የዜጎች ድህነትና ምሬት
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 9 2017“የኑሮውን ሁኔታ መቋቋም አልተቻለም፤ ምን ማድረግ እንደሚገባ ራሱ ግራ ይገባሃል” የሚሉት አንድ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የመንግስት ሰራተኛ የገቢያቸውና የወጪው አለመመጣጠን ፍጹም የከፋ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡
አስተያየት ሰጪው በእየለቱ በተጋነነ መልኩ የሚንር የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ከአብዛኛው ዜጋ እለታዊ ገቢ ፈጽሞ የማይገናኝ እንደሆነባቸውም አስረድተዋል፡፡ “የመንግስት ሰራተኞች እና የአብዛኛው ሰው የእለት ገቢ ባልጨመረበት እዛጋ የቤት ኪራይ ይንራል፤ እንደ ሽንኩርት እና ዘይት ያሉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ያለቅጥ በተጋነነና ምክንያታዊ ባልሆነ ሁኔታ ዋጋቸው ይጨምራልና ኑሮን መግፋት ከብዶናል” ነው ያሉት፡፡
የዓለም ባንክ መረጃ ስለድህነት
የዓለም ባንክ መረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ 26 ሃገራት ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት ውስጥ የከፋ የብድር አዘቅት ውስጥ እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል። አገራቱ ደካማ ኢኮኖሚ እንዳላቸው የገለጠው ሪፖርቱ በዋናነት የኮቪድ ወረርሽኝ እና ግጭቶች የሃገራቱን ኤኮኖሚ ይበልጥ ማድቀቃቸውንም ጠቁሟል።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በርካታ ዜጎቻቸው ዘርፈብዙ ድህነት ውስጥ የሚገኙ በሚል ባወጣው መረጃም የኢትዮጵያ ስም እንደ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ናይጄሪያ ካሉ አገራት ጋር ተጠቅሷል፡፡
ስለአገር እድገትና የዜጎች ተጠቃሚነት የባለሙያዎች አስተያየት
የምጣኔ ሃብት ተንታኝ አብዱልመናን መሃመድ፡ “በቅርቡ የኢትዮጵያ አዲሱ ፕሬዝዳንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርቷ እያደገ ነው ሲሉ ሰምተናቸዋል፡፡ ይህ ጥቅል ቁጥር ነው፡፡ እድገቱን ለዜጎች ስታካፍል ግን ምን ያህል ነው ሲባል የሚመጣው ነገር የኢኮኖሚ እድገት አንዱ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ህዝብ ስላላት ከብዙ አፍሪካ አገራት ነው የምታንሰው ከዚህ አኳያ፡፡ ይህ ደግሞ በሌላ ማሳያ ተስተውሏል የሚባለው የኢኮኖሚ እድገቱ ብዙ ዜጎችን ተጠቃሚ አለማድረጉን ያሳያል፡፡ ከዚህ አኳያ የሚወሰድ ልኬት ነው ወሳኙ” ብለዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ባለሙያ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ናቸው፡፡ “መጀመሪያ ተነጻጻሪ ጥቅማችን የት ላይ ነው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ለዛ ደግሞ በርካታ ህዝብ ባለበት አገርግብርና ቀዳሚ ትኩረት የሚሻ መሆኑን በመረዳት ያንን የሚያበረታታ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ በአገሪቱ የደሃ ቁጥር የሚበዛበትን ገጠር ስንደግፍ በጸጥታ የታጀበ የማያቋርጥ የኢንቨስትመንት ምልልስ ማረጋገጥ ያስፈልጋልም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችና መስእቦች ግንባታ ከኢኮኖሚ እድገት አኳያ
ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት ለቱሪዝም ሰጠሁ ባለው ትኩረት መጠነሰፊ የፓርኮች ግንባታእና ከተሞች ማስዋብ ብሎም የመስህቦች ልማት ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ያስረዳል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ግን ይህም ለአገር እድገት ብሎም ለዜጎች ተጠቃሚነት ባይነቀፍም የቅደም ተከተሉ ምርጫ ግን አሁናዊ የአገሪቱ ሁኔታን ያገናዘበ አይመስልም በማለት ይሞግታሉ፡፡ አቶ ሸዋፈራሁ፤ “አገሪቱንና ዜጎችን ከድህነት የማውጫ አንዱ መንገድ ከግብርናም ባሻገር በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ መስራት ትልቁ አዋጭ መንገድ ነው” ሲሉ ሌላው ባለሙያ አብዱልመናን ደግሞ “ግጭት ባለበት አገር ለቱሪዝም ዘርፍ የቅድሚያ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ሌሎችን አማራጮች መመልከት ዜጎችን ከድህነት የማውጫ ስልት ሊሆን ይችላል” ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር