1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የየካቲት 2 ቀን 2018 የዓለም ዜና

ሰኞ፣ የካቲት 2 2018

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ግዛት ሰራዊቷን እንድታስወጣና ከኢትዮጵያ አማጽያን ጋር የምታደርገውን ማንኛውም ትብብር እንድታቆም በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቀረበላትን ጥሪ ውድቅ አደረገች። ሶማሊያና ሳውዲ ዓረቢያ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሱዳን ወደ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት (ኢጋድ) እንደምትመለስ አስታወቀች። አለፈው ሳምንት በሞስኮ በአንድ የሩስያ ጀነራል በተፈጸመው የግድያ ሙከራ የፖላንድ እጅ አለበት ሲል የሩስያ የአገር ውስጥ የስለላ መስሪያቤት አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/58O7F

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር ማስተባበያ

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ግዛት ሰራዊቷን እንድታስወጣና ከኢትዮጵያ አማጽያን ጋር የምታደርገውን ማንኛውም ትብብር እንድታቆም በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቀረበላትን ጥሪ ውድቅ አደረገች። የኤርትራው የማስታወቂ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው በሰጡት ምላሽ ውንጀላውን ውድቅ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዎን ጢሞቲዎስ በአለፈው ቅዳሜ ለኤርትራው አቻቸው በጻፉት ደብዳቤ «ባለፉት ጥቂት ቀናት የታዩት ክስተቶች የኤርትራ መንግሥት ተጨማሪ ግጭት የማባባስ መንገድ መምረጡን ያሳያሉ» ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም «ኤርትራ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣና ከአማጽያን ጋር የምታደርገውን ማንኛውንም ዓይነት ትብብር እንድታቆም» ሲሉ ጠይቀዋል። ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ዕልባት እንዲሰጠው በኢትዮጵያ በኩል ዝግጁነት እንዳለ በማከል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ለዚሁ ወቀሳ በሰጡት ምላሽ « የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትላንት ባወጡት መግለጫ በኤርትራ ላይ የሰነዘሩት ግልጽ ውሸትና የተፈበረከ ወቀሳ፤ ድምጸቱና ይዘቱ አስደናቂ፣ ድብቅ ፍላጎትና አጠቃላይ ዓላማን የሚያንጸባርቅ ነው» ብለውታል። « በሚያሳዝን መልኩ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በኤርትራ ላይ የሚደረገው ተቀባይነት የሌለው የጠብ ጫሪነት ዘመቻ ቀጣይነት የሚያሳይ ርምጃ ነው» ያሉት ሚኒስትሩ አክለውም «የኤርትራ መንግስት ከዚህ በፊት እንደገለጸው ትርጉም የለሽ ውዝግብ በመግጠም ሁኔታውን የሚያባብስ ቤንዚን የማርከፍከፍ ፍላጎት የለውም» ብለዋል።

ሶማሊያና ሳውዲ ዓረቢያ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውን 

ሶማሊያና ሳውዲ ዓረቢያ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። የመግባቢያ ስምምነቱን የሳውዲ የመከላከያ ሚኒስትርና የሶማሊያው አቻቸው ጋር በሪያድ መፈረሙን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አክሏል።
የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ የመግባቢያ ስምምነቱ ሶማሊያ የመሬት፣ የባሕርና የአየር ክልሏን ለመጠበቅ የሚያስችላትን የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችንና የጦር መሳሪያዎችን ከሳውዲ ድጋፍ እንድታገኝ ያስችላታል።
ስምምነቱን በሪያድ የተፈራረሙት የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር አሕመድ ሞሊም ፈቂ እና የሳውዲ አቻቸው ልዑል ካሊድ ቢን ሳልማን እንደሆኑ መግለጫው አክሏል። የሳውዲ ዓረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር  ልዑል ካሊድ ቢን ሳልማን በኤክስ ገጻቸው ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ቢገልጹም ዝርዝር ነገሮች ከመግለፅ ተቆጥበዋል። 
እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷንና በቀጠናው ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ ሶማሊያ አጋር ፍለጋ ስታማትር መቆየቷን ዘገባው አክሏል።  


ሱዳን ወደ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት (ኢጋድ) እንደምትመለስ አስታወቀች። 

ሱዳን ወደ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት (ኢጋድ) እንደምትመለስ አስታወቀች። ሱዳን ከኢጋድ አባልነት ላለፉት ሁለት አመታት እራሷን ያገለለችው ድርጅቱ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ወደ ስብሰባ በመጋበዙ ነበረ።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ «የሱዳን ሪፐብሊክ መንግስት በኢጋድ መሉ ተሳትፎ የማድረግ ተግባሩን እንደገና ይጀምራል» ብሏል። የሱዳን መንግስት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በጥር 2024 ከኢጋድ አባልነት እራሱን ያገለለው፤ ኢጋድ በኡጋንዳ በተካሄደው ስብሰባው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዥ እንዲገኙ በመጋበዙ ነው። በወቅቱ የሱዳን መንግስት ድርጊቱን «በሱዳን ሉዓላዊነትና የውስጥ ጉዳይ መግባት ነው» ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።
ሱዳን ወደ ኢጋድ መልሳ ለመቀላቀል የወሰነችው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት የበላይ ሃላፊ ዶክተር ገበየሁ ወርቅነህ እና የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ካሚል እድሪስ በአለፈው ጥር ወር ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ እንደሆነ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። 

የእስራኤል ጦር ሰራዊት በጋዛ ሰርጥ 4 ፍልስጤማውያንን መግደሉን አስታወቀ።

የእስራኤል ጦር ሰራዊት በጋዛ ሰርጥ 4 ፍልስጤማውያንን መግደሉን አስታወቀ። ጦሩ እንዳለው ፍልስጤማውያኑ የተገደሉት በአካባቢው ወደተሰማሩ የእስራኤል ጦር አባላት በመተኮሳቸው ነው።
የእስራኤል የመከላከያ ሰራዊት ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ ፍልስጤማውያኑ ታጣቂዎች በራፋሕ ከአንድ ቱቦ ሥር ሆነው ወደ እስራኤ ሰራዊት አባላት ቢተኩሱም በወታደሮቹ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል።
መግለጫው አክሎም ድርጊቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በጥቅምት 10 ቀን 2025 በእስራኤልና ሐማስ መካከል የተደረሰውን «የተኩስ አቁም ስምምነትን የሚጥስ» ሲል ገልጾታል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍልስጤማውያን ታጣቂ ቡድን ሐማስ በኩል ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ እንደሌለ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።  
በራፋሕ በርካታ ፍልስጤማውያን ታጣቂዎች በቱቦዎች እየተደበቁ እንደሚገኙና የእስራኤል ጦር በአለፈው ወር  በርካታዎቹን ማሰሩንም ለማወቅ ተችሏል። የእስራኤል ወታደሮች በየሥርቻው የተደበቁትን ፍልስጤማውያን ታጣቂዎችን ለማጥፋት የጀመረውን ሥምሪት እንደሚቀጥልም ጦሩ አክሏል።
በእስራኤልና ሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በጋዛ ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን ለጥቃቶቹና ለተኩስ አቁም ስምምነቱ መጣስ አንዱ ሌላኛውን እንደሚከሱ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በሊባኖስ በሕንጻ መደርመስ አደጋ 15 ሰዎች ሞቱ

በሰሜናዊ የሊባኖስ ግዛት በምትገኝ ትሪፖሊ ከተማ አንድ ሕንጻ ተደርምሶ 15 ስቪሎች መሞታቸውን የሐገሪቱ የስቪል መከላከያ ባለስልጣን አስታወቀ። ሕንጻው የተደረመሰው በእርጅና ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ሃላፊው አክለዋል።
 የድርጅቱ የበላይ ሐላፊ ጀነራል ኢማድ ክሪሽ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሕይወት የተረፉትን ሰዎች ለማፈላለግ በተደረገው የነብስ አድን እንቅስቃሴ 8 ሰዎች በሕይወት ተርፈዋል። ትላንት የደረሰውን የመደርመስ አደጋን ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ተቃዎሞአቸውን አሰምተዋል።   
ከከተማዋ ነዋሪዎች 70 በመቶው በድሕነት የሚነሩ እንደሆነና በከተማዋ ያሉ የመኖሪያ ሕንጻዎች ለረዥም ዓመታት ጥገና የናፈቃቸው እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዋና ከተማዋ ቤይሩትና በትሪፖሊ ቢያንስ 16,000 የሚሆኑ መኖሪያ ሕንጻዎች የመደርመስ አደጋ እንደተደቀነባቸው የጀርመን ዜና አገልግሎት ያሰራጨው መረጃ ያመላክታል።

በአንድ የሩስያ  ጀነራል በተፈጸመው የግድያ ሙከራ የፖላንድ እጅ አለበት ሲል የሩስያ የአገር ውስጥ የስለላ መስሪያቤት ከሰሰ።

በአለፈው ሳምንት በሞስኮ በአንድ የሩስያ  ጀነራል በተፈጸመው የግድያ ሙከራ የፖላንድ እጅ አለበት ሲል የሩስያ የአገር ውስጥ የስለላ መስሪያቤት አስታወቀ። መስሪያቤቱ በድረ ገጹ ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫ በድርጊቱ የፖላንድ የስለላ ድርጅት ተሳትፏል ሲል ከሷል።
በአለፈው ሳምንት የሩስያ የወታደራዊ መረጃ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ጀነራል ቭላድሚር አለክስዬቭ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በሚገቡበት ሰዓት ከታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ክፉኛ መቁሰላቸውን ይታወሳል። የሩስያ የጸጥታ ሐይሎች ባደረጉት ክትትል የግድያ ሙከራ አድራጊዎቹ በቁጥጥር ሥር ያዋሉ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ በሰጡት የእምነት ቃል በድርጊቱ የፖላንድ የስለላ ክፍል መሳተፉን እንደገለጹ ታውቋል።
የድርጊቱ ፈጻሚዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በነሐጤ 2025 በዩክሬይን የስለላ መስሪያቤት መመልመላቸውንና የሩስያ የጉዞ ሰነድ ተሰርቶላቸው ወደ ሞስኮ እንዲገቡ መደረጉን፤ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከፈጸሙ በኋላ 30,000 የአሜሪካ ዶላር እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው ማመናቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ፈረንሳይ በግድ የተመለሱ ስደተኞች የሕግ ባለሙያ ድጋፍ አያገኙም መባሉን

ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ፈረንሳይ በግድ የተመለሱ ስደተኞች የሕግ ባለሙያ ድጋፍና የትርጉም አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን የሐገሪቱ የእስረኞች ተቆጣጣሪ መስሪያቤት አስታወቀ። መስሪያቤቱ ዛሬ ይፋ ባደረገው ዘገባ ስደተኞቹ ስለቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው ምንም እንደማያውቁ አክሏል።
ዩናይትድ ኪንግደምና ፈረንሳይ በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ የሚሻገሩ ስደተኞች መልሰው ወደ ፈረንሳይ እንዲላኩ፤ በምትካቸው ደግሞ ፈረንሳይ ውስጥ የስደተኝነት ጥያቄያቸውን በሕጋዊ መንገድ ያቀረቡትን ዩናይትድ ኪንግደም  እንድትቀበል መስማማታቸው ይታወቃል። በዚሁ ስምምነት መሰረት ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ፈረንሳይ የተመለሱ ስደተኞች ጉዳያቸውን ለማስረዳት የትርጉም አገልግሎት እንደማያገኙና የሕግ ባለሙያ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው ነው የፈረንሳይ ይእስረኞች ተቆጣጣሪ መስሪያቤት ያስታወቀው።
ከፈረንሳይ በእንግሊዝ የባሕር ወሽመጥ በአነስተኛና ደረጃቸውን ያልጠበቁ  የፕላስቲክ ጀልባዎች ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች ሕይወታቸው እንደሚያጡም ዘገባው አክሏል።  

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ፀሐይ ጫኔ 
 


 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።