1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ይገባታል?

ሰኞ፣ መጋቢት 14 2012

የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት በቅርበት የሚያውቁ የሕክምና እና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች ጣልያን፤ ቻይና እና ኢራንን የመሳሰሉ አገሮች ያመሰው የኮሮና ወረርሽኝ 110 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ባሏት አገር ቢስፋፋ የሚፈጠረው ቀውስ አስግቷቸዋል። 15 ሺሕ ገደማ ሰዎችን ለገደለው የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ እንዴት መዘጋጀት ይገባታል?

https://p.dw.com/p/3Zqkf
Deutschland Coronavirus
ምስል picture-alliance/dpa/C. Soeder

ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ለከፋው እንድትዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል

እስካሁን አስራ አንድ ሰዎች በኮሮና መያዛቸውን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ተሕዋሲው በአገሪቱ እንዳይስፋፋ ለመከላከል ያስፈልጋሉ ያላቸውን እርምጃዎች ወስዷል። የአዲስ አበባ "መሸታ ቤቶች" እና ጭፈራ ቤቶች ካለፈው አርብ ጀምሮ መዘጋታቸውን ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 አገራት የሚያደርገውን በረራ መሠረዙን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

አገሪቱ ከዩኒቨርሲቲዎች በቀር ትምህርት ቤቶቿን ዘግታለች። የስፖርት ውድድሮችም አይካሔዱም።በማረሚያ ቤቶች የእስረኞች ጉብኝት ተከልክሏል። ይኸ የእስረኞችን ቤተሰቦች፤ የሐይማኖት መሪዎች እና ጠበቆቻቸውን ይጨምራል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና በጥቁር አንበሳ  ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሲሳይ ለማ "ቫይረሱ ከትንፋሻችን ጋር በሚወጡ ብናኞች ውስጥ ከአንድ ሜትር እስከ ሁለት ሜትር ይጓዛል። [ቫይረሱ] ብዙ መሄድ አይችልም፤ ክብደት አለው። በአካባቢው ባሉ ዕቃዎች ላይ ያርፋል። ንክኪ ሲኖር እጃችን ላይ ሊያርፍ ይችላል" የሚሉት ዶክተር ሲሳይ ለማ በስኳር፣ ልብ እና ደም ግፊት ሕሙማን እና ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ እንደሚበረታ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። የበሽታ መከላከል አቅማቸው ከጤናማዎች አንፃር የተዳከመ፤ ትንባሆ የሚያጤሱ እና አልኮል የሚጠጡ ሰዎችም ጥንቃቄ ሊያደርጉ  እንደሚገባ ዶክተር ሲሳይ እስካሁን የሕክምና ባለሙያዎች በእጃቸው የገባውን መረጃ መሰረት አድርገው ይመክራሉ።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ "የኮሮና በሽታ በጣም አደገኛ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት መተላለፊያ መንገዱ ቀላል ነው። በተለይ ደግሞ ማኅበረሰባዊ መሥተጋብራችን ቅርብ ለሆነ እጅግ በጣም በቀላሉ መተላለፍ የሚችል በሽታ ነው። እኛ እርስ በርስ በጣም ቅርብ ነን" ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ትዝአለኝ ኢትዮጵያ በቅጡ ካልተዘጋጀት ይኸ ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። "የቫይረሱ ዕድገት እየተራባ የሚሔድ (exponential growth) ነው። ለምሳሌ እንበልና  50 ሰው መጀመሪያ ላይ ቢያዝ ከ15 ቀን በኋላ 2000 ሰው ይኖረናል። ቀጥሎ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ወደ 91 ሺሕ አካባቢ ሰዎች ሊያዙ ይችላሉ" ብለዋል።

ኮሮና የቻይና፣ የጣልያን፣ የፈረንሳይ፣ የኢራን የጤና ሥርዓቶችን ክፉኛ ፈትኗል። በጀርመኑ ሐይድልበርግ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ዘገዬ ኃይሉ «የኮሮና በሽታ 2019 (#COVID19) ዘመናዊ ሕክምና ላላቸው አገራት ከፍተኛ ጭንቀት ሆኗል። አሁን ባለው ሁኔታ ስናየው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቀጥሎ ከፍተኛ ማኅበራዊ ሥጋት በሁሉም አቅጣጫ የፈጠረ ሆኖ ነው የተገኘው" ሲሉ የተፈጠረውን ቀውስ ያስረዳሉ።

"በተሕዋሲው ከተያዙ ሰዎች 20 በመቶው ለህክምና ወደ ሆስፒታል ስለሚያመሩ እና በሽታው አሁን ያለው የመተላለፍ ባሕሪ እና ያለው የሆስፒታሎች አቅም አለመመጣጠን ይኸን ክስተት በጣም አስጊ እንዲሆን አድርጎታል። ሁለተኛው ለዚህ በሽታ መድሐኒት አለመኖሩ ነገርየው እንዲባባስ አድርጎታል» ሲሉ ዶክተር ዘገዬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና በጥቁር አንበሳ  ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሲሳይ ለማ እና  በጀርመኑ ሐይድልበርግ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ዘገዬ ኃይሉ በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ውይይቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ