1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐማራ ክልል ግጭት መንስኤና የወደፊቱ ሁኔታ-ዉይይት

ዓርብ፣ መጋቢት 20 2016

በግጭቱ በሰብዓዊ መብት ጥቃት የሚጠየቁ ግለሰቦችላይ ማዕቀብን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎችንና ግፊቶችን ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶክተር ደምሴ፣የሽግግር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሂደት መካሄድ እንዳለበት አብራርተዋል። በዘር ላይ የተመሠረተ ያሉት ህገ መንግስት በአዲስ መተካት እንዳለበትም እንዲሁ።

https://p.dw.com/p/4eFbW
በዐማራ ክልል ለተከታታይ ዓመታት በተደረጉ ግጭቶች ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ (ፎቶ ከክምችታችን)
ባለፉት 5 ዓመታት በተደጋጋሚ ጦርነትና ግጭት ከተጎዱ የዓማራ ክልል አካባቢዎች አንዱ (ፎቶ ከክምችታችን)ምስል Seyoum Getu/DW

የዐማራ ክልል ግጭት መንስኤና የወደፊቱ ሁኔታ-ዉይይት

     

የዐማራ ክልልን የሚያዉከዉን  ግጭትለማስቆም ስልታዊ ለውጥ ማድረግና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ የሕግ ባለሙያዎች አስታወቁ።የግጭቱን መነሻ፣ያለበትን ደረጃና የወደፊቱን ሁኔታዎች በዳሰሰ ዉይይት ላይ የተካፈሉ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት የግጭቱ መሠረታዊ ምክንያቶች መልስ ማግኘት አለባቸዉ፤ ተጠያቂነትም ሊሰፍን ይገባል።ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በተደረገዉ የፓናል ዉይይት ላይ የኢትዮጵያና የሕዝብ ዓለም ዓቀፍ ህግና ፖሊሲ የተባለ ቡድን ባለሙያዎች በአስረጂነት ተሳትፈዋል።

የግጭቱ መነሾና የተከተሉ ሁኔታዎች

የግጭቱ መነሾ፣ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው የዐማራው ሕዝብ ስር የሰደዱ ቅሬታዎች፣ከፖለቲካ መገለል፣ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግድያዎችንና መጠነ ስፊ መፈናቀሎች መሆናቸው ተመልክቷል።እነዚህ ተግዳሮቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ተባብሰው፣በቀጠለው አስከፊ ግጭት፣ በክልሉ በሰላማዊ ዜጎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችና አሰቃቂ ወንጀሎች መፈጸማቸው ይነገራል።

የህዝብ ዓለም አቀፍ ህግና ፖሊሲ የተባለው ተቋም ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት አምባሳደር ስቴቨን ራፕ፣ ጦርነቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት ሲናገሩ የሚከተለውን ተናግረዋል።

"ባለፉት ሶስት አመታት ተኩል በኢትዮጵያ የታዩት ግጭቶች ለሰላማዊ ሰዎች እጅግ አደገኛ በሆነ መንገድ ሲካሄዱ ቆይተዋል።"

ዘላቂ የግጭት አፈታት መንገዶችን አስመልክቶ ፕሮፌሰሩ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባም አስረድተዋል።ከዚህ አኳያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ወንጀሎች በሚገባ መሰነድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ሚና

ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ዶክተር ደምሴ አለማየሁ በበኩላቸው፣ በዐማራ ክልል በቀጥለው ግጭት የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ሚና ምን መሆን እንደሚገባው ሲያስረዱ፣ ችግሩን በሚገባ መገንዘብ እንዳለበቸው አሳስበዋል።

"ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በመጀመሪያ ሊወስድ የሚገባው እርምጃ፣በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል መገንዘብ ነው።"

በጦርነትና ግጭት በተደጋጋሚ ከተጎዳዉ የዓማራ ክልል አንዱ
ከዐማራ ክልል አንዱ አካባቢ።መጀመሪያ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በቅርቡ ደግሞ በአማራ ክልል ግጭት ምክንያት የክልሉ ሕዝብ እየተጎዳ ነዉ (ፎቶ ከክምችታችን)ምስል Seyoum Getu/DW

በግጭቱ በሰብዓዊ መብት ጥቃት የሚጠየቁ ግለሰቦችላይ ማዕቀብን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎችንና ግፊቶችን ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶክተር ደምሴ፣የሽግግር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ዴሞክራሲያዊ  የሆነ ሂደት መካሄድ እንዳለበት አብራርተዋል። በዘር ላይ የተመሠረተ ያሉት ህገ መንግስት በአዲስ መተካት እንዳለበትም እንዲሁ።

የዐማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ በዓለም አቀፍ የህግ ተቋማት አማካይነት የፓናል ውይይት እንዲካሄድበት መደረጉ፣ ያለውን አንድምታ በተመለከተ  የጠየቃቸው አምባሳደር ብርሃነመስቀል ነጋ፣ በጉዳዩ አስረጂነት ከተጋበዙ ምሁራን አንደኛው ናቸው።

"በዐለም አቀፍ ደረጃ የዐማራው ጉዳይ ወደፊት አየመጣ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃ ምንድናቸው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ሁሉ፣ ማዕቀብ መጣሉ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ የጦር መኮንኖችም ሆኖ ባለስልጣናት ላይ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ ሁሉ ምን ምን እንደሆኑ የተብራራ ነው። ወደፊት እንግዲህ በቀጣይነት በተግባር ሊሰራ የታቀደውን ሥራ የሚያመለክት ነው ማለት ነው።"

ሰላምና ፍትሕ

አምባሳደር ብርሃነመስቀል ለቀውሱ መፍትሔ ለማበጀት፣ሰላምና ፍትሕ አብረው መሄድ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

"በሰቆቃ የሚኖር ህዝብ፣ ብዙ በደል ብዙ ግድያ፣ስደት በየቀኑ እየተፈጸመበት ያለ ሕዝብ፣ፍትሕ ይሻል።ያንን ፍትሕ ደግሞ ያገኛል በግድ።ምክንያቱም ያንን ፍትሕ ካላገኘ፣ ሰላም አይኖርም ኢትዮጵያ ውስጥም የትም። እና ሰላምና ፍትሕ  አብረው ነው የሚሄዱት።"ብለዋል። 

 ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ