1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘመኑ የኢትዮጵያ ትውልድ ተራማጅ ነውን?

ማክሰኞ፣ የካቲት 26 2016

ትውልዱ እንዴት የሚገለጽ ነው? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ «ያለንበት ዘመን ለእግዚአብሔር ክብርን የነሣ፤ ከፍቅርና ከአንድነት የራቀ፣ ራስ ወዳድነትና በቃኝ አለማለት የወረረው፤ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የተዋጠ ትውልድ የታየበት ዘመን ነው» ብለዋል ።

https://p.dw.com/p/4dBoz
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ። ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል DW/G. Tedla HG

ትውልዱ ምን ላይ ቆሞ ይገኛል ?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዐቡነ ማትያስ «የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን፣ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ፣ ለሃይማኖትም ሆነ ለማኅበረ - ሰብ ጤናማ ህላዌ ያልተመቸ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው» ሲሉ ሰሞኑን ገልፀውታል ።

ውልዱ እንዴት የሚገለጽ ነው? ጦርነት፣ ድህነት፣ የውጭ ባሕል ተጽእኖ፣ ከጎሣ ማንነት እና ከሃይማኖት መነሻ ግጭት ባልተለያት ሀገር ውስጥ የቀጣይ ሃያ እና ሠላሣ ዓመታትን ኢትዮጵያ በዛሬው ትውልድ እንዴት ማየት ይቻላል?

ስለ ትውልዱ የሚነሱ ጥያቄዎች

ይህ የዛሬው የኢትዮጵያ ትውልድ ወል መታወቂያው እንዴት ያለ ይሆን ? ይዋደዳል? በቅጡ ተምሯልን ? ስለ ሀገር ሰንደቅ አላማ ፣ ስለ ሉዓላዊ ክብር፣ ስለ ዳር ድንበር መከበር ፣ ስለ ትውልድ ሕይወት መሻሻል ፣ ስለ ሥነ ምግባር እድገት ለለውጥ የማይተኛ ነውን ? አንድነቱስ?

«ብዙ ጊዜ የአሁኑ ትውልድ የተበላሸ ፣ የከሸፈ ትውልድ ነው ይባላል ። እኔም የዚህ ትውልድ አባል ስለሆንኩኝ ይህን ትውልድ እንደዚህ ብየ መጥራት አልፈልግም ። .... አሁን ሕዝቡ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተከፋፍሏል ። አንድነት የለውም ።»

ይህ ጉዳይ የተተወ ይመስላል

በሀገር ሁለንተናዊ የሕብረተ-ሰብ መስተጋብር ውስጥ እነዚህን መሰል ትውልድን የሚመለከቱ ጉዳዮች የእውነተኛ ውይይት ርእስ መሆን ለምን ተሳናቸው?  ይህ ከሆነ ለዚህ ችግር ተጠያቂው ማነው ? የትውልዱን ርምጃ ዝግመት የበዛበት ያደረገውስ ማን ነው ?

«በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እየተቋቋሙ ሕዝቡን ከትክክለኛ ጎዳና እያዘናበሉት የፖለቲካ መጫወቻ እያደረጉት በየጊዜው ሲፈታተኑት የኖሩት መሪዎች ናቸው ።» የትዳር እና የመገናኛ አውታር ጉዳይ አማካሪ የሆኑት አቶ ሀበነዮም ሲሳይ ጥያቄያችንን አብረው ይጠይቃሉ ።

በሀገር ሁለንተናዊ የሕብረተ-ሰብ መስተጋብር ውስጥ እነዚህን መሰል ትውልድን የሚመለከቱ ጉዳዮች የእውነተኛ ውይይት ርእስ መሆን ለምን ተሳናቸው ? 
በሀገር ሁለንተናዊ የሕብረተ-ሰብ መስተጋብር ውስጥ እነዚህን መሰል ትውልድን የሚመለከቱ ጉዳዮች የእውነተኛ ውይይት ርእስ መሆን ለምን ተሳናቸው ? ምስል Seyoum Getu/DW

«ትውልድ ራሱ ያንን ችግር እሱ ነው የፈጠረው ወይስ የችግሩ ሰለባ ነው?» በማለት።

ቅዱስ ፓትርያርክ ዐቡነ ማትያስ ስለ ትውልዱ ምን አሉ ?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ «ያለንበት ዘመን ለእግዚአብሔር ክብርን የነሣ፤ ከፍቅርና ከአንድነት የራቀ፣ ራስ ወዳድነትና በቃኝ አለማለት የወረረው፤ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የተዋጠ ትውልድ የታየበት ዘመን ነው» ብለዋል ።

አክለውም «የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን፣ ከቅድስና ይልቅ ነውረ ኃጢአትን፤ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ፣ ለሃይማኖትም ሆነ ለማኅበረ - ሰብ ጤናማ ህላዌ ያልተመቸ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው» በማለት አዝማሚያው አደገኛ እንደሆነ ገልፀዋል ።

የትዳር እና የመገናኛ አውታር ጉዳይ አማካሪው አቶ ሀበነዮም ሲሳይ የትውልዱ የእኔነት ጉዞ ድካም አቅላይ የነበሩ የሕበረት አንጓዎችን መበጠሱን ጠቅሰዋል ።

«እንደ ማሕበረሰብ ተጋግዘን የምኖረውን፣ ድካማችንን የምናቀልበት ነገር አሁን ላይ በእኔነት ስሜት ተጣቦ የዜሮ ድምር ውጤት አይነት እየሆነ ነው ያለው ።» 

ትውልዱ ምን ላይ ቆሞ ይገኛል ?

ትውልድ ጦርነት ሲጋጋል ተቆጭም ተደማጭም ካጣ ምን ይሆናል? የጭካኔ ድርጊቶች ሲበራከቱ ፣ ለሕግ፣ ለሃይማኖት ተገዢነት ሲሸረሸር ፣ ልቅነት ሲስፋፋ ትውልዱ ምን ላይ ቆሞ ነው ? የሚለውን የጠየቅናቸው አቶ ሀበነዮም ሲሳይ ምላሽ አላቸው።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ የዚህ ወቅት ትውልድ እንዴት ይገለፃል ? ምን እየሠራ ነው ?
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የዚህ ወቅት ትውልድ እንዴት ይገለፃል ? ምን እየሠራ ነው ? ምስል Solomon Muchie/DW

«እንደ ጥንቱ ሥርዓት ወይ ማንነታችንን ፣ አኩሪ ታሪካችንን የምንለውን የእኛነታችንን መገለጫ አጥብቀን አልያዝንም ። ጥለነዋል ። አራክሰነዋል ። ወይም ደግሞ አደገ ፣ ሰለጠነ እንደሚባለው ዓለም በአስተሳሰብም አልላቅንም፣ ራሳችንን መቻል የምንችልበትንም ጥበብ እና ትምህርትም አልያዝንም ። ስለዚህ እንዳደጉት ሀገራትም አልሆንንም እንደነበረው ማንነታችንም አልሆንም ።»

ይህ ከሆነ እንግዲያውስ ምን ይደረግ ?

«መንግሥት በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራት አለበት ። ወጣቱን እንደገና ማደራጀት አለበት ። ወጣት በሚገባ መደራጀት አለበት ። ተኮትኩቶ ማደግ አለበት ።» አቶ ሀበነዮም እንደሚሉት ደግሞ፦ ሁሉም ከወቃሽነት ወጥቶ ይቅርታን ፣ ምስጋናን የሚተገብር ትውልድ ለመሆን የድርሻን መወጣት ያሻል ።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ የዚህ ወቅት ትውልድ እንዴት ይገለፃል ? ምን እየሠራ ነው ? ውይይት ያሻዋል ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ