የዐማራ እና የትግራይ ሕዝቦች ትብብር
ዓርብ፣ መጋቢት 4 2018
''ተስፋ ለሰላም'' የዐማራና የትግራይ ህዝቦች ወደተባበረ ትግል የመሸጋገር ተነሳሽነት እያሳዩ መሆናቸው፣ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረለት ገልጿል። ይህ አዲስ የትብብር ተነሳሽነት፣''ተስፋ ለሰላም'' እንደሚለው፣የሁለቱን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን፣አጠቃላዩን የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና ከጥፋት የሚታደግ አዎንታዊ ክስተት ነው።
ዶቼ ቨለ ያነጋገራቸው፣በዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆኑት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያው አቶ አሉላ ሰሎሞን፣በግጭት አፈታት እና ህዝቦች መቀራረብ ላይ በተለያዩ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀቶች ተሳትፎ በማደረግ ይታወቃሉ።
''ከአሁን በፊትም፣በእንደዚህ ዐይነት ህዝቦችን በሚያቀራርቡ ሥራዎች ተሳትፎ በማድረግ ሳደርግ ቆይቻለሁ፤አስታውሳለሁ ከሁለት ዓመት በፊት የተለያዩ አደረጃጀቶች የተሳተፉበት፣በተለይ በዋናነት፣''ተስፋ ለሰላም'' የዐማራና የትግራይ ህዝቦች የሰላም ግንኙነት ላይ ላይ የሚሰሩ ወገኖቻችን ከፍተኛ ሞራልና መበረታታት ያደረጉበት ዝግጅት አድርገን ነበር፤እና ይሄ መቀጠል አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ።በተለይ ህዝቦች የጎንዮሽ ግጭት ውስጥ መግባት የለባቸውም።''
የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች
''ተስፋ ለሰላም''፣የማንነትም ሆነ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች፣በሁለቱ ህዝቦች መቀራረብና መተባበር፣በሂደት መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ቀዳዳዎችን ሁሉ ዘግቶ፣የተጀመረውንትብብር የበለጠ ማጽናት እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ፣አቶ አሉላም ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
''በተለይ በዋናነት ደግሞ፣ከዚህ ከመሬት ግዛት ይገባኛል፣ከእነዚህ ነገሮች ተያይዘው በዋናነት የሚነሳው የትግራይና የዐማራ ክልል ነው።እነዚህ ህዝቦች ለረጂም ጊዜ የጋራ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው።በጋራ አገሪቱን በመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያረጉ ናቸው። በእነዚህ ህዝቦች መኻከል የሚፈጠር ግጭት ሃገራዊ አደጋውም ከፍተኛ መሆኑን አምናለሁ።ስለዚህ ፋይዳው ከፍተኛ ስልሆነ፣ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ ያለፉ የነበሩ ደግሞ በይቅርታ፣በንግግር፣በውይይት እንዲፈቱ መስራት አለብን በሚል ነው ተሳትፎ እያደረግኹ ያለኹት።''
የታሪክና ባህል ተጋሪ ሕዝቦች
የዓለም አቀፍ የግጭትና የዲፕሎማሲ ተመራማሪ አቶ ነጋልኝ መኳንንት በበኩላቸው፣የትግራይና የዐማራ ህዝቦች፣በባህልም ሆነ በታሪክ በብዙ የሚጋሩ ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸው፣ሊራራቁ የማይችሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
''አይደለም የዐማራና የትግራይ ህዝብ፣ ለረጅም ዓመታት የኖረ፣የባህል የታሪክ መጋራት ያለው፣በብዙ መንገድ ልትለየው የማትችለው ህዝን ነው።ማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች፣የፖለቲካ ልዩነት ሊኖሩ ይችላሉ።የትም ሃገርኢትዮጵያ ውስጥም ይሁን ሌላም ሃገር እንዳለው፤ከእዛ ባሻገር ግን ሁለቱ ህዝቦች በታሪክ መከራዎችን፣ብዙ ጦርነቶችን ብዙ መነሳት መውደቆችን አብሮ የመጡ ህዝቦች ናቸው፤በብዙ መንገድ ልትለያያቸው የማትችላቸው ህዝቦች ናቸው።''
ግንኙነትን የሚያጠናክሩ እርምጃዎች
የትግራይ እና ዐማራ ህዝቦች ግንኙነትንየበለጠ የሚያጠናክሩ፣ከእነሱም አልፎ በአገር ደረጃ፣እንዲሰፋ የሚያግዙ የውይይት መድረኮችን የማመቻቸት ፍላጎት እንዳለው፣''ተስፋ ለሰላም''ጠቁሟል።
ይህ ግብ፣ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባው የግጭትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው አሰገንዝበዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ዐማራው ከኦሮሞ ጋር፣ዐማራው ከደቡቡ ጋር፣ ከጉራጌው ከሌላው ከጋምቤላ ጋር ውይይት ቢያደርግ፣አንድነት ለማድረግ፣በምንም ዐይነት መንገድ አለመዋጋትና ልዩነት ካለ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር እውነታን ይዞ ነው ታዲያ፣ከጀርባው ሌላ የፖለቲካና የጥቅም ሴራ ከሌለበት ዝም ብሎ የዐማራና የትግራይ ሳይሆን ዐማራም፣ትግራይም፣ኦሮሞም ሌላውንም ጨምሮ መሄድ አለበት።''
ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር