1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

የዎላይታ ዞን መምሕራን ሥራ ማቆም፣ የትምሕርት ቤቶች መዘጋት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2016

ትምህርት ቤቶቹ የተዘጉት ከባለፈው የመጋቢት ወር ጀምሮ ደሞዝ አልተከፈለንም ያሉ መምህራን ሥራ በማቆማቸው ነው ተብሏል ፡፡ የትምህርት ቤቶቹን መዘጋት ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ሊቀመንበር በበኩላቸው “ የመምህራኑን ጥያቄ ለመፍታት ማህበሩ ከዞን እና ከክልል ትምህርት ቢሮች እየተነጋገረ ይገኛል “ ብለዋል

https://p.dw.com/p/4fBcs
በዎላይታ ዞን በመምህራን ደሞዝ ስላልተከፈላቸዉ ሥራ በማቆማቸዉ ምክንያት ከተዘጉት ትምሕርት ቤቶች አንዱ
በዎላይታ ዞን በመምህራን ደሞዝ ስላልተከፈላቸዉ ሥራ በማቆማቸዉ ምክንያት ከተዘጉት ትምሕርት ቤቶች አንዱምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የዎላይታ ዞን መምሕራን ሥራ ማቆም፣ የትምሕርት ቤቶች መዘጋት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን በአብዛኞቹ ወረዳዎች የሚገኙትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን የየአካባቢው ወላጆችና መምህራን ገለጹ ፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የተዘጉት  ከባለፈው የመጋቢት ወር ጀምሮ ደሞዝ አልተከፈለንም ያሉ መምህራን ሥራ በማቆማቸው ነው ተብሏል ፡፡ የትምህርት ቤቶቹን መዘጋት ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ሊቀመንበር በበኩላቸው “ የመምህራኑን ጥያቄ ለመፍታት ማህበሩ ከዞን እና ከክልል ትምህርት ቢሮች እየተነጋገረ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

 

የትምህርት ቤቶች መዘጋት በዎላይታ ዞን

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን የሁምባ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ታደሠ ባንጫ ከልጆቻቸው ሦስቱን ትምህርት ቤት በመላክ ሲያስምሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ  ፡፡ ከባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ግን  የእሳችውን ጨምሮ በርካታ የመንደሩ ተማሪዎች  ትምህርት ቤት መሄድ መዘቆማቸውን ነው ለዶቼ ቬለ የገለጹት  ፡፡ “ አሁን ላይ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ እቤት ውለዋል ያሉት ታደሠ “ መምህራን ሥራ በማቆማቸው ተማሪዎች ተስፋ ቆርጠው ወደ ቤት ተመልሰዋል ፡፡ ምናልባት ከዚህ በኋላ በየቀበሌው እንደገና ትምህርት ጀምሩ ተብሎ እስኪታወጅ እየጠበቀን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

የመምህራን ደሞዝ ጉዳይ

በዎላይታ ዞኑ በአብዛኞቹ የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተዘጉት  ከደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ መምህራንሥራ በማቆማቸው መሆኑን የተማሪ ወላጆች ተናግረዋል ፡፡ ከባለፈው የመጋቢት ወር ጀምሮ ደሞዝ ባለማግኘታቸው ሥራ እንዳልገቡ ለዶቼ ቬለ የገለጹት አንድ መምህር ሠው ሳይበላ እንዴት ሊንቀሳቀስ ይችላል ሲሉ ይጠይቃሉ ፡፡

ሥራ ለማቆም የተገደድነው ደሞዝ ባለመከፈሉ እንጂ ሌላ ምክንያት የለንም ያሉት እኝሁ አስተያየት ሰጪ  በዚህም የተነሳ ክፍያችን እስኪፈፀም ሥራ አንገባም ብለን ማስተማር አቁመን እንገኛለን ፡፡ እስከአሁን ችግራችሁ ምንድ ነው ብሎ ያነጋገረን አካል የለም ፡፡ የትምህርት ሥራውም እንደተቋረጠ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

የዎላይታ ዞን መስተዳድር የምክር ቤት አባላት በከፊል
የዎላይታ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት ከሚያደርጋቸዉ ሥብሰባዎች አንዱምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የማህበሩ የመፍትሄ ፍለጋ ጥረት

ዶቼ ቬለ በትምሀርት ቤቶቹ መዘጋት ዙሪያ  የዎላይታ ዞን ትምህርት መምሪያንም ሆነ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ምላሽ የሚሰጠው አካል አላገኘም የትምህርት ቤቶች መዘጋትና የመምህራን የደሞዝ ክፍያ መፍትሄ እንዲሰጠው በዞንና በክልል ደረጃ የሚገኙ የትምህርትና የፋይናንስ ተቋማትን በደብዳቤም በአካልም መጠየቃቸውን የተናገሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አማኑኤል ጳውሎስ “ ደሞዝ ያልተከፈለው አንድ ጊዜ ከማህበራዊ ዋስትና ገንዘብ ሥላልተከፈለ ነው ይላሉ ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወረዳዎቹ ያለባቸው የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ተቆርጦ ነው ይባላል ፡፡ በእኛ በኩል እየቀረቡ የሚገኙ ምክንያቶች በሙሉ አሳማኝ አይደሉም ፡፡ በማህበሩ በኩል የመምህራኑ ደሞዝ እንዲከፈልና የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ከማህበሩ ከዞን እና ከክልል አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ይገኛል “ ብለዋል  ፡፡

ባለፈው ዓመት ምሥረታቸውን ያካሄዱት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በአፈር ማዳበሪያ ዕዳና በበጀት ጉድለት የተነሳ ለሠራተኞቻቸው ደሞዝ መክፈል መቸገራቸውን ዶቼ ቬለ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ