አዲስ አበባ፤ 130ኛው የአድዋ ድል በዓል
130ኛው የአድዋ ድል በዓል በዛሬው ዕለት ተከበረ። በዓሉ በተለይ አዲስ አበባ በመንግሥት ደረጃ በአድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ መከበሩን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል። እንዲያም ሆኖ ግን እንደወትሮ ሕዝብ በሚያከብርበት አደባባይም ሆነ የአድዋ ድልድይ ላይ ይከናወኑ የነበሩ ትዕይንቶች ዘንድሮ እንዳልነበሩ ተነግሯል።
ዕለቱን በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው ባስተላለፉት አጭር መልእክት «ዛሬ በመላው አፍሪቃ እና በጥቁር ሕዝብ ላይ ጨልሞ የነበረ ሰማይ ጸሐይ የፈነጠቀበት ቀን ነው» ካሉ በኋላ፤ «ተከብረን የምንኖርባትን ኢትዮጵያን ከድንቅ ስልጣኔ እና ታሪክ ጋር ከነታላቅ ክብሯ በደም መስዋእትነት ላስረከቡን አባቶቻችን ክብር ይገባቸዋል።» ብለዋል። ትናንት እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ ባስተላለፉት መልክትም፤ የዐድዋን ድል «የኢትዮጵያውያንን የማይቀየር ዐቋምና ዐቅም ያሳየ ድል» ብለውታል። በዓሉ አድዋ ላይ መከበሩንም መረጃዎች ያሳያሉ።
ደቡብ ሱዳን፤ ሩዌንግ ግዛት በደረሰ ጥቃት 169 መገደላቸው
ደቡብ ሱዳን ሩዌንግ ግዛት ውስጥ በደረሰ ጥቃት 169 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ዛሬ አስታወቁ። ማንነታቸው ባልታወቀው ታጣቂዎች ከተገደሉት 90ው ሕጻናት፤ ሴቶችና አረጋውያን ሲቪሎች መሆናቸው ተገልጿል። የወረዳው ኮሚሽነርና ዋና ዳይሬክተርም በጥቃቱ መገደላቸውን የአካባቢው የማስታወቂያ ሚኒስትር ጀምስ ሞኒሊያክ ማጆክ ለሮይተርስ ተናግረዋል። በተጠቀሰው የሰሜናዊ ደቡብ ሱዳን ግዛት አመጽ መቀስቀሱን በሀገሪቱ የተመድ ተልዕኮ UNMISS ትናንት ማምሻውን ይፋ አድርጓል። ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥም የጸጥታው መደፍረስ መባባሱንም አስታውቋል። ማንነታቸው ያልተለየው ታጣቂዎቹ ወጣቶች አቢሞኖም የተባለችው ወረዳ ጽሕፈት ቤት ጥቃት በማድረስ ከ20 በላይ ሰዎችን መግደላቸውንም UNMISS በመግለጫው ጠቅሷል። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪዎች ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ መስጠታቸውንም አመልክቷል። አቢሞኖም እና ሩዌንግ ተጎራባች ወረዳዎች እንደሆኑ የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ ጠቁሟል። ደቡብ ሱዳን ውስጥ ባለፉት ሳምንታት በፕሬዝደንት ሳል ቫኪር እና በተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር መካከል በተጀመረው የሥልጣን መጋራት ሂደት ምክንያት ግጭት ማገርሸቱ እየተነገረ ነው። የተመድ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ አስቀድሞ ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል።
ጁባ፤ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የድንበር የለሽ ሀኪሞች 26 ባልደረቦች መጥፋታቸው
ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ጥቃት እየተባባሰ በመጣባት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ 26 ባልደረቦቹ መጥፋታቸውን ዛሬ አስታወቀ። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ላንኪን እና ፒየሪ በተሰኙ አካባቢዎች ከነበሩ 291 ሠራተኞች ባለፉት ሳምንታት የ26ቱ ድምፅ እንዳልሰማ ገልጿል። ሁለቱ የተጠቀሱት ቦታዎች ጆንግሌ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አካባቢዎቹ በመንግሥትና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል በዋነኛነት ግጭት የሚካሄድባቸው መሆናቸው ተመልክቷል። ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በእነዚህ ቦታዎች የህክምና አገልግሎት መስጠቱን አቋርጧል። በተለይም ላንኪን ላይ የድርጅቱ ቢሮ በመንግሥት የአየር ድንብደባ ከሳምንታት በፊት መመታቱንም ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን አመልክቷል። አብዛኞቹ ሠራተኞቹም ከነቤተሰቦቻቸው ከጥቃቱ ለመሸሽ መገደዳቸውን፤ በአሁኑ ጊዜም አብዛኞቹ መበታተናቸውን አስታውቋል።
መካከለኛው ምሥራቅ፤ የኢራን ሚሳኤሎች፤ የሂዝቦላህ ጥቃት፤ የእስራኤል አጸፋ
በመካከለኛው ምሥራቅ የተለኮሰው ጦርነት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። በእስራኤል አሜሪካ ጥምር ጥቃት ከፍተኛ ባለሥልጣኗን ያጣችው ኢራን እስራኤልን ጨምሮ በአቅራቢያዋ የአሜሪካ ይዞታ በሚገኝባቸው የአረብ ሃገራት ላይ የከፈተችውን ጥቃት ዛሬም አጠናክራለች። በርካታ የአሜሪካን የጦር አውሮፕላኖች ኩየት ላይ የተከሰከሱ ሲሆን በኩየት ከአሜሪካ ኤምባሲም ጥቁር ጭስ ሲወጣ መታየቱ ተዘግቧል። ያደረሰው ጉዳት ባይገለጽም የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላን ቆጵሮስ የሚገኘውን የብሪታንያ ወታደራዊ ጣቢያን መምታቱም ተገልጿል። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የሳውዲ የነዳጅ ማጣሪያ በእሳት የጋየ ሲሆን ሊባኖስም በመካከለኛው ምሥራቅ በተፋፋመው ጦርነት ውስጥ ተጎትታ እየገባችበት ነው። የሂዝቦላኽን የሮኬት ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በዛሬው ዕለት ደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ከባድ ድብደባ መፈጸሟን ተከትሎ ሰዎች አካባቢውን እየለቀቁ ነው። እስራኤል የሂዝቦላኽን ጥቃት ተከትሎ የአጸፋ እርምጃዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ዝታለች።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የሂዝቦላኽ መሪም የአያቶላህ አሊ ኻሚኒን ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ይጠብቀዋል ሲሉ ዝተዋል።
«ከትናንት ምሽት ጀምሮ ከዋነኛውን ኢላማ ለማዘናጋት ሞክራችኋል፤ ዋነኛው ኢላማ ዋነኛ ሆኖ ይቀጥላል፤ ኢራንንና ሊባኖስ ውስጥ ሂዝቦላኽን መደብደብ። ሂዝቦላኽ ላደረገው ሁሉ፤ እስራኤል ላይ ለተኮሰው ከባድ ዋጋ እንደሚከፍል እናረጋግጣለን። ከመስከረም 27 በፊት ወደነበሩት ደንቦች አንመለስም። የተኩስ ልውውጥ እንዲኖርም አንፈቅድም። ሂዝቦላኽን በኃይል እንደበድባለን።»
ከእና ወደተለያዩ የአረብ ሃገራት የሚደረጉ በርካታ የአውሮፕላን በረራዎች ተሰርዘዋል። መንገደኞችም ለእንግልት ተዳርገዋል። ሃገራት ዜጎቻቸውን ለማውጣት እየተጣደፉ ነው።
ቴህራን፤ የኢራን ጊዜያዊ አስተዳደር ምክር ቤት ማስጠንቀቂያ
የኢራን ጊዜያዊ አስተዳደር ምክር ቤት ኃላፊ የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተሳሳተ ስሌት ነው አሉ። አሊርዛ አራፊ ለጊዜዊ የአስተዳደር ምክር ቤቱ ኃላፊነት እንደተመረጡ ለመጀመሪያ ባደረጉት ንግግር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቀናት የተለኮሰው ጦርነት ማብቂያው ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
«በድጋሚ ዩናይትድ ስቴትስ እና ጽዮናዊው አገዛዝ በስህተት ስሌት ተመርኩዘው ያልተገባ፤ የተሳሳተና ኢፍትሀዊ የሆነ እርምጃ ወስደዋል፤ እናም ፈጣሪ ቢፈቅድ ይህ ስሌት የተሳሳተ መሆኑን ያረግጣል። ይህ ምክር ቤት፤ በመደበኛ ስብሰባዎቹ እና አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን በማድረግ የተጣለበትን ኃላፊነት ያከናውናል። ለሁሉም የጦር ኃይሎች እና ለታላቁና ለተከበረው የሀገራችን ሁሉም ዘርፎች እናንተን በማገልገል ላይ መሆናቸውን አረጋግጣለሁ።»
አያይዘውም በተቻለ ፍጥነት በሟቹ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ እግር የሚተካ መሪ እንደሚመረጥም ተስፋቸውን ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ ዛሬም ኢራን ላይ የእስራኤል ድብደባ ተጠናክሮ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፔተ ሄግሰት በበኩላቸው ለጊዜው ኢራን ውስጥ የአሜሪካ ወታደሮች እንደሌሉ ገልጸው፤ አስፈላጊ ከሆነ መኬድ እስከሚገባው ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ