የወላይታ ክልል የመሆን ጥያቄ እንዲመለስ ግፊት ያደረገው ሰልፍ | ኢትዮጵያ | DW | 17.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የወላይታ ክልል የመሆን ጥያቄ እንዲመለስ ግፊት ያደረገው ሰልፍ

በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ዞኑ ክልል ለመሆን ያቀረበው ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ግፊት ተደርጓል። የደቡብ ክልል ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እያስጠና ቢሆንም በምስረታ ላይ የሚገኘው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሐይለሚካኤል ለማ "እኛ ሕገ-መንግሥታዊ ስላልሆነ የጥናት ቡድኑን አንቀበልም" ሲሉ ይቃወሙታል

የወላይታ ነዋሪዎች የዞኑ ክልል የመሆን ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ዛሬ ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔዱት ሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ። በዛሬው ዕለት በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሔደው እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተገኘበት ሰልፍ የወላይታ ዞን ያሉበት ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ሰላማዊ ሰልፉ በከተማዋ ከሚገኘው የወላይታ ዞን አስተዳደር ፅህፈት ቤት ተነስቶ እስከ ስታዲየም የዘለቀ ነበር። ሰልፉን የወላይታ የአገር ሽማግሌዎች፣ የምሁራን እና የወጣቶች ማኅበራት በጋራ ያዘጋጁት ነው። 

የዞኑ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው በሚወተውተው ሰልፍ የክልልነት ርዕሰ-ጉዳይ ከፍተኛውን ቦታ ይዟል። የሰልፉ ተሳታፊዎች "የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሕዝባችንን የክልል ጥያቄ አዳፍኖ በመያዙ አጥብቀን እንቃወማለን" የሚል መፈክር ይዘው ታይተዋል። "የወላይታ ሕዝብ ክልል የመመስረት ሕገ-መንግስታዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል፤ የክልል ምክር ቤት በአስቸኳይ የወላይታን ጥያቄ ወደ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይላክ" የሚሉ መፈክሮችም ነበሩበት። 

ጥያቄው በተደጋጋሚ መቅረቡን የሚያስታውሱት በምስረታ ላይ የሚገኘው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሐይለሚካኤል ለማ "የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ነው፤ ታሪካዊ ጥያቄ ነው። ስለዚህ ይኸ ጥያቄ መመለስ አለበት" በሚል በአደባባይ መቅረቡን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ሐይለሚካኤል "በዞን ምክር ቤት እና ሕዝቡ በየመንደሩ ተወያይቶበት የቀረበው የክልልነት ጥያቄ ክልል ምክር ቤት ቢቀርብም እስካሁን ድረስ ለምርጫ ቦርድ አልተላከም። ተልኮ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሔድ አልተደረገም" ሲሉ ይናገራሉ። 

ተመሳሳይ በርከት ያሉ ጥያቄዎች የገጠሙት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ጉዳዩን ማጥናት መጀመሩን አስታውቋል። ይኸ ግን በዛሬው ዕለት በሶዶ ከተማ አደባባይ በወጡ ዜጎችም ይሁን በአቶ ሐይለሚካኤል ዘንድ ተቀባይነት ያለው አይመስልም። 

የፌድራል እና የክልል መንግሥታት ካካሔዱት ጥናት በኋላ ረቂቅ ሊቀርብ ዝግጅት መኖሩን እንደሚያውቁ የተናገሩት አቶ ሐይለሚካኤል "እኛ ሕገ-መንግሥታዊ ስላልሆነ የጥናት ቡድኑን አንቀበልም። ሕገ-መንግሥታዊ ሒደቱን ተከትሎ የክልል ጥያቄ እንዲመለስ ነው የምንፈልገው" ሲሉ በአፅንዖት አስረድተዋል። 

በዛሬው ሰልፍ በተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ተኮር ጥቃቶች እንዲቆሙ፤ የፈጸሙም ለሕግ እንዲቀርቡ ተጠይቋል። በሰልፉ የተካፈሉት አቶ ሐይለሚካኤል "ቢሾፍቱ፣ ዝዋይ፤ ሻሸመኔ፤ አዋሳ እና በተለያዩ አካባቢዎች የወላይታ ተወላጆች ብሔርን መሰረት ያደረገ ከፍተኛ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። ለዚህ ፍትኅ እንፈልጋለን። በፍርድ ቤት እንኳ የተከሰሱ የደኢሕዴን ከፍተኛ አመራሮች እስካሁን ድረስ ለፍትኅ አልቀረቡም። ስለዚህ እነዚህ ይኸንን ጥቃት ያስተባበሩ፤ የመሩ እና የፈጸሙ አካላት በሙሉ ለፍትኅ እንዲቀርቡ እንፈልጋለን" ሲሉ ተናግረዋል። 

አቶ ሐይለሚካኤል ለማ በምክትል ሊቀ-መንበርነት የሚመሩት የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የምሥረታ ሒደት ላይ የሚገኝ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። ምክትል ሊቀ-መንበሩ እንደ ወላይታ እና ሲዳማ ዞኖች ሁሉ በቁጥር በርከት ያሉ ክልል የመሆን ጥያቄዎች የቀረቡበት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል "እየፈረሰ" ነው የሚል እምነት አላቸው። 

ክልሉን ለሁለት አስርት አመታት የመራው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የወላይታ ሕዝብን ጥቅም ማስከበር ባለ መቻሉ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ መመስረቱን አቶ ሐይለሚካኤል ለማ አስረድተዋል። 

በሰላማዊ ሰልፉ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተሰናበቱ በርካታ የቀድሞ ወታደሮች መለዮ ለብሰው ተሳትፈዋል። የወላይታ ዞን ባለሥልጣናትም ሰላማዊ ሰልፉ በተካሔደበት ቦታ ተገኝተዋል።  

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ