1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነት ተፈናቅለዉ ችግር ላይ የሚገኙ ሴቶች

ዓርብ፣ የካቲት 29 2016

ዛሬ ዓለማቀፉ የሴቶች ቀን በመላው ዓለም ስከበር ውሏል፡፡ እለቱ ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች እኩልነትና ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ ምቹ የኑሮ አውድ እንዲኖራቸው ማስገንዘብና መወትወት ላይ ያተኩራል፡፡ በኢትዮጵያ በግጭት ፈተና ለመፈናቀል ተዳርገው አስከፊውን ኑሮ ሚገፉ እናቶች ግን ከዚህም የላቀ ትኩረትን ይሻሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4dJmA
ፎቶ ማህደር፤ የተፈናቀሉ ሴቶች
ፎቶ ማህደር፤ የተፈናቀሉ ሴቶችምስል Alemenew Mekonnen/DW

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን እና የጦርነቱ ሰለባ ሴቶች በኢትዮጵያ

በጦርነት ተፈናቅለዉ ችግር ላይ የሚገኙ ሴቶች 

ዛሬ ዓለማቀፉ የሴቶች ቀን በመላው ዓለም ስከበር ውሏል፡፡ እለቱ ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች እኩልነትና ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ ምቹ የኑሮ አውድ እንዲኖራቸው ማስገንዘብና መወትወት ላይ ያተኩራል፡፡ በኢትዮጵያ በግጭት ፈተና ለመፈናቀል ተዳርገው አስከፊውን ኑሮ ሚገፉ እናቶች ግን ከዚህም የላቀ ትኩረትን ይሻሉ፡፡

የግጭት ፈተና ለሴቶች

ዓለምጸሃይ ገብረዮሓንስ ሴቲት ሁመራ ከተባለ አከባቢ በ2013 ኣ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በግጭቱ በመፈናቀል ቤተሰቦቻቸውን በትነው የተፈናቃይነት ኑሮን ለመግፋት ተገደዋች፡፡ የ38 ዓመቷ ዓለምፀሓይ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ሁለት ጊዜ በመፈናቀል ከአንዱ ልጇ ጋር አሁን ላይ በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ በተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ስትገኝ፤ አንደኛውን ልጇን ደግሞ በዚያው በሴቲት ሁመራ ጎረቤት ጋር ጥላ ግጭቱን ሸሽታ መውጠቷን ታስረዳለች፡፡ ይህ የተፈናቃይነት ህይወት በተለይም እንደ እናት ፈታኙ ስትል ትገልጻዋለችም፡፡ “ልጅ ዞ ተፈናቃይነት በጣም ከባድ ነው፡፡ አንዱን ልጄን ብይዝም አንዱን በዚያው ለጎረቤት ነው ጥዬ የመጣሁ፡፡ ህ ለእናት ከባድ ነው፡፡ ፈጣሪ ብፈቅድ ፍላጎታችን ቤተሰቦቻችንን ሰብስበን ሰርጠን መኖር ነው” ብላለች፡፡ ዓለምጸኃ ለዚህ ደግሞ እንደ እናት ስለ ሰላም መስፈን አብዝታ ትሻለች፡፡

የተፈናቃዮች እሮሮ

ዘሪቱ ሁሴን ደግሞ ከምእራብ ኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ዞን በ2013 ዓ.ም. በአከባቢው በተቀሰቀሰው ግጭት ተፈናቅለው ወደ ደቡብ ወሎ ቃሉ ተፈናቃዮች ካምፕ ከገቡ ጊዜው ወደ ሶሰርተኛ ዓመቱ እየገሰገሰ ነው፡፡ የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ዘሪቱ የመጀመሪያዋን ልጃቸውን በሞት ብያጡም ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ከግጭቱ ሸሽተው ወሎ ከትመዋል፡፡ ግጭቱ ከመፈናቀልም አልፎ ትዳራቸውንም ማፍረሱን የሚስረዱት ተፈናቃይዋ፤ እንደ እናት አሰልቺ ያሉትን የግጭት መዘዝ ተሻግረው ስላምን አጥብቀው ይሹአታል፡፡ “የተፈናቃይነት ህይወት ከባድ ነው በአንድ ቤት 20-25 አባወራ ሆነን እንኖራለን፡፡ ከመሞት መሰንበት በሚል እንጂ ይህ ህይወት ይከብዳል” ይላሉ፡፡

ሞሚና ደሳለኝ የተባሉ የስድስት ልጆች እናትም በተመሳሳይ ከሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በ2013 ዓ.ም. ተፈናቅለው በዚያው በቃሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ ከትመዋል፡፡ በዚህ ህይወት የእናትነት ፈተና ያሉትን ብርቱ ውጣውረድ ሲያስረዱም፤ “የእናትነት ያህል ምንም ማድረግ ይሳነኛል፡፡ ልጆቼ ሲለቅሱ አብረ ከማልቀስ ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ መጣም ቀረ የሰው እጅ አይተን ነው ኑሮ የምንገፋው” ብለዋል፡፡

ፎቶ ማኅደር፤ ሴቶች በደብርሃን
ፎቶ ማኅደር፤ ሴቶች በደብርሃን ምስል Eric Lafforgue/imago images

የሴቶች ቀን አንድምታ ለተቸገሩ ሴቶች

ዛሬ ዓለማቀፍ የሴቶች ቀን በመላው ዓለም ታውሶ ውሏል፡፡የሴቶችና ወንዶች እኩለነትን ማረጋገጥ የሚሉ መልእክቶችም በጉልህ ተስተጋብቷል፡፡ ለነዚህ በግጭት ተፈናቅለው ለሚንከራተቱት ደግሞ ጥያቄና ፍላጎታቸው ከዚያም ይልቃል፡፡ ሰላማዊት ካሳዬ በኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የነጻ ህግ አገልግሎት አስተባባሪ ናቸው፡፡ እንደ ዛሬ ባሉ ለሴቶች ልሰጥ የሚገባውን ትኩረት በሚያስታውሱ ቀናት ቅድሚያ ትኩረቱን በችግር ላይ ላሉ ሴቶች መድረስ ግብ ተደርጎ ሊሰራ የሚገባ ነው ባይ ናቸው፡፡ “ግጭቶች ሲነሱ ለትቃት በመጋለት ሴቶች ቀዳመሚ ናቸው፡፡ በብዛት እራሳቸውን መከላከልና አስቀድመው ከአደጋው ማምለት ቀዳሚ ፈተና ይሆንባቸዋል” ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከዓለመማቀፍ የሰብኣዊ ተቋማት እስከ የመንግስት የህግ ረቂቆች እነዚህን ልዩ ትኩረት የሚሻቸውን ሴቶች ባይዘነጉ በሚል አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ “እነዚህ በግጭት የተፈተኑ፤ ከዚያም የተፈናቀሉ ሴቶች እንዲጠበቁ ባሉበት ሁሉ የህግ ከለላን እንዲያገኙ መወትወት ያስፈልጋል፡፡ አገራዊ የህግ ረቂቆች እንኳን ስወጡ እነሱን ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ መሆን ይገባልም” ብለዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ