ጉዳይ አንደኛው ጥያቄ ነው። አቶ ካሳሁን የከሰል ድንጋይ የሚያመርቱ ወጣቶች "ዋናው ቡና ወዳለበት ደን ውስጥ አይገቡም ወይ? ነገ ጣውላ፤ ከሰል አይወጣም ወይ? አካባቢው ምድረ በዳ እንዳይሆን እሰጋለሁ" ይላሉ። አቶ ካሳሁን የወጣቶቹን የገቢ ጥያቄ፤ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎችን ሥጋት እና የድንጋይ ከሰል የማምረቱን ፍላጎት ማጣጣም ይገባ እንደነበር በአፅንዖት ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic