የዘመን ሽግግር
በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ አብዛኞቹ ብሄር ብሄረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላቸውን እያበሰሩ ይገኛሉ ፡፡ የተለያዩ ቋንቋ ፣ ባህልና ወግ ያላቸው እነዚህ ሕዝቦች ወደ አዲስ ዓመት የሚሻገሩት የክረምት ወቅት ማብቃቱን ተከትሎ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ነው ፡፡ ዎላይታ ፣ ሃድያ ፣ ከምባታ ፣ ጋሞ ፣ ጎፋና ኦይዳ ብሄሮች በአዲስ ዘመን ሽግግር ላይ ከሚገኙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡ የአዲስ ዓመት በዓላት መጠሪያቸውም በዎላይታ “ ጊፋታ “ ፣ በሃድያ “ ያ ሆዴ “ ፣ በከምባታ “ መሠላ “ ፣ በጋሞ “ ዮ ማስቃላ “ ፣ በጎፋ “ ጋዜ ማስቃላ” እና በኦይዳ “ ዮኦ ማስቃላ" በመባል ይታወቃሉ ፡፡
የዎላይታ የዘመን መለወጫ ጊፋታ
የዘመን መለወጫ በዓላቸውን እያከበሩ ከሚገኙት መካከል የዎላይታ ብሄር አንዱ ነው ፡፡ የዘመን መለወጫ በዓሉም ጊፋታ በሚል ይጠራል ፡፡ የጊፋታ በዓል የዎላይታ ብሄር በራሱ ነባር የዘመን አቆጣጠር ሥሌት መሠረት የሚከናወን መሆኑን በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአገር በቀል ዕውቀት ጥናት ተቋም የባህል ባለሙያው አቶ እያሱ ጌጄቦ ይናገራሉ ፡፡
ለጊፋታ በዓል ዝግጅት አባወራዎች አስቀድመው ”ቆራጱዋ” ወይም ቁጠባ ያደርጋሉ ፡፡ በዋዜማ ቀናትም ሁሉም፡፡ ዋናው በዓል መድረሱ የሚረጋገጠው ግን ወጣቶች በሚያደርጉት የእንጨት ማሰባሰብ ዝግጅት ሥለመሆኑም የባህል ባለሙያ አቶ እያሱ ጌጄቦ ጠቅሰዋል ፡፡ የሚሰባሰበው እንጨትም በህብረት ለጉሊያ / ችቦ / መሥሪያነት ያገለግላል ፡፡
የጊፋታ እሴቶች
በጊፋታ በዓል ዝግጅት ወጣት ወንዶች የማገዶ እንጨት ይፈልጣሉ ፣ የከብቶችን ሳር አጭደው ይከምራሉ ፡፡ ልጃገረዶች ደግሞ እንሶስላ እየሞቁ ጎን ለጎን እናቶቻቸውን በሥራ ያግዛሉ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ጊፋታ ለመቀበል ያደረ ዕዳን መክፈልና የተጣሉ ሰዎች ካሉም እርቅ ማውረድ የግድ ነው ይላሉ አቶ እያሱ ፡፡
የጊፋታ በዓል የሚከበረው የጋራ የሆነ እርድ በመፈጸም መሆኑን የሚጠቀሱት አቶ እያሱ “ ማታ ላይ ወጣቶች ጉሊያ በመባል የሚጠራውን የተሰበሰበ እንጨት የማቃጠል ሥርዓት ይከናወናል ፡፡ ይህም አዲሱ ዓመት ብረሃን ይሁን የሚል መልካም ምኞትን ለማስተላለፍ ይውላል “ ብለዋል፡፡
መሠላ
በከምባታ ብሄር የዘመን መለወጫ “ መሠላ “ ሌላውየአዲስ ዓመት መሸጋገሪያ በዓል አንዱ ነው ፡፡ በብሄሩ በተለያዩ ምክንያቶች በሩቅ የነበሩ የቤተሰብ አባላት የሚገናኙት በዚሁ የመሠላ በዓል ወቅት ነው ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ነዋሪው እርስ በእርስ በመረዳዳት በዓሉን በጋራ በደስታ እንደሚያሳልፍ በከምባታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል እሴቶች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደስታ ዘለቀ ይናገራሉ ፡፡
በመሠላ በዓል የምግብ ዝግጅት ከበዓሉ ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት ጀምሮ እንደሚከናወን የሚናገሩት አቶ ደስታ “ ለበዓሉ የወተት ፣ የቆጮና የሥጋ የምግብ አይነቶች ይቀርባሉ ፡፡ ወጣት ወንዶች ፣ ልጃገረዶችና አዛውንቶች የተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖችን ይጫወታሉ ፡፡ የዘፈኖቹ ይዘትም በአብዛኛው ቀደምት ጀግኖችን የሚያወድሱ ናቸው “ ብለዋል ፡፡
የመሠላ በዓል እንደ ዎላይታው የጊፋታ በዓል ሁሉ በውስጡ ከፍተኛ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን የያዘ ነው ፡፡ ከበዓሉ በፊትም በተለያዩ ምክንያቶች ጥል ውስጥ በከረሙ ሰዎች መካከል ዕርቅ የማውረድ ሂደት ከመሠላ እሴቶች መካከል አንዱ መሆኑንም አቶ ደስታ ጠቅሰዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር