1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ወጣቶች

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መጋቢት 6 2016

ለአንድ ሳምንት ያህል የዘለቀው እና ሩሲያ የተካሄደው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ባለፈው ሳምንት ሀሙስ ተጠናቋል። በዚህ ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው 70 የሚሆኑ ወጣት ኢትዮጵያውያን ተካፍለው ነበር።ስለ ፌስቲቫሉ እና ተሞክሯቸው ጠይቀናል።

https://p.dw.com/p/4dYR6
የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ወጣቶች
የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ወጣቶችምስል Privat

የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ወጣቶች

ሩሲያ ያዘጋጀችው እና ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀው የዘንድሮው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል  «መጪውን ጊዜ አብረን እንጀምር» የሚል መሪ ቃል ነበረው። 
ከ180 ሀገራት የተውጣጡ 20000 የሩሲያ እና የውጭ ሀገራት ተሳታፊዎች እንደተገኙበት የፌስቲቫሉ ድረ ገፅ ይጠቁማል። ፌስቲቫሉ እጎአ ከመጋቢት 1 እስከ 7 ቀን ድረስ እንዲካሄድ የወሰኑት ደግሞ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው።  70 የሚሆኑ ወጣት ኢትዮጵያውያንም በዚህ ዝግጅት ላይ ተገኝተዋል።  ከእነዚህ አንዱ ጋዜጠኛ ተሾመ ኃይሉ ነው።  ተሾመ በመደበኛ ስራው ጋዜጠኛ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የኮሚኒኬሽን እና አድቮኬሲ ዳሬክተር ነው። በዚህ ዝግጅት ላይ ከኢትዮጵያ የተሳተፈው  የልኡካን ቡድን እንዴት  እንደተውጣጣ ገልፆልናል።  «በኢትዮጵያ ከሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በዋናነት ያስተባበረው የወጣቶች ምክር ቤቱ ነው።» የሚለው ተሾመ በጋራ በመቀናጀት ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ሲሰሩ እንደነበር ይናገራል።

ወጣቶቹ ሀገራቸውን እንዴት አስተዋወቁ?

ባህል፣ ስፖርት፤ ሚዲያ፤ ሳይንስ እና ትምህርት ተሳታፊ ወጣቶቹ ከተሰማሩበት ዘርፎች ጥቂቶቹ ናቸው። «ከየክልሉ እና ከየወጣት አደረጃጀቱ  ኢትዮጵያን ወክለው ሊያስተዋውቁ ይችላሉ ተብለው የተመረጡ ወጣት ኢትዮጵያውያን ነን የተጓዝነው» የምትለው የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት፤ ፈዲላ ቢያ  ኢትዮጵያ የሰው ዘር እና የቡና መገኛ መሆኗን ከመንገር ባሻገር ሀገራችንን በደንብ የምናስተዋውቅበት አጋጣሚም አግኝተን ነበር ትላለች። « ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ስላለችው የኢኮኖሚ እድገት፤  ኢትዮጵያ በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዓለምን እየፈተነ ያለ የአየር ንብረት ላይ የራሷን አስተዋፅዎ እያበረከተች እንደሆነ ባገኘናቸው መድረኮች ሀገር የማስተዋወቅ ስራ ሰርተናል» ፈዲላ የሴት ኢትዮጵያውያን ልኡካን ተሳትፎም ከፍተኛ የሚባል ነበር ትላለች። « በፐርሰንት ደረጃ ሲታይ ከ50 በላይ ነው የሚሆነው። ከነበሩት ተሳታፊዎች የሱቶች ተሳትፎ ሰፊ ነበር። 

የቡና ማፍላት ሥነ ሥርዓት
« የሀገራችንን የቡና ሥነ ሥርዓት እዛ አዘጋጅተን ነበር። እዛ ላይ ብዙ ሰዎች ተገንተዋል።» ምስል Privat

የቡና ማፍላት ሥነ ሥርዓት

ዓለምፀሀይ  ጋዲሳ ከሴት ልኡካኑ ሌላኛዋ ናት። የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ስትሆን ወደ ሩሲያ የሄደችው  የመስሪያ ቤቷን የወጣቶች ዘርፍ ወክላ እንደሆነ ነግራናለች።   በፌስቲቫሉ ላይ ለሴቶች ተብሎ የተለየ የተዘጋጀ ነገር ባይኖርም ብዙ ሴቶች ተሳታፊ እንደነበሩ እና ጥሩ ተሞክሮ እንደነበራት ነግራናለች። « እውነቱን ለመናገር በጣም ጥሩ ነገር ነው ያገኘሁበት። ትልቁ እድል ከብዙ ሀገራት ወጣቶች ጋር የመገናኘት እና የመነጋገር፣ ስላለው ልዩነት እና አንድነት፤ ስለ አኗኗራችን ልምድ ልውውጥ ነበር። ፌስቲቫሉ ላይ የተሰጡ ስልጠናዎች ነበሩ» በማለት የነበራትን ተሞክሮ ትዘረዝራለች። « የሀገራችንን የቡና ሥነ ሥርዓት እዛ አዘጋጅተን ነበር። እዛ ላይ ብዙ ሰዎች ተገንተዋል።» በማለት ለሁሉም ወጣቶች ትምህርት የሚገኝበት ፌስቲቫል እንደሆነ ትናገራለች። 

ሌላው ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዩሱፍ መሀመድ ነው። « እንደ ወጣት አመራር ድርሻውን አግኝተን ነው ወደ ሩሲያ ሶቺ የሄድነው» የሚለው ዩሱፍ ሁሉም ልኡካን 7 ቀናቱንም የቆዩ ሲሆን ሌሎች አሁን ድረስ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶች እንዳሉም ገልፆልናል። « ፕሮግራሙ ሁለት አይነት ነው። ዋናው ፌስቲቫል በሶቺ የተደረገው ነው። 70ዎቹም ሰባቱን ቀን ተሳትፈዋል።  ግን በሌሎች አካባቢዎች የተከናወኑ ፌስቲቫሎችም ነበሩ። » በማለት እስካሁን ድረስ በጉብኝት እና በተሳትፎ ላይ ያሉ ወጣቶች እንዳሉ ያብራራል።
ዩሱፍ« ጥሩው ነገር ብዙ ልምድ ማግኘት መቻሌ ነበር ይላል» ። ሁሉም ያነጋገርናቸው ወጣቶች በዚህ የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ሲካፈሉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር። « ሁላችንም የራሳችንን ሚና እና ድርሻ የተወጣንበት ሁኔታ ስለነበር በጣም ደስ የሚል ነበር። እና ወጣት ለወጣት ግንኙነቱ በጣም የተጠናከረ ነበረ።»

የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ወጣቶች
የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ወጣቶችምስል Privat

የሩሲያ ወረራን ከሚቃመሙ ሀገራት የመጡ ወጣቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል?

የዘንድሮው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል የተካሄደው በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው። ጋዜጠኛ ተሾመ የጦርነት ስጋትን በተመለከተ ዝግጅቱ የነበረው በደቡባዊ ሩሲያ ስለነበር « ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው የነበረው። » ይላል። ሩስያ በዩክሬይን ላይ ያደረገችውን ወረራከሚቃመሙ ሀገራት የመጡ ወጣቶች በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ቢሆንም ጦርነቱ ርዕስ እንዳልነበር ይናገራል። « ምንም እንኳን በጦርነቱ ላይ የተለያዩ አስተሳሰቦች ቢኖሩም በፌስቲቫሉ የተሳተፉ ወጣቶች ግን ብዙም ስለዚህ ጦርነት ጎራ የመያዝ ነገር አልነበራቸው» በማለት ይልቁንስ ትኩረታቸው «መጪውን ጊዜ አብረን እንጀምር» በሚለው መሪ ቃል እንደነበር ይናገራል።

እጎአ በ2017 ዓም ከተካሄደው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮው ዝግጅት ላይ ለመካፈል 300 ሺህ ማመልከቻወች ከተለያዩ ሀገራት ገብተው እንደነበር እና ይህም በስድስት እጥፍ የሚበልጥ እንደነበር የፌስቲቫሉ ድረገፅ ይጠቁማል።የተላኩለትን ማመልከቻዎች ለይቶ ዝግጅቱ ላይ የሚካፈሉትን ወጣቶች የወሰነው የሩሱያ መንግሥት እንደሆነ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ዓለምፀሀይ ገልፃልናለች። 
ፈዲላ ቢያ  የዓለም የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ስትካፈል የመጀመሪያዋ ቢሆንም የተለያዩ የወጣቶች መድረኮች ላይ የመሳተፍ እድል አግኝታለች። ሌሎች ወጣቶችም  እንደ የዓለም የወጣቶች ፌስቲቫል እና መሰል መድረኮች ላይ መካፈል እንዲችሉ ወጣቶች በቅድሚያ በየአደረጃጀት ቢታቀፉ ጥሩ ነው ናይ ናት።  « ሀገራችንን ወጥቶ ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን እዚህ ያለውንም ስራ ለመስራት በየአደረጃጀቱ መታቀፍ ቢችሉ የተሻለ ነው።»

ልደት አበበ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር