1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውኃ አቅርቦት እጥረት በአዲስ አበባ፦ የነዋሪዎች አስተያየት

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ መስከረም 22 2017

አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪዎች በውኃ አቅርቦት ተደጋጋሚ እጥረት አማረሩ ። አንዳንድ ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት፦ በአቅራቢያችን በቂ ውኃ እያገኘን አይደለም፤ በሳምንት አንድ ጊዜ ነው የምናገኘው ብለዋል ።

https://p.dw.com/p/4lL0c
Wasser und Wassermangel
ምስል Wolfgang Maria Weber/picture alliance

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የውኃ ሮሮ

አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪዎች በውኃ አቅርቦት ተደጋጋሚ እጥረት አማረሩ ። አንዳንድ ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት፦ በአቅራቢያችን በቂ ውኃ እያገኘን አይደለም፤ በሳምንት አንድ ጊዜ ነው የምናገኘው ብለዋል ። የንፁሕ ውኃ አቅርቦት እጥረት፤  የዋጋው መወደድ እንዲሁም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የተዝለገለገ ነገር ከውኃው ጋር እንደሚፈስ፤   ለህመም መዳረጋቸውንም ገልጠዋል ። 

እያደገ የመጣውን የከተማውን ስፋት በሚመጥንና ያለቅጥ እየተለጠጠ የመጣውን የሕዝብ ብዛት በሚመጥን መልኩ የውኃ አቅርቦት እየተከናወነ አለመሆኑን ነዋሪዎች በስፋት ያነሱታል፡፡

በርካታ የመዲናዋ አከባቢዎች ላይ የውኃ አቀራረብ ሁኔታው ከቦታ ቦታ ልዩነት ቢኖረውም በርካታ ቦታዎች ላይ ግን ውኃ በፈረቃ በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ቀን ብቻ በቧንቧ የሚቀርብበት ሁኔታ መኖሩንም ተጠቃሚዎች ያነሱታል፡፡ ይህ ደግሞ የሚቀርበው ውኃ ከመጠጥና ከምግብ ስራ ተርፎ ለንጽህና እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ሚውልበት እድሉ ዝቅ ያለ መሆኑንም ነው ተጠቃሚዎቹ የሚገልጹት፡፡

በየሰው ግቢ የሚቀርበው የቧንቧ ውኃ በእጅጉ በሚያጥርባቸው የከተማዋ ዳርቻዎች አከባቢ ደግሞ የቦኖ ውኃ ሲገኝ፤ ሲታጣም ከሌሎች ሰፈሮች በጂሪካን እገዙ የሚጠቀሙ መኖራቸውም ነው የሚገለጸው፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ጥራት የሌለው ውኃ የሚለቀቅበት ጊዜ እንደሚያጋጥም፤ ብሎም በታንከር (ማጠራቀሚያ) ውስጥ የሚቆይን ውኃ ለመጠጥ ለመጠቀም በመገደድ ለጤና መታወክ የሚዳረግ ሰው እንደሚኖርም አስተያየት ሰጪዎች ይጠቆማሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በውኃ አቅርቦቱ ላይ አበክሮ እንዲሠራም ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው ተማጽእኖአቸውን ገልጸዋል ።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ