1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባው ረቂቅ አዋጅ እና የፖሊሲ ሰነድ ምን ይዟል?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 12 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጪ ባንኮች በአገሪቱ ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል። ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል በአምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት የውጭ ባንኮች ፈቃድ ሊሰጣቸው እንደሚችል የመንግሥት የፖሊሲ ሰነድ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ የውጭዎቹ ባንኮች እስከ 30 በመቶ ድርሻ ከአገር ውስጥ ባንኮች እንዲገዙ ይፈቅዳል።

https://p.dw.com/p/4LI7H
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአገሪቱ ገበያ ሁለት ሶስተኛ ድርሻ አለው። ምስል DW/E. Bekele

ከኤኮኖሚው ዓለም፦የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባው ረቂቅ አዋጅ እና የፖሊሲ ሰነድ ምን ይዟል?

የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሶስት እስከ አምስት ለሚሆኑ የውጭ ባንኮች ፈቃድ መስጠት የሚያስችለውን ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል። የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ለዓለም አቀፍ ባንኮች የሚከፍተው ይኸ ረቂቅ አዋጅ "በቅርቡ" ጸድቆ ሥራ ላይ እንደሚውል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ከአንድ ሣምንት ገደማ በፊት ተናግረው ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀው እና ዶይቼ ቬለ የተመለከተው የፖሊሲ ሰነድ ከአምስት ዓመታት በፊት ወይም በኋላ ተጨማሪ ንዑስ (የውጪዎቹ ተቀጽላ ባንኮች) ወይም ቅርንጫፍ ባንኮች  እንዲከፈቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በልዩ ሁኔታ ሊፈቅድ እንደሚችል ያትታል። 

በፖሊሲ ሰነዱ መሠረት የተዘጋጀው የባንክ ሥራ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የውጭ ባንኮች በአራት መንገዶች ወደ አገሪቱ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅድ ነው። በተያዘው ዓመት ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት የውጪ ባንኮች በኢትዮጵያ ንዑስ ባንክ (subsidiary bank) እና ቅርንጫፍ ባንክ (branch bank) ማቋቋም ይፈቀድላቸዋል። በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ከሚገኙ ባንኮች እስከ 30 በመቶ ድርሻ መግዛት ለውጪዎቹ ባንኮች የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ ወኪል ቢሮ በመክፈት ሥራቸውን እንዲያከናውኑም ዕድል ይሰጣል። ባንክ ያልሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ወይም የኢትዮጵያ ድርጅቶች በሥራ ላይ በሚገኙትም ይሁን ወደ ፊት በሚቋቋሙት ባንኮች የሚኖራቸው ድርሻ ግን ከ5 በመቶ መብለጥ አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ባንኮች ለውጭ ዜጋ፣ ለውጭ ባንክና ድርጅት መሸጥ የሚችሉት ጠቅላላ ድርሻ ከ40 በመቶ መብለጥ እንደማይችል በረቂቅ አዋጁ ሰፍሯል። 

ረቂቅ አዋጁን እና የፖሊሲ ሰነዱን የተመለከቱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ በተለይ የውጭዎቹ ከአገር ውስጥ ባንኮች 30 በመቶ ድርሻ እንዲገዙ የሚፈቅደው አሰራር የበላይነት እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ። "የኢትዮጵያ የአክሲዮን ይዞታ በጣም የተበታተነ ነው" የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን "አንድ የውጭ ባንክ 30 በመቶ እንዲገዛ የፈቀድክለት እንደሆነ የበላይነት ይኖረዋል። ባንኩን እንደፈለገ ሊዘውረው ይችላል" ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ
የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ለዓለም አቀፍ ባንኮች የሚከፍተው ይኸ ረቂቅ አዋጅ "በቅርቡ" ጸድቆ ሥራ ላይ እንደሚውል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ከአንድ ሣምንት ገደማ በፊት ተናግረዋልምስል picture-alliance/M.Kamaci

ለባንክ ሥራ ማሻሻያ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም ይሁን በፖሊሲ ሰነዱ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓላማዎቹን ለማሳካት "ለንዑስ ባንኮች ትኩረት"  እንደሰጠ አቶ አብዱልመናን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይኸ የውጭ አገር ባንኮች "ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመሠረት እና የሚመዘገብ ተቀጽላ ኩባንያ" አቋቁመው በአገሪቱ የባንክ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ ነው። 

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ተቋማት የሚከፍቱት ንዑስ ባንክ (Subsidiary bank) ከበለጸጉት አገራት የዘርፉን ክኅሎት፣ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን ካፒታል እና የውጭ ምንዛሪ ለመሳብ እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀው የፖሊሲ ሰነድ ላይ ሰፍሯል። ይኸ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ በፖሊሲ ሰነዱም ይሁን በባንክ ሥራ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነው። ረቂቅ አዋጁ እንደሚለው የውጭ አገር ዜጎች እና በውጭ አገር ዜጎች የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በባንኮች ኢንቨስት የሚያደርጉት በውጭ ምንዛሪ መሆን ይገባዋል። 

የረቂቅ አዋጁ መሠረት በሆነው የፖሊሲ ሰነድ ከተዘረዘሩት አምስት ግቦች መካከል ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የብድር እና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቶችን ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል። "በአገሪቱ ያሉ ባንኮች የተቀመጠላቸው የካፒታል መጠን 5 ቢሊዮን ብር ነው። ለውጭ ባንኮች ደግሞ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ይመጣል። የመጀመሪያው የውጭ ባንኮች ሲቋቋሙ እሱን ብር ይዘው ይመጣሉ። ከዚያ በኋላ ግን የውጭ ምንዛሪ ይዘው የሚመጡበት መንገድ እኔ አይታየኝም" ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን የኢትዮጵያ መንግሥት የተለየ የውጭ ምንዛሪ የማግኘ ዕድል እንደማይኖረው አስረድተዋል።

የውጭዎቹ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከአገር ውስጦቹ እኩል መስተናገድ እንደሚኖርባቸው የመንግሥት የፖሊሲ ሰነድ ቢያሳስብም የማመልከቻ እና የፈቃድ ክፍያን በመሳሰሉ ጉዳዮች ልዩነት ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪ የውጪዎቹ ባንኮች ፈቃድ አግኝተው በኢትዮጵያ ሥራቸውን ሲያከናውኑ የተወሰኑ ገደቦች ይጣሉባቸዋል። በረቂቅ አዋጁ እንደሰፈረው ለባንክ ሥራ ከሚጠቀሙባቸው በስተቀር የውጭ ንዑስ ባንኮች ወይም ቅርንጫፍ ባንኮች ከአምስት ዓመታት በላይ ንብረቶች መያዝ አይፈቀድላቸውም። 

የውጭ ባንኮች በረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች ከሦስት ዓመታት ባልበለጠ የሥራ ውል መቅጠር ይፈቀድላቸዋል። ይሁንና ይህ የሚፈቀደው ግን ተመሳሳይ ክህሎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አለመኖራቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ለሦስት ዓመታት የተቀጠሩት የውጭ አገር ዜጎች የሥራ ውል ሲያበቃ በኢትዮጵያዊ ሊተኩ እንደሚገባም በረቂቅ አዋጁ ሰፍሯል። ለሥራው ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ካልተገኙ የውጭ አገር ዜጎች የሥራ ውል ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ሊራዘም የሚችል ቢሆንም ይኸም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጋገጥ አለበት። "መንግሥት ምን አልባት ሐሳቡ በሶስት ዓመታት ውስጥ በውጭዎቹ እና በአገር ውስጥ ባለሙያዎች መካከል የእውቀት ሽግግር ይኖራል ነው" የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን "ማበረታታት" ተገቢ ቢሆንም ገደቡ ባይኖር ወይም አነስተኛ ቢሆን የሚል አቋም አላቸው። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ሥጋቶች ምንድናቸው?

የኢትዮጵያ የባንክ ገበያ ለውጭዎቹ ሲከፈት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሥጋቶችን መንግሥት ያዘጋጀው የፖሊሲ ሰነድ ዘርዝሮ አቅርቧል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ለድንበር ተሻጋሪ ድንጋጤዎች የመጋለጡ ፈተና ነው። ግዙፍ ድንበር ተሻጋሪ ባንኮች ሲከስሩ የሚፈጠረው ቀውስ በሌሎች አገሮች ወደከፈቷቸው ንዑስ እና ቅርንጫፍ ባንኮች ይሻገራል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር ይኸ ከውጭዎቹ ባንኮች በንዑስ እና ቅርንጫፍ ባንኮች ሊሸጋገር የሚችል ቀውስ ጥንቃቄ የሚያሻው እንደሆነ ያስረዳሉ። 

Äthiopien Addis Abeba Tsehay Insurance & Nib Bank
በረቂቅ አዋጁ መሠረት ባንክ ያልሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ወይም የኢትዮጵያ ድርጅቶች በሥራ ላይ በሚገኙትም ይሁን ወደ ፊት በሚቋቋሙት ባንኮች የሚኖራቸው ድርሻ ግን ከ5 በመቶ መብለጥ አይችልም። ምስል DW/E. Bekele Tekle

በባንክ ዘርፉ የውጭ ባለቤትነት መበርታት የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ "በሌላ ሀገር ወይም ክልል ውስጥ ለሚከሰቱ የገንዘብ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል።" ከዚህ በላይ ግን ድንበር ተሻጋሪዎቹ ባንኮች የሚኖራቸው የፈረጠመ አቅም የአገር ውስጦቹን ተወዳዳሪነት ሊያጨናግፍ በሒደትም በውጭ ባለወረቶች እንዲጠቀለሉ ሊያደርግ ይችላል። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ጫና ውስጥ በሚገባበት ወቅት የውጭዎቹ ባንኮች ጥሪታቸውን ቋጥረው ወደ መጡበት ቢመለሱ ሊፈጠር የሚችለው ተጨማሪ ቀውስ ሌላው በፖሊሲ ሰነዱ የሰፈረ ሥጋት ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የፖሊሲ ሰነድ የዓለም አቀፎቹን ባንኮች ውስብስብ ድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ እና አገልግሎት ዝውውር መቆጣጠር ብሔራዊውን ባንክ ሊፈታተን እንደሚችል አስጠንቅቋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን በእርግጥም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ አገር ባንኮችን በመቆጣጠር ረገድ ድክመት እንዳለበት ይስማማሉ። ይኸ ዓለም አቀፎቹን ባንኮች የመቆጣጠር አቅም ጉዳይ ከ1990ዎቹ ጀምሮ እንደ ምክንያት ሲቀርብ የቆየ መሆኑን የሚያስታውሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "ዘላለም እንደ ምክንያት ሊቀርብ ስለማይችል ብሔራዊ ባንክ የግድ አቅሙን ማዳበር አለበት" ብለዋል። 

ለምን ጥቂት ባንኮች?

በኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ መሠረት አዲስ የተመሠረቱትን ጨምሮ 30 ባንኮች ፈቃድ ተሰጥቷቸው ገበያውን ተቀላቅለዋል። የባንኮቹ ጥሪት እስከ ሰኔ 2014 ድረስ ብቻ 2.5 ትሪሊዮን ብር ገደማ ደርሷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የባንክ ዘርፉ በፍጥነት ማደጉን በተደጋጋሚ ቢናገሩም "ተደራሽነታቸው ውስን፣ አገልግሎቶቻቸውም ተለምዷዊ" ሆኗል እየተባሉ ይተቻሉ። የውጭዎቹ ባንኮች ዘርፉ ላሉበት በርከት ያሉ ውስንነቶች መፍትሔ ሊያበጁ እንደሚችሉ ቢታመንም የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቂት ፈቃዶች ብቻ መስጠትን መርጧል። ዶክተር አብዱልመናን ከአገሪቱ ገበያ ሁለት ሶስተኛውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቆጣጠሩ ለዚህ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። "በዚያ ጠባብ ገበያ ላይ ብዙ ባንኮች በአንዴ ቢመጡብኝ ውድድር ይበዛና የባንክ ዘርፉን መረጋጋት ይነሳዋል" የሚል የመንግሥት ሥጋት ለውጭ ባንኮች ሊሰጥ የሚችለውን የፈቃድ ብዛት ውስን እንዳደረገው ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ