1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የየካቲት 30 ቀን 2018 ዓም የዓለም ዜና

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ሰኞ፣ የካቲት 30 2018

የደቡብ ሱዳን ጦር የተቃዋሚ ኃይሎች በሚገኙባት አኮቦ ግዛት ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት ዜጎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በማዘዙ በሺህዎች የሚቆጠሩት ወደ ኢትዮጵያ መሸሻቸው ተሰማ። በናይሮቢ ኬንያና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰው የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 42 መድረሱን መንግሥት አስታወቀ። ከእስራኤል እና አሜሪካን ጋር በሚሳኤልና በሰው አልባ አውሮፕላኖች እየተፋለመች የምትገኘው ኢራን አቋሜን አልለወጥኩም አለች። የሟቹን ሃይማኖታዊ መሪ አሊ ኻሚኒን ልጅም በእግራቸው ለመሪነት መርጣለች። እስራኤል በዛሬው ዕለትም በተለያዩ የሊባኖስ ግዛቶች የተጠናከረ ጥቃት ቀጥላለች። ሂዝኮላኽም በጥቃቱ መግፋቱን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/5A4ek

ጁባ፤ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየሸሹ ነው

የደቡብ ሱዳን ጦር የተቃዋሚ ኃይሎች በሚገኙባት ምሥራቃዊ ግዛት ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት ዜጎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በማዘዙ በሺህዎች የሚቆጠሩት ወደ ኢትዮጵያ መሸሻቸው ተሰማ። አሶሲየትድ ፕረስ እንደዘገበው አኮቦ ከተሰኘችው ግዛት ደቡብ ሱዳናውያን ከትናንት በስተያ ቅዳሜ ምሽት ጀምሮ በመልቀቃቸው አሁን ከተማዋ ባዶ ሆናለች። ሲቪሎች ከተማዋን ከለቀቁ በኋላም ትናንት ከቀትር በኋላ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ የተመድ የረድኤት ተቋማት መግለጻቸውንም አመልክቷል። የተጠቀሰችው ከተማ የተቃዋሚው የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች የነጻነት ንቅናቄ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ SPLM-IO የተሰኘው በሪክ ማቻር የሚመራው ቡድን የመጨረሻዋ ጠንካራ ይዞታ እንደሆነች ተገልጿል። በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና በማቻር መካከል የቀጠለው ውዝግብ ዳግም ግጭት ቀስቅሶ በደቡብ ሱዳን የተለያዩ ግዛቶችም እየተዛመተ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል። በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ የጤና መሠረተ ልማትና አገልግሎት ከጥቅም ውጪ እየሆነ መሄዱም ተገልጿል። የሀገሪቱ ባለሥልጣናትን ግን ወደ ጎረቤት ኬንያ እየሄዱ እንደሚታከሙ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

 

ናይሮቢ፤ ኬንያ ውስጥ በጎርፍ ምክንያት 42 ሰዎች መሞታቸው መድረሳቸው

በናይሮቢ ኬንያና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰው የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 42 መድረሱን መንግሥት አስታወቀ። ባለፈው ዓርብ ዕለት የወረደው ከባድ ዝናብ መጠነ ሰፊ ጎርፍ ማስከተሉ ነው የተነገረው። የጎርፍ አደጋው ሰዎችን ማስጠሙን ተሽከርካሪዎችን እየጠረገ መውሰዱና የሀገሪቱን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራ ማስተጓጎሉን ሮይተርስ ዘግቧል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የመከላከያ አባላትን ጨምሮ በጎርፍ የተወሰዱና የተጎዱ ሰዎችን ለማውጣት እየሠሩ እንደሆነ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ 172 መኪኖች በጎርፍ መወሰዳቸውን የኬንያ የመንግሥት አገልግሎትና የሰው ሀብት ሚኒስትር ጂኦፌሪ ኪሪንካ ሩኩ ለዜና አውታሩ ገልጸዋል። መሠረተ ልማቶች እና በሕዝቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ ተመልክቷል። ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ቅዳሜ ዕለት ከሀገሪቱ የእህል ክምችት በአስቸኳይ በጎርፉ ለተጎዱ ቤተሰቦች እንዲከፋፈል ትዕዛዝ ሰጥተዋል።  

 

ቴህራን፤ «የኢራን አቋም አልተለወጠም» የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ

ከእስራኤል እና አሜሪካን ጋር በሚሳኤልና በሰው አልባ አውሮፕላኖች እየተፋለመች የምትገኘው ኢራን አቋሜን አልለወጥኩም አለች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባግሀይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኢራን አቋም አልተለወጠም ብለዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደውን ጦርነት በተመለከተ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ግድየለሽነትን መርጧል ሲሉም ኮንነዋል። ሚኒስትሩ አክለውም የተመድም ድጋፍ አለማሳየቱን መራር እውነታ ሲሉ ወቅሰዋል። ኢራን ለሕልመኛና ቅዠታሞች መቃብር ናት ያሉት ሚኒስትሩ እስላማዊ ሪፑብሊክ ኢራንና የኢራን ሕዝብ የሀገሪቱን አንድነት እንዴት እንደሚከላከሉ ያውቃሉ ሲሉም ለሌሎች ሃገራት ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል። ኢራን የምትወስደው እርምጃ ሕጋዊ ነው ያሉት ኢስማኢል ባግሀይ በተሳሳተ ስሌት ጦርነቱን ከፈቱብን ያሏቸው ሃገራት ማጣፊያው አጥሯቸዋል የሚል መልእክት ያዘለ ንግግር አድርገዋል።

«አሁን የእየደረሰባቸው ያለው ድብደባ የእነዚያ በጣም የተሳሳቱ ስሌቶች ውጤቶች ናቸው።  በዚህ ቅዠት ውስጥ ይቆዩ። ይኸው ቅዠት ነው በሚያሳዝን ሁኔታ በእንዲህ ዓይነት የተሳሳቱ ስሌቶች ነው። አሁን እነሱ እራሳቸው በዚህ እረግረግ ውስጥ መጠመዳቸው እየተሰማቸው ነው።»

ኢራን በዛሬው ዕለት በሞቱት ሃይማኖታዊ መሪ ምትክ ልጃቸውን ለዚሁ ሥልጣን መምረጧን ይፋ አድርጋለች። የ56 ዓመቱ አያቶላ ሞጅታባ ኻሚኒ በአባታቸው እግር መተካት ቴህራን በአሜሪካ እና እስራኤል የተከፈተባትን ጦርነት ይበልጥ ሊያባብስ እንደሚችል እየተነገረ ነው። ሂዝቦላኽ ከአዲሱ መሪ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነኝ ብሏል።

 

ሊባኖስ፤  ሊባኖስ ላይ የቀጠለው የእስራኤል ድብደባ

እስራኤል በዛሬው ዕለትም በተለያዩ የሊባኖስ ግዛቶች የተጠናከረ ጥቃት ቀጥላለች። የእስራኤል ጦር ኃይል ኢላማው የሂዝቦላኽ ክንፎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ይገልጻል። ዋና ከተማ ቤይሩት ላይም ዛሬ የተፈጸመው ድብደባ ከፍተኛ ጭስ ማስከተሉን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የእስራኤል ጦር ኃይል ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫም ባለፉት ቀናትም ተመሳሳይ ባካሄደው ጥቃት የሂዝቦላኽን በርካታ ሮኬትና ሚሳኤል መተኮሻዎችን ማውደሙን አስታውቋል። ከጥቃቱ ጎን ለጎንም በሂዝቦላኽ የሚወነጨፉ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችንም ማክሸፉን ገልጿል። የእስራኤል ጦር ወታደሮቹን የሂዝቦላኽን ጥቃት ለማክሸፍ ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ማስገባቱንም አመልክቷል። የአካባቢውን ነዋሪዎችም ስፍራውን እንዲለቁ አስጠንቅቋል። ሂዝቦላኽ በበኩሉ ወደ ሊባኖስ የገቡ የእስራኤልን ወታደሮች ላይ በጸረ ታንክ ሚሳኤል ጉዳት አድርሻለሁ ብሏል። ወደ ሰሜን እስራኤልም ሮኬቶችን መተኮሱን ገልጿል። የሊባኖስ ፕሬዝደንት ደግሞ የሂዝቦላኽ እርምጃ ሀገራቸውን ሊያፈራርስነው ሲሉ ቡድኑን ከሰዋል።

 

ብራስልስ፤ ቤልጂየም በአይሁድ ቤተጸሎት ደጃፍ የደረሰው ፍንዳታ

የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ጸረ ሴማዊነትን አጥብቄ እዋጋለሁ ሲሉ ዛቱ። ዛሬ ማለዳ በቤልጂየሟ ሊየዥ ከተማ በአንድ የአይሁድ ቤተጸሎት ደጃፍ የደረሰው ፍንዳታ በሰው ላይ ጉዳት አላደረሰም ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ባርት ደ ቬበር፤ ጸረ ሴማዊነት በእሴታችና በማኅበረሰባችን ላይ የተቃጣ ጥቃት በመሆኑ በግልጽ ልንዋጋው ይገባል ሲሉ በማኅበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልክእት ገልጸዋል። የቤልጅየም የሀገር ውስጥ ሚኒስትር በበኩላቸው በፍንዳታው የአይሁድ ማኅበሰብ ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ አጸያፊ ጸረ ሴማዊ ድርጊት ነው ሲሉ ነቅፈዋል። የሊየዥ የከተማ ከንቲባ ዊሊ ዴምየር፤ ድርጊቱን ኮንነው፤ በሌላ ሀገር የሚካሄድ ጦርነትን ወደ ቤልጂየም ማስገባት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

የቤተ ጸሎቱ ራቢ፤ ጆሹዋ ነይማን፤ በበኩላቸው ፍንዳታው በሰውም ሆነ የ120 ዓመት ዕድሜ ባለው የአይሁድ ቤተጸሎት ላይ ያስከተለው ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል። ፈንጂው እዚያው ተቀምጦ ይሁን ተወርውሮ የፈነዳው አለመታወቁን ገልጸው የሚካሄደው ምርመራ የተፈጸመውን ይፋ ያወጣዋል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል።

«ምርመራው እውነቱን ይፋ ያወጣዋል። ፖሊስንም ሆነ የተለያዩ የሕግ አስከባሪ ተቋማትን አልጠየኩም፤ ግን ምርመራው በትክክል ምን እንደተከሰተ ይወስናል። ሁሉንም ካሜራዎች እና የቀረጹትን መረጃ በሙሉ ያገኛሉ ብዬ አምናለሁ። »

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።